በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር የሀያ አራተኛ ሳምንት ሶስተኛ ዕለት ጨዋታ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ፋሲል ከነማ በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘዉን ለገጣፎ ለገዳዲ 2ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
በሀያ ሶስት ነጥቦች እና አስራ አንድ ደረጃዎች ተበላልጠው የዕለቱ የቀን ዘጠኝ ሰዓት መርሐግብር ለመከወን ወደ ሜዳ በገቡት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ሁለቱም ቡድኖች ለግብ የቀረቡ ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ ተስተውሏል። በተለይ አፄዎቹ የጨዋታውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እና አልፎ አልፎም በመስመር በኩል ብልጫ በመዉሰድ በጨዋታዉ በቁጥር በርከት ባሉ አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው በአብዛኛው የጨዋታ እንቅስቃሴ በመከላከል ሲያሳልፉ የነበሩት ለገጣፎዎችም በጨዋታው ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸዉ ከቀኝ መስመር በኩል ጥሩ ኳስ በረጅሙ ለናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ተጫዋቾች ለጥቂት ያመለጠዉ ኳስ አጋጣሚው በአፄዎቹ በኩል አስቆጭ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚች ሙከራ በኋላም በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት በሜዳዉ የቀኝ መስመር በኩል የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ አጥቂዉ ካርሎስ ዳምጠዉ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ የግቡን ቋሚ ነክታ ወደ ዉጭ የወጣችበት አጋጣሚም በለገጣፎዎች በኩል የተደረገች አስደናቂ ሙከራ ነበረች ።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ለገጣፎዎች በመሐመድ ፤ አማኑኤል እንዲሁም ካርሎስ ዳምጠዉ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም በተቃራኒው በአጋማሹ መገባደጃ ወቅት ግን ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። በዚህም በ45ተኛው ደቂቃ ከአፄዎቹ የግራ ማጥቃት በኩል አማካዩ በዛብህ መለዮ ያቀበለዉን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸዉ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችለዋል።
ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ የጨዋታ መንግድ የቀጠለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በሙከራ ረገድ ግን በንፅፅር የተቀዛቀዘ አጋማሽ ሁኖ ተስተውሏል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም በ52ተኛዉ ደቂቃ ላይ አፄዎቹ ጥሩ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር በዚህም ከመሐል ክፍል ይሁን ለአጥቂዉ ኦሲ ማዉሊ ያቀበለዉን ኳስ ግብ ጠባቂዉ በፍጥነት ያወጣዉ አጋጣሚ ጥሩ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል።
በንፅፅር ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ ደካማ የነበሩት ለገጣፎዎች በሁለተኛዉ አጋማሽ ተጠቃሽ የሚባል ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ፤ በተቃራኒው በጨዋታውም የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ግን ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም በዕለቱ ድንቅ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ ሱራፌል ዳኛቸዉ ከመሐል ሜዳ አካባቢ ድንቅ ኳስ የኮፊ ሜንሳህ መረብ ላይ አሳርፎ ክለቡ ፋሲል ከነማ 2ለ0 እንዲያሸንፍ ማድረግ ችሏል።
ዉጤቱን ተከትሎም በጨዋታዉ ድል የቀናቸዉ አፄዎቹ ነጥባቸዉን ወደ 37 ነጥብ ከፍ በማድረግ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በተቃራኒው ለገጣፎዎች ደግሞ በ11 ነጥብ በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።