*.,,የተጨዋቾች ማህበርና ፌዴሬሽኑ የክስ ፋይል ተዘግቷል አልተዘጋም በሚል እየተወዛገቡ ነው…
*….ሀድያ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አዳማ ከተማና ሰበታ ከተማ መግለጫውን ተቃወሙ..
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊና ስራ እእፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ጋር ተያይዞ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ተቃውሞ ገጠመው።
ውድድር የመምራት እንጂ በምርጫው በድምጽ እንኳን የማይወከለው ሊግ ኩባንያ ዛሬ 8.30 ላይ በኢንተርኮንቴንታል ሆቴል መግለጫ መጥራቱ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተቃውሞ ገጥሞታል።
- ማሰታውቂያ -
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ ፌዴሬሽኑ አክሲዮን ማህበሩ የጠራውን መግለጫ እንዲሰርዝ ደብዳቤ መጻፉ ታውቋል። ከምርጫው ጋር ተያይዞ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው እስከ ነሀሴ 6/2014 ውሳኔውን እንዲያሳውቅ እየተጠበቀ ባለበት ሰአት የሊግ ኩባንያው የመግለጫ ጥሪ በኮሚቴው ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ተሰግቷል።
ሊግ ኩባንያው መግለጫ ለመስጠት በቦርድ ደረጃ መወሰኑ ከውድድር ውጪ በፌዴሬሽኑ ሀላፊነት ላይ ጣልቃ መግባቱን ያሳያል ብሏል ምንጫችን.. ክለቦች ከተሰጠው ሀላፊነት በላይ መራመዱን በማየት የተቃውሞ ደብዳቤ ሊጽፉ እንደሚችሉ እየተነገረም ነው።ሊግ ኩባንያው የንግድ ስራ ድርጅት የሚሰራ ተቋም ሆኖ የጠቅላላ ጉባኤ አባል ሳይሆን ስለ ጉባኤውና ምርጫው ማውራት ተገቢ አይደለም ተብሏል። ሊግ ኩባንያው አንድ ድምጽአለኝ ቢልም ፌዴሬሽኑ ግን ጠቅላላ ጉባኤው በ2006 የፌዴሬሽኑ መዋቅር ይቀጥል መባሉን በመግለጽ ኩባንያው ድምጽ የለውም ብሏል።
ከምርጫው ጋር ተያይዞ ቅሬታቸውን ለፊፋ ያሰሙ ወገኖች ያሉ ሲሆን ካፍም ሆነ ፊፋ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።ሶስት አባላት ያሉት የምርጫው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን መርምሮ አጠቃላይ ውሳኔውን እስከ መጪው ዓርብ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ ዜና ወልቂጤ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና።፣ አዳማ ከተማና ሰበታ ከተማ ከደቂቃዎች በኋላ የሚሰጠው የሊግ ኩባንያውን መግለጫ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። ሁለቱም በየግላቸው በሰጡት መግለጫ ” ከተሰጠው ሀላፊነት ውጪ የጠራው መግለጫ ህገወጥና እንደ አክሲዮን ማህበር አባልነታችን የማይመለከተን ነው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የተወዳዳሪዎችን አቤቱታ እየተከታተለ ባለበት ሰአት መካሄዱ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾችና ባለሙያዎች ማህበር ለመደበኛ ፍ/ቤት ያቀረበው ክስ ፋይሉ ተዘግቷል።
ባለፈው ዓርብ በቂርቆስ መደበኛ ፍርድቤት የነበረው ቀጠሮ የማህበሩ ጠበቆች ባለመገኘታቸው ፍ/ቤቱ የክስ ፋይሉን እንደዘጋው ከፌዴሬሽኑ የደረሰን መረጃ ያስረዳል።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ፍትሀብሄር ችሎት ጠበቆቹ ባለመገኘታቸው ፋይሉ ተዘግቷል በማለት ፌዴሬሽኑ ቢናገርም ማህበሩ ግን ፍጹም ውሸት ነው ለመጪው አርብ ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ ጉዳዩ የሚታይ ይሆናል በማለት አስረድቷል። የሁለቱን ወገኖች ክርክር ተከትሎ በተገኘ ሌላ ገለልተኛ መረጃ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ሰዎች ቀድመው ደርሰው የማህበሩ ጠበቆች አልመጡም በሚል ክሱ እንዲነሳ ጠይቀው ከወጡ በኋላ የማህበሩ ጠበቆች ፍ/ቤቱ ይደርሳሉ ይህን ተከትሎ የፌዴሬሽኑ ጠበቆችና ተወካዮች እንዲገቡ ሲፈለጉ ባለመገኘታቸው ፍርድ ቤቱ ለመጪው ጠዋት አራት ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል። ፌዴሬሽኑ ግን አሁንም የደረሰው ነገር እንደሌለ እየገለጸ ነው።