👉” ከጠቅላላ ጉባኤው አባላት ውጪ በሌላ ወገን መፍትሄ ለማምጣት የሚሯሯጡ ካሉ አይሆንም ሀገር የሚያስቀጣ ድርጊት ነው””
መቶአለቃ ፈቃደ ማሞ
/የሊግ ኩባንያው ፕሬዝዳንት/
ከጠቅላላ ጉባኤው አባላት ውጪ በሌላ ወገን መፍትሄ ለማምጣት የሚሯሯጡ ካሉ አይሆንም ሀገር የሚያስቀጣ ድርጊት እንዳይሆን
“በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መረጋጋትና ሰላም ሲኖሩ የሊግ ኩባንያው ህልውና ይረጋገጣል” ሲል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በሰጡት መግለጫ የሊጉ የስራ አመራር ቦርድ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ወደ ሊጉ እንዳይመጣ መስተካከል እንዳለበትና ለስፖርት ቤተሰቡ እንዲገለጽ መወሰኑን አስረድተዋል።
“ሱፐር ስፖርት በሄደባቸው አገራት መሃል በሊጉና በፌዴሬሽኑ መሀል አለመግባባት ሲፈጠር ከየሀገሩ ጥሎ ወጥቷል” ያሉት የሊግ ኩባንያው ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ማሞ ” ለዚህም ኬንያና ናይጄሪያ ምሳሌ ናቸው ሱፐርስፖርት ሰላም ይፈልጋል ሰላም ካለ ዕድገት ይፈጠራል” ሲሉ ገልጸዋል።
የመግጫው አንኳር በፌዴሬሽኑ ላይ የታየው የአሰራር ክፍተት በምርጫው ላይ የፈጠረው ጫና ወደ ሊጉ እንዳይወርድ መሆኑን በማሳሰብ መግለጫቸውን ሰጥተዋል። “የፌዴሬሽን ዋና መስሪያ ቤት በፊፋ መልካም ፈቃድ በ95 ሚሊየን ብር ግዢ ቢደረግም ስሙ ወደ ፌዴሬሽን አልዞረም በዚህም ህንጻው ስሙ ባለመዞሩ የፌዴሬሽኑ ነው ማለት አይቻልም ህንጻው ስሙ ባለመዞሩ አራት አመት ሙሉ ገቢ አላገኘም ትልቅ ኪሳራ ሆኗል በኛ በኩል የባለቤትነት መብቱ መቼ ይገኛል? የመንግስት የሚመለከተው አካልስ ለምን ዝም አለ? እንዴትስ ስም ሳይዞር ሙሉ 95 ሚሊዮን ይከፈላል? እስከ መቼ ነው ስሙ የማይዞረው ? መንግስት ገቢ አጥቶ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካልስ እንዴት ዝም አለ” ሲሉ ጠይቀዋል።
ስለ ትጥቅ ስምምነቱ የተናገሩት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ” በፊት የነበረው አመራር ከኤሪያ ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጋር የነበረው ውል በማፍረስ የ100ሺህ ዶላር ኪሳራ ለመክፈል ቢስማማም ካምፓኒው ሀሳቡን ቀይሮ ሳያስከፍል ቀርቷል ለምን እንደቀረም አይታወቅም አሁን ያለው ግን ከአምብሮ ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጋር አወዛጋቢ ውል ተዋውሏል። ይህን ውል ላዋዋለው ግለሰብ 200ሺህ ብር መክፈላቸው ግን ያሳፍራል” ሲሉ ተናግረዋል። መቶ አለቃ አክለውም የአውሮፕላን ቲኬት የቢዝነስ ክፍል ወጪ በማድረግ ለአንድ የፌዴሬሽኑ አመራር የግል ጉዞ 385 ሺህ 435 ብር
ወጪ መደረጉም ያለውን ክፍተት ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል።
በዚህ የምርጫ ወቅት ስለፌዴሬሽኑ ችግር ማውራት የአቶ ኢሳያስ ጅራን የመመረጥ እድል ለማጥበብ አይመስልም ወይ? የተባሉት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ
“እኛ ሌላ ሀሳብ የለንም የተፈጠሩ አስተዳደራዊ ችግሮች ወደ ሊጉ እንዳይመጣ የሚመጣው አመራር እጁን እንዲሰበስብ ለማድረግ ነው እንደተቋም ለኳሱ የሚጠቅመው እገሌ ነው ብለን በይፋ የመናገር መብት አለን አሀን ግን የመቀስቀስ ሀሳብ የለንም” ሲሉ መልሰዋል።
የተፈጠሩት ችግሮች ሙስና ናቸው ወይስ በስህተት? በናንተ በኩል የደረሳችሁበት ድምዳሜ ምንድነው የተባሉት የቦርድ ሰብሳቢው “የተፈጠረው ችግር በእንደዚህ ምክንያት ነው ማለት አንችልም የአውሮፕላን ቲኬት ግዢው በግዴለሽነት ይመስላል የህንጻው ግዢ ግን ግራ ያጋባል በጠቅላላ ጉባኤ የኦዲተሩ ሪፖርት በመንግስት ቢሮክራሲ የህንጻው ስም አልዞረም ለመንግስት የሚከፈል ክፍያ ሳይከፈልና ስሙ ሳይዞር ለግዢው በእምነት ሙሉውን ከፍለናል ከተባለ ሀላፊነት መውሰድ የግድ ይኖርባቸዋል” ሲሉም አሳስበዋል።
“ማንንም ይምጣ ማንም በምርጫው ስጋት የለብንም አሁን የቀረቡት ተወዳዳሪዎች በተመለከተ ለአንዳቸውም አናደላም ጠቅላላ ጉባኤ ድምጽ ይስጥ የተሰጠውን ድምጽ አንቀበልም አንልም የመግለጫ ጊዜው በተመለከተ ለኛ አሁን ጊዜው ነው ምርጫው የኛን የሊጉ ህይወት ይወስናል የምትመርጡትን አመራር ጀርባ አጥኑና ምረጡ እያልን ነው” ሲሉ መልሰዋል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የሚወዳደሩት የኢት.ቡና ዋናስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝን በተመለከተ የተናገሩት የሊግ ኩባንያው ፕሬዝዳንት ” የአቶ ገዛኸኝ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መሳተፍ መብቱ ነው ላቆመው አልችልም ሊግ ኩባንያው ላይ ስላለሁ አንተ አትወዳደርም ማለት አልችልም መግለጫውንም የሰጠሁት ገዛኸኝን ልጠቅም አይደለም እንኳን ለፌዴሬሽን ፕሬዝዳትነት ለሀገር ፕሬዝዳንትነት መወዳደር መብት ነው ” ሲሉ አስረድተዋል።
“የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሀፊ ደብዳቤ ልኮልኛል በጣም አሳፋሪ ነው ጸሀፊው ገለልተኛ አለመሆኑ ያሳዝናል ብትናገር በህግ እንጠይቅሀለን ብለውኛል ለመጠየቅም ዝግጁ ነኝ” ያሉት መቶ አለቃ ፈቃደ ” ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጥሩ ሰው ናቸው ተሰብስበን ስንነጋገር እንቢ አይቻልም ብለው አያውቁም ግን የተባባልነው አይፈጸምም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“እንኳንስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ቀርቶ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዝዳንቱ ሲመረጡ ወጥተን አደባባይ እንናገር የለ አሁንስ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታንዊ ምርጫ ላይ ቢነገር ለምን ይገርማል..?” ያሉት መቶ አለቃ “ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ፕሬዝዳንት መሆን አለባቸው የለባቸውም የሚለው ያከራክራል ፊፋ በቀጥታ ሊያዝ አይችልም ሌሎቹ ግን በፊፋ መመሪያ ብቻ ነው የሚሰሩት የምርጫ አስፈጻሚና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት የተመረጡትም የማይጣሰውን የፊፋን ህግ ጥሰው ነው ” በማለት አስረድተዋል።
ስለ ችግሩ መፍትሄ የተጠየቁት መቶ አለቃ ፈቃደ “ቁጭ ብለን ተነጋግረን ተወያይተን ችግሩን ገምግመን የማስተካከያ ርምጃ ለመውሰድ ከተዘጋጀን መፍትሄ ይመጣል ነገር ግን ካልተስማማን ፊፋ ይዳኘናል ከጠቅላላ ጉባኤው አባላት ውጪ በሌላ ወገን መፍትሄ ለማምጣት የሚሯሯጡ ካሉ አይሆንም ሀገር የሚያስቀጣ ድርጊት እንዳይሆን ያሰጋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አስተያየት ይስጡ