በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛዉ እየተመራ በዘንድሮው የውድድር አመት በፕሪሚየር ሊጉ ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘዉ ባህርዳር ከተማ በዛሬው ዕለት ቀን 10 ሰዓት ላይ በወራጅ ቀጠናዉ የሚገኘዉን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ገጥሞ ከመመራት ተነስቶ ከ83ተኛዉ ደቂቃ በኋላ ባስቆጠራቸዉ ሶስት ጎሎች ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።
ያን ያህል ለዕይታ ሳቢ ባልነበረዉ የሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ አስራ አምስት ያህል ደቂቃ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ከራሳቸዉ የሜዳ ክፍል ለማዉጣት ሲሞክሩ እና ወደ ተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ተስተዉለዋል ፤ በተጨማሪም በመስመር ተጫዋቾቻቸው በኩል ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠረ ሲጥሩ የተስተዋለ ቢሆንም ያን ያህል ግን ዉጤታማ ሲሆኑ አልተመለከትንም።
በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ14ተኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራን በባህርዳር ከተማ በኩል አስመልክቶናል። በዚህም ፍፁም ጥላሁን ከቀኝ መስመር ተመላላሹ መሳይ አገኘሁ የተቀበለዉን ኳስ ከሳጥን ዉጭ አክርሮ ወደ ግብ ልኮ የነበረ ቢሆንም የግቡ ቋሚ የመለሰበት አጋጣሚ የጨዋታው የመጀመሪያ ተጠቃሽ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል።
- ማሰታውቂያ -
ከላይ ከተጠቀሰዉ ሙከራ ውጭ እምብዛም የሚጠቀስ የግብ ሙከራም ሆነ ማራኪ የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ ያልተመለከትንበት የዕለቱ ጨዋታ በተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በንፅፅር ተሻሽለዉ የተመለሱት ኢትዮ ኤሌትሪኮች በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የቀኝ መስመር ተመላላሹ ጌቱ ሀይለማርያም ያሻገረለትን ኳስ አማካዩ አብነት ደምሴ በግንባር በመግጨት ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑ እንዲመራ ማድረግ ችሏል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ባህርዳር ከተማዎች እስከ 50ኛዉ ደቂቃ ድረስ ያልታየባቸዉን የኳስ ቅብብል እና ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ቡድን ሳጥን የመድረስ ሁኔታ አስመልክተዉ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የጀመሩ ሲሆን በዚህም በ60 እና 61ኛዉ ደቂቃ ላይ የመሐል ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል እና የፊት መስመር ተጫዋቹ ዱሬሳ ሹቤሳ በተከታታይ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
በዚህ ሂደት በቀጠለው እና ግብ ካስቆጠሩ በኋላ አመዛኙን ሰዓት በመከላከል ያሳልፉ የነበሩት ኤሌትሪክትሪኮች በ66ተኛዉ ደቂቃ ላይ አማካያቸዉን በቀይ አጥተዋል። በዚህም የመሐል ሜዳ ተጫዋቹ አብነት ደምሴ የባህርዳር ከተማዉ አማካይ ያብስራ ተስፋየ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል። ይሄንን ተከትሎ የተገኘዉን ቅጣት ምት ፊአድ ፈረጃ አክርሮ ወደ ግብ ልኮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ታካ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር ማጥቃታቸዉን አጠናክረዉ የቀጠሉት ባህርዳር ከተማዎች በ83ተኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም መሳይ አገኘሁ ከማዕዘን ያሻማትን ኳስ ከተጨራረፈች በኋላ ፉአድ ፈረጃ አግኝቷት ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጫናቸዉን ይበልጥ ያጠነከሩት ባህርዳር ከተማዎች በ87ተኛዉ እና በጭማሪ ደቂቃ በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ሁለት ጎሎችን አስቆጥረዉ ከመመራት ተነስተዉ አዲስ አዳጊዉን ቡድን ማሸነፍ ችለዋል።