ከደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ ለስድስት ቀናት ገደማ ያለ ልምምድ የቆየዉ የገብረ ክርስቶስ ቢራራዉ ወልቂጤ ከተማ እና በአስራ ሰባተ ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቀጠና ላይ አስራ አራተኛ ደረጃ ተቀምጦ የነበረዉ የመሳይ ተፈሪዉ አርባምንጭ ከተማ ያደረጉት የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ 2ለ2 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።
በተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን አስር ያህል ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል በመስመር እና ከተከላካይ ክፍል በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ተጋጣሚ ቡድን ላይ ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ በዚህም በ12ተኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዷል። በዚህም ከአርባምንጭ ተከላካይ ክፍል የተጣለዉን ኳስ ተመስግን ደረሰ ለፊት አጥቂዉ አህመድ ሁሴን አቀብሎት አጥቂዉ ኳሷን በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ እና በሙከራ ረገድ እምብዛም በነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም የአርባምንጭ ከተማዉ የመስመር አጥቂ ተመስገን ደረሰ በድጋሚ በቅጣት ምት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ኳሷ በግቡ አናት ላይ ለጥቂት ወጥታለች። ከዚች ሙከራ በኋላ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ ለመማግኘት ሲጥሩ የነበሩት ክትፎዎቹ በተደጋጋሚ ከመስመር ከማነሱ ኳሶች እና የፊት መስመር አጥቂዉን ጌታነህ ከበደ ማዕከል ያደረጉ ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ሳይሳካላቸዉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በተነቃቃ መንፈስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት ክትፎዎቹ አጋማሹ ከተጀመረ ከ10 ያህል ደቂቃዎች በኋላ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የአርባምንጭ ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተከትሎ የተገኘችዉን ኳስ በቅርበት የነበረዉ አምበሉ ጌታነህ ከበደ ከርቀት ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።
ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ በተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ከአስር ደቂቃ በኋላ ወልቂጤ ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም በድጋሚ የአርባምንጭ ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተከትሎ ተስፋየ መላኩ የሰጠዉን ኳስ ተቀይሮ የገባዉ አቤል ነጋሽ ወደ ግብነት በመቀየር ወልቂጤዎች እንዲመሩ ማድረግ ችሏል።
ከመምራት ወደ መመራት የተሸጋገሩት አርባምንጮች በተደጋጋሚ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸዉን ግብ ለማስቆጠር በፊት መስመር አጥቂዎቹ አህመድ ሁሴን እና ተመስገን ደረሰ አማካኝነት ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን በዚህም ዉጥናቸዉ ሰምሮ የአቻነት ግብ በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ተመስገን ደረሰ ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ ኤሪክ ካፓይቶ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። በዚህም የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ 2ለ2 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።