በአቤኔዘር አበበ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሉን ሲያስቀጥል፣ መቻል የመሪነት እድሉን አምክኗል!
ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ሀድያ ሆሳዕና
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀድያ ሆሳዕናን 2-0 በመርታት የድል ጉዞውን ማስቀጠል ችሏል።በጨዋታው የበላይነቱን በመያዝ የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ9ኛው ደቂቃ ተመስገን ብርሃኑ ወደ ጎል ያሻማትን ኳስ የሀድያ ሆሳዕናው ተጫዋች ዳግም ወንድሙ በራሱ ጎል ላይ በማስቆጠሩ መሪነቱን ወስዷል።ፈረሰኞቹ ጫናቸውን በመቀጠል የተከላካዮቹ ስተት በመጠቀም በ44ኛው ደቂቃ ቢላል ገመዳ በጥሩ ሁኔታ ያመቻቸውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ወደ ጎልነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ወደ 2-0 አሳድገዋል።ሀድያ ሆሳዕና በመጀመሪያው አጋማሽ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ወደ ዕረፍት አምርቷል።ከዕረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢያሳይም ጎል ማስቆጠር አልቻለም። ሀድያ ሆሳዕና በዙም ሙከራ ሳያደርግ በመጨረሻም ጨዋታው በፈረሰኞቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 0-0 መቻል
በዚህም መቻል የሊጉን መሪነት ለመያዝ የነበረውን ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።
በመጀመሪያው አጋማሽ መቻል ከኋላ ኳስ መስርቶ ለመጫወት ሲቸገር ታይቷል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአብዛኛው ትኩረቱን በመከላከል ላይ በማድረግ አጋማሹ ያለ ጎል እንዲጠናቀቅ አድርጓል።ከዕረፍት መልስ መቻል የማጥቃት እንቅስቃሴውን ማሻሻል ቢችልም በ62ኛው ደቂቃ በረከት ካሌብ በስምዖን ማሩ ላይ በሰራው ጥፋት ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ተሰናብቷል።በዚህም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የቁጥር ብልጫ ቢያገኝም ወደ ጎልነት መቀየር አልቻለም። መቻልም በተጫዋች ብልጫ ስር ቢገባም ውጤቱን መቀየር ሳይችል ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።
አስተያየት ይስጡ