መነሻ ገጽ ዜናዎች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምልከታ
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምልከታ

አጋራ
አጋራ

የሊጉ የአንደኛ ሳምንት ምልከታና የሁለተኛ ሳምንት መርሀግብር…

የ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀግብር ባሳለፍነው ሳምንት በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች የውድድር ዘመን ጉዞውን መጀመሩ ይታወሳል። የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን በመጀመሪያ ሳምንት መርሀግብሩ ባለ ሜዳ የሆኑ ሁሉም ቡድኖች ማሸነፍ ሳይችሉ ያጠናቀቁበት ሲሆን ከሜዳ ውጪ የተጓዙ ክለቦች በአንፃሩ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ተፅዕኖ ውስጥ ሳይከታቸው ሦስት ነጥቦችን ያሳኩበት ነበር። በሳምንቱ ከነበሩ ዘጠኝ ጨዋታዎች ከሜዳ ውጪ የተጫወቱ ስድስት ቡድኖች ማሸነፍ ሲችሉ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ በኢትዮጵያ ፕሪምየር የ29 አመታት ጉዞ ውስጥ በተለይ ከሜዳ ውጪ ክለቦች ተጉዘው በዚህ ቁጥር ልክ በአንድ የጨዋታ ሳምንት ብቻ ማሸነፋቸው በሊጉ አዲስ ታሪክ ሆኖ መመዝገብ ችሏል።

ፕሪምየር ሊጉ ባለፈው ዕርብ መስከረም 29/2019 በሁለት ጨዋታዎች መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን አዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1ለ0 መርታት ሲችል ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም ዐይተን 29ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ጎል የአመቱ የመጀመሪያ ጎል መሆን ከመቻል አልፋ በፍፁም ቅጣት ምትም መቆጠሯ ሌላ የቀዳሚነት ስፍራ ላይ እንድትቀመጥ አስችሏታል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ጨዋታ የሀላባ ስታዲየም ሲያስተናግድ የሊጉ አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ ደግሞ ከወልዋሎ ጋር 1ለ1 ባጠናቀቀበት ጨዋታ ላይ 49ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በግንባር ገጭቶ ከመረብ ያሳረፋት ጎል ደግሞ በክፍት ጨዋታ መረብ ላይ ያረፈች ቀዳሚዋ ግብም መባል ችላለች። 39 ቢጫ ካርዶች በተመዘዙበት የጨዋታ ሳምንት ውስጥ የሀላባ ከተማው የመስመር ተጫዋች ያሬድ መሐመድ 21ኛው ደቂቃ ላይ የተመለከታት ቢጫ ካርድ ደግሞ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያዋ ቢጫ ካርድ ስትሆን አንድም ቀይ ካርድ ግን አልተመዘዘም።

በጨዋታ ሳምንቱ ሌላ መረጃ የሆሳዕናው አብዩ ኤርሳሞ ስታዲየም ከስድስት አመታት በኋላ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በጋሞ ጨንቻ ተወካይነት ከስምንት አመታት በኋላ የሀገሪቱን ትልቅ የሊግ ዕርከን ዳግም በማስናገድ ወደ ቀደመ ክብራቸው መመለስም ችለዋል። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2019 የውድድር ዘመን ላይ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አድጎ መወዳደር የጀመረው ሀላባ ከተማ ከመንግስት እና ከህብረተሰቡ በተውጣጣ ገንዘብ ራሱ ባስገነባው ስታዲየም ላይ መጫወት መቻሉ በልዩነት በሳምንቱ የሚወሳው ከፍ ያለ የትኩረት ነጥብ ነበር። በሌላ ጉዳይ ደግሞ በየአመቱ እንከን የማያጣው የሀገራችን የዳኝነት ጉዳይ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንትም በተመሳሳይ ችግሮችን አስመልክቶን አልፏል። ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡና ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በጉልህ የዳኝነት ክፍተትን መታዘብ የቻልን ሲሆን በቀጣይም መሻሻል እንዳለበት ሀገሬ ቴሌቪዥን በስፍራው በመገኘት መታዘብ ከቻለቻቸው ሁነቶች ለመገንዘብ ችሏል።

የሊጉ የሁለተኛ ሳምንት መርሀግብሮች ነገ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች የሚቀጥል ሲሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም በመጀመሪያው ሳምንት ሽንፈት የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ ነጥብን ከያዘው ነገሌ አርሲ ጋር ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሲገናኙ ሀላባ ከተማ በሜዳው ባህርዳር ከተማን አስር ሰዓት አዳማ ከተማ በበኩሉ ሸገር ከተማን አስራ ሁለት ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ላይ ያስተናግዳል። ቅዳሜ የሳምንቱ ትልቁ ደርቢ ሁለቱን የመዲናይቱን አንጋፋ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን ሲያገናኝ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ዕሁድ ሆሳዕና ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ ከሀዋሳ እና ከሲዳማ ሀዋሳ ላይ ሦስት ነጥቦችን የሸመቱት መቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የሚገናኙ ሲሆን ወልዋሎ ከፋሲል ከነማ እንዲሁም ጋሞ ጨንቻ ከሲዳማ ቡና ሊያደርጉት የነበረው መርሀግብር ወልዋሎ እና ሲዳማ ባለባቸው አህጉራዊ ውድድር ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ የዞሩ ጨዋታዎች ሆነዋል።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...