ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በፕሪምየር ሊጉ ያሳለፈው ኬኒያዊው ግብ ጠባቂ 13ኛ ክለቡን ሊቀላቀል ከጫፍ መድረሱ ሲታወቅ በፊፋ ቅጣታቸው የፀናባቸው ፈረሰኞቹም የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂ መጠቀማቸውም የሚቀር አይመስልም።

በአሁኑ ሰዓት ለኬኒያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ላይ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ፋሩክ ሻኪሎ ከአንድ አመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቆይታው በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ናይሮቢ ዩናይትድ የተባለ ክለብን ለመቀላቀል ከጫፍ መድረሱን የሀገሪቱ እውቅ የሚዲያ ገፆች ዘግበዋል።
ሁሹሩ በተባለው የኬኒያ ክለብ የክለብ ህይወቱን ጀምሮ በታላንታ ፣ ቱስካር ፣ ሞሆሮኒ ፣ ፖስታ ሬንጀርስ ፣ ቫንዳሪ ፣ ካካሜጋ እንዲሁም ወደ ታንዛኒያ አምርቶ ለያንግ አፍሪካ ፣ ኬ ኤም ሲ እና ሚትቡዋ ሹገር ከተጫወተ በኋላ በድጋሚ ወደ ሀገሩ ኬኒያ ተመልሶ ካካሜጋ እና ኬ ኤስ ቢ ናይሮቢ ተባሉ የሀገሪቱ ክለቦች ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ወደ ሀገራችን መጥቶ ከፈረሰኞቹ ጋር የአንድ አመት ቆይታን ያደረገው ይህ ተጫዋች ወደ ሀገሩ ተመልሶ በኬኒያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሆኖ ለጨረሰው ናይሮቢ ዩናይትድ በእግር ኳስ ህይወቱ አስራ ሦስተኛ ክለቡ አድርጎ ሊቀላቀል ከስምምነት መድረሱን ያገኘሁት መረጃ ይጠቁማል።
የተጫዋቹን ማምራትም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፊፋ በፀናበት ቅጣት የተነሳ በቀጣዩ አመት በሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂ ለመጫወት መገደዱም የማይቀር መስሏል።
አስተያየት ይስጡ