ከሀያ አመታት በላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ቆይታ የነበረው አማካዩ መስዑድ መሐመድ ጫማውን ሰቅሏል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ መነሻ ክለቡ ሲሆን በመቀጠል ግን በኢትዮጵያ ቡና ፣ ጅማ አባጅፋር ፣ ሰበታ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ እና ያለፉትን ሁለት አመታት ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ማድረግ ችሏል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መለያ ደግሞ ከታዳጊ እስከ ዋናው ድረስ በመሰለፍ መጫወት የቻለው የመሐል ሜዳው አመለሸጋ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች መስዑድ መሐመድ ከሀያ አመታት በላይ ከቆየበት እግር ኳስ የፊታችን ዕሮብ ድሬዳዋ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ጫማውን በይፋ ይሰቅላል ተጫዋቹም ረጅም ጊዜ መጫወቱን ገልፆ በእግር ኳስ ህይወቱ አስተዋጽኦ ያደረጉለትን ሁሉ በማመስገን ከእግር ኳስ አለም መገለሉን ከሀትሪክ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ይፋ አድርጓል።
“ለማቆም ረጅም ጊዜን ሳስብ ነበር ረጅም ጊዜ ተጫወትኩ አሁን ግን በቂ ነው። ከእግር ኳስ ስትለይ ስሜቱ ከባድ ነው። ከልጅነትህ ጀምሮ የምታውቀው ብቸኛው ነገር ነው የእግር ኳሱም ፍቅር ነው እንደዚህ ረጅም ጊዜ የሚያቆይህ ከቆየህበት ነገር ደግሞ ስትለይ በጣም ስሜታዊ ያደርጋል ግን ደግሞ አንድ ቀን እንደማይቀር ታውቀዋለህ። ከልጅነቴ ከሰፈር ጀምሮ መንገድ ያሳዩኝ አሰልጣኝ ማርቆስ እና መርሻ ሚደቅሳ ረጅም ጊዜን ለመጫወቴ የእነርሱ ሚና በቀላል የምትገልጸው አይደለም። ከልጅነት ጀምሮ ራስህን እየጠበክ ስትቆይ ሳታስበው ነው ረጅም ጊዜ የምትጫወተው ድካሞች ሳይኖሩ ስለ ሪከቨሪ ምንም ግንዛቤ ሳይኖረኝ ልምምድ ሰርቶ ማረፍ የሚባለውን ከልጅነት አሰልጣኞቼ ነው።”
“በክለብ ደረጃ ኤልያስ ጁሀርን ማግኘቴ እሱም በደንብ አግዞኛል በመብራት ሐይል አሰልጣኝ ጉልላት ፍርዴ ሳያሰለጥነኝ ደግሞ በጣም ከልጅነቴ ጀምሮ እየመከረኝ በእግር ኳሱ ብቻም ሳይሆን በሌላም መንገድ የሚመክረኝ ተድላ የሚባል ሰው አለና እሱንም በጣም በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ ለህይወቴ መስመር ያስያዘኝ ሰው ነው ባለ ብዙ ልምድ ነው እግር ኳስን ያውቃል ህይወትን እንድመራ አድርጎኛል ሁሉንም አመሰግናለሁ። በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በክለብ ትልልቅ አሰልጣኞች ነጮቹን ጨምሮ እነ አስራት ሐይሌ አብርሀም መብራቱ ስዩም አባተ ፣ ሰውነት ቢሻው ፣ ትልልቅ አሰልጣኞች ናቸው ያሰለጠኑኝ እነዚህን ሁሉ አመሰግናለሁ።” ሲል የገለፀ ሲሆን የካፍ ቢ ላይሰንስ እንዳለው እና በታዳጊ ፕሮጀክት አሰልጣኝነት ወይም በክለብ ደረጃ አንድ ነገር አበረክታል ሲል ሀሳቡን ቋጭቷል።
አስተያየት ይስጡ