1.ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል በተደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ መድን ተጫዋቾች በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ውስጥ አምስት (5) ቢጫ ካርድ እና አንድ (1) የምክትል አሰልጣኝ ቢጫ ካርድ በድምሩ ስድስት ቢጫ ካርድ የሚያሰጡ ጥፋቶች ስለመፈፀማቸው ከዕለቱ የጨዋታና የውድድር አመራሮች ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 65 በፊደል ተራ ቁጥር ሀ መሠረት ቡድኑ የብር 5,000 (አምስት ሺህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡ የቅጣቱንም ገንዘብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አካዉንት ከዛሬ 19/09/2018 እስከ 25/09/2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት 7 ቀን ዉስጥ ለፌዴሬሽኑ ገቢ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ የቅጣት ገንዘቡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ባይከፍል በየቀኑ 2 (ሁለት ከመቶ) ተጨምሮ በቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል።

2.ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል በተደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በ32 ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድን ተጫዋች መለያ ቁጥሩ 3 ያሬድ ካሣዬ (መታወቂያ ቁጥር 18-500) ተቀይሮ በሚወጣበት ወቅት ከጨዋታው ሜዳው ከወጣ በኋላ ለብሶ ይጫወትበት የነበረውን መለያ በማውለቅ ንዴትና ብስጭት በተቀላቀለበት ሁኔታ በዋናው አሰልጣኝ አካባቢ ወርውሮ መሬት ላይ በመጣል ሳያነሳ ወደ ተጠባባቂዎች መቀመጫ ወንበር ላይ ሄዶ የተቀመጠ መሆኑና ተወርውሮ የተጣለውን መለያ የኢትዮጲያ መድን ቡድን አመራር ያነሳው ስለመሆኑ የዕለቱ የውድድር አመራር ሪፖርት ቀርቧል፡፡
የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴም የቀረበውን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ተጨዋቹ የቡድኑ መገለጫ የሆነውን መለያ እና ለዋናው አሰልጣኝ ክብር ባለመስጠቱ አውልቆ መወርወሩ አስነዋሪ ድርጊት የፈጸመ መሆኑን በማረጋገጥ ለፈጸመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 በፊደል ሐ ተራ ቁጥር 7 መሠረት ብር10000 (አስር ሽህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡ የቅጣቱንም ገንዘብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አካውንት ከዛሬ 19/09/2018 እስከ 25/09/2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት ባሉት 7 ቀን ዉስጥ ለፌዴሬሽኑ ገቢ እንዲደረግ ተወስኗል ፡፡ የቅጣት ገንዘቡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ባይከፍል በየቀኑ 2 (ሁለት ከመቶ) ተጨምሮ በቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል ፡፡
3. ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል የግማሽ ፍጻሜ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በተካሄደበት ወቅት ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን አርማ የያዙና መለያ የለበሱ ደጋፊዎች ካታንጋ አካባቢ የነበሩ 20 ( ሃያ) መቀመጫዎች በመሰባበር ከቦታቸው ተነቅለው የተጣሉ በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 5 ምዕራፍ 2 አንቀፅ 20 ተራ ቁጥር 14 መሠረት ቡድኑ (ክለቡ) እንዲተካ እና እንዲያሰራ ተወስኗል፡፡ ለመተካት እና ለማሰራት እንዲቻል ባለንብረቱ በሚያቀርበው ግምት መሰረት እንዲከፍልም ተወስኗል።
አስተያየት ይስጡ