* እስከ መጨረሻዉ ሳምንት ለሊጉ ክብር ሲፎካከሩ የነበሩት አፄዎቹ አመቱን በሁለተኝነት አጠናቀዋል!!
* በመጨረሻም አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል !!
የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የዉድድር አመት በዛሬዉ ዕለት ፈረሰኞቹን ሻምፒዮን አድርጎ እንዲሁም ሰበታ ከተማን ፣ ጅማ አባጅፋር እና አዲስአበባ ከተማን ወደ ታችኛዉ ሊግ ሸኝቶ ፍፃሜውን አግኝቷል።

አስቀድሞ በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን በክረምቱ የተጫዋቾች የዝዉዉር መስኮት ወደ ስብሰባቸው በመቀላቀል ወደ ቀደመ ሀያልነታቸዉ ለመመለስ ወጥነዉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አመቱን በሰርቪያዊዉ አሰልጣኝ ጀመረዉ የነበረ ቢሆንም ከሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በስተቀር ከአሰልጣኙ ጋር መቀጠል ሳይችሉ የቀሩት ፈረሰኞቹ ምክትል አሰልጣኙን ዘሪሁን ሸንገታ በዋና አሰልጣኝነት መድበዉ አመቱን በድንቅ ብቃት አሳልፈዉ በዛሬዉ ዕለት ሰኔ 24/2014 ዓ.ም በባህርዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከአዲስአበባ ከተማ ጋር ያደረጉትን የመጨረሻ ጨዋታ በኢስማኢል ኦሮ አጎሮ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ሁለት ሁለት ጎሎች በድምሩ 4ለ0 በሆነ ሰፊ ዉጤት አዲስአበባ ከተማን በማሸነፍ ሊጉ እንደ አዲስ ከተዋቀረ ጀምሮ 15ኛ ዋንጫቸዉን ከፍ አድርገዉ መሳም ችለዋል።
በሌላኛው የሊጉ መርሐግብር ደግሞ አፄዎቹ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በድሬዳዋ ከተማ ተሸንፈዉ አመቱን በሁለተኝነት ደረጃ ሲያጠናቅቁ በአንፃሩ በዕለቱ ድል የቀናዉ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከመዉረድ ስጋቱ ተላቆ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል።
አስቀድሞ ጨዋታቸዉን በድል አጠናቀዉ የፈረሰኞቹን መሸነፍ ወይም አቻ መዉጣት ይጠብቁ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች እስከ 76ኛዉ ደቂቃ ድረስ በበረከት ደስታ እና በዛብህ መለዮ ግቦች ተጋጣሚያቸውን ሲመሩ የነበረ ቢሆንም ከ77ኛዉ ደቂቃ በኋላ ግን በተከታታይ በተቆጠሩባቸዉ ሶስት ግቦች በድሬዳዋ ከተማ ተሸንፈዉ አመቱን በሁለተኝነት አጠናቀዋል። በተቃራኒው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ጠንካራውን ፋሲል ከነማ አሸንፎ በአመቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል።

ምንም እንኳን በዚህ በፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ላይ ጥያቄም ቅሬታም አለኝ የሚለዉ አዲስ አበባ ከተማ ፋሲል ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ባደረገዉ ጨዋታ ከአቅም በታች እንደተጫወተ እና በተለይ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነዉ ለዋንጫ እየተፎካከሩ የሚገኙት አፄዎቹ ላለመዉረድ እየታገለ በሚገኘዉ ድሬዳዋ ከተማ በ13 ደቂቃዎች ዉስጥ ሶስት ግቦችን ማስተናገዳቸው እንደማይዋጥላቸዉ እና አወዳዳሪዉ አካል በቶሎ ጨዋታዉን መርምሮ ዉሳኔ እንዲሰጠን ሲሉ ደብዳቤ አስገብተዋል።
በለላኛዉ የሊጉ መርሐግብር ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተደረገዉ የሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ የሰላሳኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የመዉረድ ስጋት ተጋርጦበት የነበረዉ አዳማ ከተማ በአብዲሳ ጀማል ሁለት እና ዳዋ ሁቴሳ አንድ ግብ ተጋጣሚያቸውን ሀዋሳ ከተማ 3ለ2 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ በሊጉ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል። ለሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ከሽንፈት ያልታደጓቸዉን ሁለት ግቦች ብሩክ በየነ እና አቤነዘር ኦቴ አስቆጥረዋል። ዉጤቱን ተከትሎም ሀዋሳ ከተማ አመቱን በ4ኛ ደረጃ ማጠናቀቁን አረጋግጧል።
ከወትሮዉ ለየት ባለ መልኩ ጥሩ ፉክክር የተመለከትንበት የ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች በነገዉ ዕለት ተካሂደዉ ፍፃሜውን የሚያገኝ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ