ውልደቱ እና እድገቱ ከአዲስ አበባ 114 ኪሎ ሜትር በምትርቀው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ወሊሶ ከተማ ነው ። በክለብ ደረጃ በወሊሶ ከተማ ፤ በሀምበሪቾ ዱራሜ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአዳማ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን የውድድር አመቱ ከመጀመሩ በፊትም በድጋሚ የአዲስ አበባ ከተማን ተቀላቅሎ ክለቡን በማገልገል ላይ ይገኛል ። በትምህርትም የመጀመሪያ ዲግሪ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ማግኘት ችሏል ።
በተለይም በዘንድሮው የውድድር አመት በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ድንቅ ብቃታቸውን በየጨዋታው ያለመዋዠቅ እያሳዩን ካሉ ተጫዋቾች አንዱ ነው ።
የአዲስ አበባ ከተማው የግብ ዘብ ዳንኤል ተሾመ
ምንም እንኳን ቡድኑ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ቢገኝም በግሉ በጨዋታዎች ላይ በሚያሳየው ብቃት የብዙዎች እጅ እንዲያጨበጭቡለት አስገድዷል ።
ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ-ገጽ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ስለ ዘንድሮው የውድድር አመት ብቃቱ ከምን የተነሳ እንደሆነ ያለን ነገር አለ…… በዳኞች ላይም አስተያየቱን ሰጥቷል….. ስለ ውጪ እና የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ያለንም አለ ….. ስለ በጎ አድራጎት ተግባሩም ሰፋ ባለ ሁኔታ አጫውቶናል ….. ከዳዋ ሆቴሳ ጋር የቃላት ጦርነት አድርገው ስለገቡበት ጨዋታም ያለን ነገር አለ ….. ሙሉ ቃለ ምልልሱ እንዲህ ቀርቧል
ሀትሪክ – ትውልድ እና ዕድገትክ ወደየት አካባቢ ነው ?
ዳንኤል : ተወልጄ ያደኩት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በወሊሶ ከተማ ነው ። እግርኳስንም የጀመርኩት እዛው አካባቢ ነው ።
ሀትሪክ : እግርኳስ አጀማመርክ ምን ይመስል ነበር ?
ዳንኤል : እግርኳስን የጀመርኩት ሰፈር ውሰጥ በመጫወት ነበር ከዛም ፕሮጀክት ገብቼ መጫወት ችያለሁ ። መጀመሪያ እንደውም ግብ ጠባቂም አልነበርኩም የፊት አጥቂ ላይ ነበር የምጫወተው ፕሮጀከት ላይ ማለት ነው ። ከዛን በአንድ ጨዋታ ላይ በረኛችን በቀይ ሲወጣ በቁመትም ረዘም ስለምል አሰልጣኛችን ታሪኩ ደንድር ይባላል በግብ ጠባቂነት ትጫወታለክ አለኝ በዛው ሙሉ ለመሉ ወደ ግብጠባቂነቱ ዞርኩ ማለት ነው ።
ሀትሪክ : ከፕሮጀክት ቀጥሎ ወደ ክለብ እንዴት ተቀላቀልክ ?
ዳንኤል : በወሊሶ ከነማ ታዳጊ ቡድን ላይ ከተጫወትኩ በኋላ ከዛም ወደ ዋናው ቡድን አደግኩኝ ። በመሀል ደግሞ የዩኒቨርስቲ ውጤት መቶልኝ ወደ ሀዋሳ ሄድኩኝ። ሀዋሳ ዩኒቨርስቲም 2003 ገባሁ በ2005 ተመርቄ ወጣው ።
ሀትሪክ : ምን ነበር ያጠናከው ?
ዳንኤል : የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ( Natural resource management )
ሀትሪክ : ከዛስ ?
ዳንኤል : ከዛ በኋላም ተመልሼ የወሊሶ ከነማን ተቀላቀልኩ ። 2004 ላይ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁም ክረምት ላይ ለእረፍት ወደ ቤት ስንመለሰ መቀሌ ላይ በተደረገ ውድድር ላይ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ወሊሶ ከተማን ወደ ብሄራዊ ሊግ እነዲገባ ማድረግ ችያለሁ ።
ሀትሪክ : በዩኒቨርስቲ ቆይታክም ሀዋሳ ዩኒቨርስቲን ወክለክ በዩኒቨርስቲዎች ውድድር ላይ ተሳትፈካል ?
ዳንኤል : አዎ እዛም እጫወት ነበር ። በ2003 የመጀመሪያ አመት ተማሪ ሆኜ ባህርዳር ላይ በነበረው ውድድር ተመርጬ የነበረ ቢሆንም ወቅቱ የፈተና ጊዜ በመሆኑ መሄድ አልቻልኩም ነበረ ግን ቀጥሎ በነበሩት ሁለት አመታት ላይ አምቦ እና አርባምንጭ በተረጉት ውድድሮች ላይ መሳተፍ ችያለሁ ።
ሀትሪክ : ከወሊሶ ከተማ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በድጋሚ ወደ ወሊሶ ከነማ ቀጥሎስ ?
ዳንኤል : ከወሊሶ ከተማ በኋላ ሀምበሪቾ ዱራሜን ተቀላቀልኩ ከዛም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ አዳማ ከተማ አመራሁ በመጨረሻም በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተመልሼ በመጫወት ላይ እገኛለሁ ።
ሀትሪክ : በዚህ ጉዞህ ላይ በኳሱ እንድትገፋበት የቤተሰብ ድጋፍ እንዴት ነበር ?
ዳንኤል – የደሀ ልጅ ስትሆን ብዙም ኳስ ላይ እንድታተኩር አይፈለግም ። ትምህርት ላይ ነበር እንዳተኩር የሚፈልጉት 2003 ዓ.ም ላይ ወደ ዩኒቨርስቲ ልገባ ስል እንኳን ከአንድም ሶስት ክለቦች ያናግሩኝ ነበር ግን ጫና ሲደረግብኝ ነው ወደ ዩኒቨርስቲም የሄድኩት ። ግን 2001 አካባቢ የኦሮሚያ ሻምፕዮን ስንሆን የመሬት ሽልማት ተበርክቶልን ነበር በዛን ጊዜ ነው ትንሽ ኳሱ ጥቅም እንዳለው ሲታይ የተወሰነ ነገር እየመጣ ነበር ቢሆንም ወደ ሀዋሳ መሄዴ አልቀረም ። እንጂ የደሀ ልጅ ሆነክ ትምህርት ላይ እንትጠነክር ነው የሚፈለገው ።
ሀትሪክ : ለቤተሰብ ስንተኛ ልጅ ነክ ?
ዳንኤል : የመጀመሪያ ልጅ ነኝ ከኔ በታች ሁለት አሉ ። ኢብራሂም አብዱላሂ የሚባል ወንድሜ እንደኔው ግብ ጠባቂ ነው በወሊሶ ከተማ ነበር የሚጫወተው አሁን ዕድሜውም ትንሽ ስለሆነ በአዲስ አበባ ከተማ በተስፋ ቡድን ውስጥ በመጫወት ላይ ይገኛል ። አንድ እህትም አለችኝ በስራ ምክንያት ከሀገር ውጪ ነው የምትገኘው ።
ሀትሪክ : በአዳማ ከተማ የነበረህ ቆይታ ምን ይመስል ነበር ?
ዳንኤል : አዳማ ከተማ በጣም የምወደው ክለብ ነው ብዙ ነገር ያየሁበትም ክለብ ነው ። እዛ በነበርኩበት ጊዜ ብዙም የመሰለፍ ዕድል አልነበረኝም አምና ነው የተሻለ የመሰለፍ ዕድልም ያገኘሁት ። ያው ሁለት የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎች ነበሩ ሮበርት እና ጃኮብም ነበር ። ግን ቀድሜም እንዳልኩህ በጣም ጥሩ ጊዜ ያሳለፍኩበት እና የምወደው ክለብ ነው ።
ሀትሪክ : ከአዳማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ያመራህበት መንገድስ ምን ይመስል ነበር ?
ዳንኤል : ወደ አዲስ አበባ የገባሁበት መንገድ ልክ ከአዳማ ከተማ እንደተለያየው አስታውሳለሁ እንውም በዚሁ በሀትሪክ ገፅ ላይ የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ ከክለቡ ጋር ተለያየ የሚል ዜና እነደተሰራ ወድያውኑ የአዲስ አበባ ከተማ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ መሰረት ደውሎልኝ እንደሚፈልገኝ እና ወዴትም እንዳላመራ ነገረኝ በዛው አዲስ አባበ ከተማን ተቀላቀልኩ ።
ሀትሪክ : እስኪ ወደ ዘንድሮው የውድድር ዓመት እንምጣና የአዲስ አበባ ከተማ የ2014 የሊጉ የ25 ሳምንታት ቆይታ በዳንኤል እንዴት ይገለፃል ?
ዳንኤል : የዘንድሮ ቆይታችን ገባ ወጣ ያለ ነገር ነው ። ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በሲቲ ካፕ ወራጅ ተብሎ የተደመደመ ክለብ ነበር ። ሳምንት እንኳን ልምምድ ሳንሰራ ነበር ወደ ውድድር የገባነው ግን ከዛ በኋላ ወደ ሀዋሳ ስንሄድ ጥሩ ነበርን ከአንዳንድ ትላልቅ ክለቦችም ነጥብ መውሰድ ችለን ነበር ። ወደ ድሬደዋ ከሄድን በኋላ ውጤት እየተበላሸብን መጣ ወደ አዳማም ባህርዳርም ስንመጣም እንዳየከው እየመራን በመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ እየተቆጠረብን ነጥቦችን እየጣልን ነው ። ከዛ ውጪ ጥሩ የሚጫወት ቡድን ነው በህብረት የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው ። ሁሉም ገና ወጣቶች እና ክህሎት ያላቸው ናቸው ግን ምን አይነት ተዓምራዊ ነገር እንዳለብን አላውቅም እየመራን ቆይተን ውጤት እያጣን እየወጣን ነው ።
ሀትሪክ : የአሰልጣኞች ለውጥ ቡድኑ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ እንዴት ይገለፃል ?
ዳንኤል : ያው በዚህ ላይ ብዙም የምለው ነገር የለኝም ግን ሁሉም ቀደም ብለው የነበሩትም የአቅማቸውን ሲሰሩ ነበር አሁንም ያለው የአሰልጣኞች ስታፍም ቡድኑን ወደ ውጤት ለመመለስ የአቅሙን በአግባቡ እየሰራ ያለበት ሁኔታ ያለው ።
ሀትሪክ : ይህ በመጨረሻ ሰዓት ላይ ግብ ማስተናገድ የቡድናቹ መለያ እየመሰለ መቷል ። ምንድነው መንስኤው ይህንን ለመቅረፍ በተለይም ልምምዶች ላይ ምን ያህል ትኩረት ሰጥታችሁ እየሰራችሁበት ነው ?
ዳንኤል : ልምምድ ላይ አሰልጣኝ ደምሰውም እያለ ባለቀ ሰዓትላይ ግቦች እንዳይቆጠሩበን ምን ማድረግ አለብን በሚለው ላይ የ እንስራበት ነበር አሁን አሰልጣኝ ጳውሎስ ከመጣ በኋላም በመከላከሉ ላይ ለብቻም አድርጎ እያሰራን ነው ። በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ይህን ነገር እንቀርፈዋለን ብዬ አስባለሁ ።
ሀትሪክ – ሊጉ አምሰት ጨዋታ እየቀረው 14ኛ ደረጃ ላይ ትገኛላቹ ቡድኑን ለማትረፍ ያለው ተነሳሽነት የቡድን መንፈስ ምን ይመስላል ?
ዳንኤል – እንደ ተጫዋች ሁሉም ሀሳቡ እና ግቡ የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን እየጣረ ነው የሚገኘው አሰልጣኞቹም የየራሳቸውን እየጣሩ ነው ። እንደሚታወቀው ያሁኑ አሰልጣኝ ጳውሎስም ልምድ ያለው አሰልጣኝ ነው በሱ ታግዘንም ክለቡን በሊጉ እንደምናቆየው እርግጠኛ ነኝ ። እዚህ ጋር ምንም ጥያቄ የሌለው ነገር በተጫዋቾች መሀልም ያለው ህብረት በጣም ጥሩ ነው በአንድ ቦታ ላይ ሰባት ስምንት ሆነው ነው የምታገኛቸው ። ወደ እረፍት ከማምራታችን በፊትም ቁጭ ብለን አውርተናል ተጫዋቾች እና አሰልጣኞችም ጋር ብቻ ሳይሆን ኃላፊዎቹም ጋር ይህ ነገር አለ እነሱም የራሳቸውን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛሉ ።
ሀትሪክ : አዲስ አበባ ከተማን በውድድር ዓመቱ በአንድ ጨዋታ ላይ በአሰልጣኝነት የመምራት አጋጣሚን አግኝተህ ነበር እስኪ ስለዛ አጋጣሚ አስታውሰን ?
ዳንኤል – እሱ ከባድ ጊዜ ነበር ያው በዛን ወቀት እኔ ጉዳት ላይ ነበርኩ በአጋጣሚም አሰልጣኞችም ቴክኒክ ዳይሬክተሩም በሙሉ በኮቪድ ተያዙ ከዛን እኔ ይዤ ገባሁ ቡድኑን ። አሰልጣኝነት በጣም ከባድ ነው ። የዛኔ አንድ ጨዋታ ብቻ ስለነበር ያን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል ። አመቱን ሙሉ ግን ቡድኑን በአሰልጣኝነት ይዤ ቢሆን ብዬ ሳስበው በጣም ይከብዳል ። ቡድንክ ውሰጥ 25 አልያም 30 ተጫዋቾችን ነው የምትይዘው በዛ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ሁሉንም ማስደሰት አትቸልም ። አስራአንድ ተጫዋች ነው የምታሰልፈው ጥሩም ሆኖ ሳይሆንም ብታሰልፈው እንደ አሰልጣኝ እየተወደድክ ነው የምትሄደው በተቃራኒው ደግሞ ተጠባባቂ ላይ ብታስቀምጥ ተጫዋች ያኮርፋል ። ስለዚህ አሰልጣኝነት ሁሉንም ማስደሰት የማትችልበት ቦታ ነው ።
ሀትሪክ – ዳንኤልን ጓንቱን ከሰቀለ በኋላ በአሰልጣኝነት የመመልከት ዕድላችን ምን ያህል ነው ?
ዳንኤል – በአሰልጣኝነት ? አይመሰለኝም የዛኔም ከጨዋታ በኋላ ለሱፐርስፖርት በሰጡሁት ቃለ ምልልስ ገልጬዋለሁ እንዳላስበው ነው የሆንኩት ብዬ ። በግል ባህሪዬ ዝም ያለኩ ሰው ነኝ ሰው ሁሉ በኔ ይደሰት ብዬ ነው የማስበው ። እዚጋር ደግሞ አሰላለፍ ስታወጣ ጥሩም ሆነ አልሆነ ያላሰለፍከው ተጫዋች ቅር ይሰኝብካል ። ስለዚህ ወደ አሰልጣኝነት የማመራ አይመስለኝም ።
ሀትሪክ – ስለ ዘንድሮው ምርጥ ብቃትህ ምን ማለት ይቻላል ?
ዳንኤል – አምናም በአዳማ ከተማ በጥሩ ብቃት እያሳለፍኩ ነበር ትንሽ ጉዳት አጋጠመኝ እንጂ ። እኔ አንድ የማምንበነት ነገር አለ አንድ ተጫዋች ተደጋጋሚ ዕድል ሲሰጠው የተሳሳተውን ስህተት ነገ ለማረም እየተዘጋጀ ነው የሚሄደው አንድ እሱ ነው እናም ደግሞ አሰልጣኝ መሰረት ይህን ብታደርግ እንዲ ብትሰራ ይህን ብታስተካከል እያለ በጣም ነው የሚያግዘኝ የሚያሰራኝም ልምምዶች ጥሩ ብቃት ላይ እንድገኝ አድርገውኛል ። ደግሞም እንዳልኩህ ተደጋጋሚ ዕድል ስታገኝ ጥሩ እየሆንክ ነው የምትሄደው ያያ ነገር ነው ዘንድሮ እያሳየሁ ላለሁት ብቃት ያበቃኝ ።
ሀትሪክ – በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ስብስብ ላይ በሊጉ ላይ ባሳዩት ወቅታዊ ብቃት የተመረጡ ግብ ጠባቂዎች አሉ ። በዚህ ስብስብ ውሰጥ መካተት ነበረብኝ ትላለክ ?
ዳንኤል – ባለፈው የወዳጅነት ጨዋታም ተመርጬ ሄጄ ነበር ። በክለብ ላይ ስትጫወት የምታስበው ነገር አለ በዚህ አመት ለብሄራዊ ቡድን ብጫወት ብለክ ታስባለክ እኔ በግሌ 100% እመርጣለሁ ብዬ ጠብቄ ነበር ። ግን እዛ ቦታ ላይ መወሰን የሚችለው አሰልጣኙ ነው ። ሁሉም አሰልጣኝ የየራሱ አጨዋወት የየራሱ መንገድ አለው በመጨረሻም ውሳኔው የሱ ነው ። ብመረጥ በጣም ደስ ይለኝ ነበር ግን በቀጣይ ብዙ ጊዜ ከፊቴ አለ ከእግዚአብሔር ጋር አሁን ካለሁበትም የተሻለ ሆኜ የብሄራዊ ቡድኑን ማልያ እለብሳለሁ ብዬ አስባለሁ ።
ሀትሪክ – የወደፊት ዕቅድክ ምን ይመስላል ?
ዳንኤል – በመጀመሪያ ደረጃ ስተጫወት በቡድንክ ጥሩ ሆነው መገኘትን ታስባለክ ከዛ ብሄራዊ ቡድንክን መወከል በሶስተኛ ደግሞ ወተክ መጫወት ያንን አቅዳለሁ አሁን ደግሞ ሊጋችንም በዲኤስቲቪ ስለሚተላለፍ ዕድል ይኖራል ብዬ አስባለሁ ። በቀጣይ አምትም ቢሆን ብቃቴን ከፍ አድርጌ በመታየት እና ዕድሎችንም ለማግኘት እጥራለሁ ።
ሀትሪክ : በውድድር አመቱ በጣም ተደስተክ የወጣህበት ጨዋታ የትኛው ነው ?
ዳንኤል : በግሌ ጥሩ አመት እያሳለፍኩ ነው ምንም እንኳን ቡድንክ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆኖ እንዲህ ማለት ቢከብድም ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረኩ የወጣውባቸው ጨዋታዎች ብዙ ናቸው ። ከምንም በላይ ግን ቡድንክ አሸንፎ እንደመውጣት የሚያስደስት የለም ቡድኔ ሲያሸንፍ ሁሌም ደስተኛ ነኝ ።
ሀትሪክ : ለየት ባለ ሁኔታ የምታስታውሰው ጨዋታ አለ ?
ዳንኤል : ለየት ባለ ሁኔታ ሀዋሳ እያለን ከአዳማ ከተማ ጋር ያደረግነው ጨዋታ ነበር ። እንደምታውቀው የልምምድ ቦታዎች በፕሮግራም ነው የምንሰራው እና አንዱ ሲወጣ አንዱ ሲገባ ትገናኛለህ ። በዛ ሰአት ከጨዋታ በፊት ከዳዋ ሆቴሳ ጋር አገባብሀለሁ አታገባበኝም የምትለው ነገር አለ አይደል ያን ተባብለን ነበር የገባነው ካስታወስክ ጨዋታውም በኔ እና በሱ መሀል ይመስል ነበር በጨዋታውም ኮከብ ተብዬ ተመርጬ ነበር እና የተሻለ ሆንክ ስተገኝ በጣም ደስ የሚል ስሜት አለው ።
ሀትሪክ : አርአያዬ ወይም አያየሁ ነው ያደኩት የምትለው ግብጠባቂ አለ ? ከሀገር ውስጥም ከውጪም ሊሆን ይችላል ?
ዳንኤል : ከሀገር ውሰጥ በአሁን ሰአት የሰበታ ከተማ ወጌሻ ቢንያም በወቅቱ የሰበታ ከተማ ግብ ጠባቂ ነበር ቅርብም ስለነበር እሱ በሚጫወት ሰአት እኔ ኳስ አቀብል ነበር ። እኛ ጋር የወሊሶ ሜዳ ላይ የዞን ምናምን ውድሮች ሲኖሩም አየው ነበር ። በጣም በጣም ጎበዝ ግብ ጠባቂ ነበር እስከ ብሄራዊ ቡድን ድረስም የሄደ ነበር ።
ሀትሪክ : ከውጪስ ?
ዳንኤል : ከውጪ ቡፎን
ሀትሪክ : የማን ደጋፊ ነክ ከውጪ ?
ዳንኤል : የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ
ሀትሪክ : የወቅቱ የአለማችን ምርጡ ግብ ጠባቂ ማነው ላንተ ?
ዳንኤል : ለኔ የሊቨርፑሉ አሊሰን ቤከር ምርጡ ግብጠባቂ ነው እሱ ሁለት ለግብ የሚሆን ኳስ አቀብሏል እኔም አንድ ኳስ አመቻችቼ አቀብያለሁ ( ሳቅ… ) ። ኤደርሰንም ጥሩ ግብ ጠባቂ ነው በእግሩም ሲጫወት በጣም ጎበዝ ነው ግን ለኔ አሊሰን ቤከር የተሻለ ግብ ጠባቂ ነው ።
ሀትሪክ : ከእግርኳሱ ወጣ እንበል እና ሰሞኑን ብዙ ሲነሳ የነበረ ነገር አለ ካንተ ጋር ተያይዞ ከበጎ አድራጎት ጋር በተያያዘ እስኪ ምን አነሳሳክ ይህን ለማድረግ ?
ዳንኤል : እኔ እንደ አጋጣሚ ይህንን ፖስት አደረኩት እንጂ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባላጋራም ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ እገኛለሁ ። የማስተምራቸው አንድ ሶስት ልጆች አሉ ዩኒፎርም ደብተር ሌሎችም የተጓደለ ነገሮች የሟሟላላቸው በሌላ ጊዜም እንዲህ ቤተሰብ አልባ ከሆኑ ልጆች ጋር አብሮ የመብላት ሆቴልም ይዣቸው እየሄድኩ አብሬያቸው የመመገብ ነገር አለ ። ግን አሁን እዚህ ባህርዳር በመጣሁበት አጋጣሚ ወደ ማታ አካባቢ ነበር ሀይቅ ሄደን ስንመለስ ከነዚህ ልጆች አንድ ልጅ ታሞ ካርድ ለማውጣት ብር የለንም ብለው የተወሰነ ገንዘብ ሰጥቻቸው እሱን ወደ ሆስፒታል ከወሰድን በኋላ ጠዋት እመጣለሁ ብያቸው ሄድኩ ። ጠዋት ስመለስም መድኃኒት ታዞለት ነበር መድኃኒቱን እዛው ሆስፒታል የሚሰሩ አዋተው ገዝተውለት ነበር ከዛ ሰብስቤያቸው እዛ አካባቢ ምግብ ቤት ነበር እዛ ሄደን ከነሱጋር ምግብ በልተን አብረን ጊዜ አሳልፈን ከዛም ሄጄ እንደምጠይቀው ተነጋግረን ነበር ፖስት ከተደረገ በኋላም አግኝቻቸወ ነበር ። አሁን እነሱ የሚፈልጉት ክረምትም እየደረሰ ስለሆነ ሸራ ምናምን ነገር ክረምቱን ለመቋቋም ይፈልጋሉ ። ግን ያው እኔ ኖሮኝ ምናምን ሳይሆን እዛጋር ለአንድ ሰው የሆነ ነገር ብታደርግ ውስጥህ የሚሰማው ደስታ አለ። እናም ለሸራው እና ሌሎች ለጠየቁኝ ነገር ምንም ችግር የለውም ብያቸዋለሁ እሱን አደርግላቸዋለሁ ። ሴት ልጆችም አሉ እዛው ጋር እና የጀበና ቡና አይነት ነገር እንዲጀምሩ እና የሚያስፈልገውን ላሟላላቸው ነበር ነገር ግን ቦታው ለዛ እንደማይቻል ነው የነገሩኝ ግን ሌላ ሀሳብ ያመጡት እንደዚህ ማስቲካ ሶፍት ነገሮችን እያዞሩ ለመሸጥ ባመቻችላቸው ደስ አስደሚላቸው ነገሩኝ እኔም ችግር የለውም አሟላለው ብያቸዋለሁ ። እዚህ እስካለው የተወሰነ ሰው ባስጀምር ቀስ በቀስ ሌሎቹም እየጀመሩ ጥሩ አየሆኑ ይሄዳሉ ። እናም እስኪ ከፈጣሪ ጋር በከተማው ያለን ቆይታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለነሱ የምችለውን ሁሉ አረጋለሁ ።
ሀትሪክ : በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ ከመጫወቻ ሜዳ ፤ ከልምምድ ሜዳ ከዳኞች አንፃር አንተ ምን ትላለክ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ?
ዳንኤል : የሜዳ ችግር የሀገራችን ችግር ነው ። በሀገራችን ብዙ ምርጥ የምትላቸው ሜዳዎች ላታገኝ ትችላለክ ለስፖርቱ በሚሰጠው ትኩረት ማለት ነው ። ዘንድሮ በጣም የተሻለ ነው ብዬ ነው የማስበው ትንሽ ብትቸገር የልምምድ ሜዳ ነው እንጂ በመጫወቻ ሜዳ ድሬዳዋ ምርጥ ነበር አዳማም ምርጥ ነበር ሀዋሳ ትንሽ የመጫወቻ ሜዳው እንጂ የልምምድ ሜዳው ጥሩ ነው ። ባህርዳር ስትመጣ ደግሞ ኢንተርናሽናል ጨዋታ አይደረግበትም ሲባል ትገረማለህ ። ለምን ? እዚህ ሁሉንም ነገር ያሟላ ነው ። የልምምድ ሜዳ ብትል የመጫወቻ ሜዳ ብትል ልዩ ነው ሁሉ ነገር የተሟላለት ነው ። ሊጉ እየተሻሻለ እየሄደ ነው በቀጥታ እየተላለፈ ነው በቀጣይ ብዙ ነገሮች ይስተካከላሉ ብዬ አስባለሁ ። ስለ ዳኞች ስመጣልህ እግርኳስ ላይ ስህተት ከሌለ ጎል የለም ይህ የታወቀ ነገር ነው ። ወይ ግብ ጠባቂ ተሳስቶ ጎል ይኖራል ወይ ተከላካይ ተሳስቶ ጎል ይኖራል ወይ ደሞ ዳኛም ተሳስቶ እንዲሁ ግብ ይቆጠራል ። በዳኛዎች በኩል ስህተት ይኖራል ? አዎ ይኖራል ። ሰው ሆኖ የማይሳሳት አይኖርም እንግዲህ አሁን እኔ በዳኞች በኩል ሳስብ ሆን ብሎ ውጤት ለመቀየር የሚገባ ዳኛ ያለ አይመስለኝም ሰው በመሆናቸው ይሳሳታሉ ። ከዛ ውጪ አሪፍ ነው ብዬ ነው የማስበው ።
ሀትሪክ : ስለዚህ የዳኞቹን ሁኔታ ጥሩ ነው ብልን መውሰድ እንችላለን ባንተ ዕይታ ?
ዳንኤል : አዎ ። ዳኞች ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር አይሳሳቱም እኔ እንደዛ ነው ማስበው ዲኤስቲቪም ላይ ስታይ እኮ ሆን ብሎ ይሳሳታል የምትለው ዳኛ የለም ። እንደውም እኮ ሌላ ሀገር ላይ ስንት ቴክኖሎጂ ኖሮም እየተሳሳቱ ነው ያሉት ። እኔ ለኛ ሀገር ዳኞች ክብርም ትልቅ ቦታም አለኝ ።
ሀትሪክ : ሌላስ የታዘብከው ነገር ?
ዳንኤል : ሌላው ደስ የሚለው ነገር የየትኛውም ክለብ ደጋፊ አሁን ባለው ሁኔታ ደስ ይላል ። በተለይ ደግሞ ውድድሩ አዳማ ከተማ ላይ በነበረበት ጊዜ በርካታ ደጋፊ ይመጣ ነበር ። በባህርዳርም የፋሲል እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ የነበረውን ድባብ ስታይ ሊጉ አንድ ደረጃ ከፍ እንዳለ ትመለከታለህ ። አሁን እዚህ አካባቢ በርካታ የባህርዳር ከተማ የፋሲል ከነማ የቅዱስ ጊዮርጊስም የሌሎችም ደጋፊዎች አሉ ። በተለይ ያን ሁላ ኪሎ ሜትር አቆራርጠው ከአዲስ አበባም ይሁን ከሌላም ከተማ እዚህ ድረስ ሲመጡ ስትመለከት የደጋፊው ለኳስ ያለው ፍቅር ያስገርምካል ለዚህ ደጋፊ ደግሞ የሚገባውን የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማሳየት የኛ ሀላፊነት ነው ። በአጠቃላይ በጨዋታዎች ላይ ረጅም ርቀቶችን ተጉዘው ክለቦቻቸውን ለመደገፍ ለሚጓዙ ተጓዥ ደጋፊዎች ትልቅ ክብር አለኝ ። ሊጉንም የሚያደምቁት እነሱ ናቸው ። ክለባቸውን በመደገፋቸው ክለባቸውን ከማበረታታት ባለፈ ሊጉንም እያሳደጉት ነው የሚገኙት ።
ሀትሪክ : እንዴት ነው ታድያ ይህ ነገር በርካታ ደጋፊዎች ያሉትን ክለብ ተቀላቅሎ ለመጫወት ጉጉት አልፈጠረብክም ?
ዳንኤል : አዎ አይቀርም እሱማ እስኪ ከእግዚአብሔር ጋር ወደፊት የምናየው ይሆናል ።
ሀትሪክ : ከግብ ጠባቂዎች ጋር በተያያዘ በተለይ በዘንድሮው ዓመት በርካታ የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎችን በአሰላለፍ ውሰጥ እየተመለከትን ነው የውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን አስቀምጠው አሰየተሰለፉም ያሉ አሉ እና ይህ ነገር ከምን የመጣ ነው ማለት ይቻላል እንዴትስ መቀጠል አለበት ?
ዳንኤል : አንድ ነገር ላንሳልክ በብሄራዊ ቡድን ላይ የሚነሳ ነገር አለ በግብ ጠባቂዎች ስህትት በግብ ጠባቂዎች ስህተት ይባላል ። ግብ ጠባቂው በክለብ ላይ የመሰለፍ ዕድል ሳያገኝ ቀርቶ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ተመርጦ ሄዶ በቀጥታ ሲሰለፍ እንዴት ነው ሊሳሳት የማይችለው ? ይሄ ምንም ጥያቄ አይኖረውም በክለብ ሳትጫወት ብሄራዊ ቡድን ስትጫወት መሳሳት የማይቀር ነገር ነው ። ለዚህ መፍትሔው ቅድም እንዳልኩህ ተደጋጋሚ የጨዋታ ዕድል ማግኘት ነው ከጨዋታ ጨዋታ ስህተቶችክን እያረምክ የመሄድ ዕድል ይኖርካል ብሄራዊ ቡድን ላይ ስቴድም ብዙም አትቸገርም ። አሁን ለምሳሌ ሙሉጌታ ምህረት ዘርዓይ ሙሉንም ብታይ የውጪዎቹን አስቀምጠው የሀገር ውሰጥ ግብ ጠባቂዎችን እየተጠቀሙ ነው ። ሀዋሳ ከተማ ላይ እያየን ነው ዳግም ተፈራ መሀመድ ሙንታሪን አስቀምጦ በጥሩ ብቃት እየተጫወተ እንደሆነ ። በፊት ላይ ያለው ነገር ምንድነው ያ ግብ ጠባቂ አምስት ቢጫ አይቶ ቢያፍና አንተ ተሰለፈክ ጥሩ ብቃት ብታሳይ እንኳን በቀጣዩ ጨዋታ ላይ እሱ ነው የሚሰለፈው ። ምንም ጥሩ ሆነህ ብትሰራም እሱ አይደል እንዴ የሚሰለፈው ማለትክ አይቀርም ። አፌን ሞልቼ ይውጡ ባልልም የጨዋታ ገደብ ቢኖር እላለሁ ። ወልቂጤ ከተማ ላይ ካየክ ሰይድ እና ሮበርትን እያቀያያረ ነው የሚጠቀመው እንደዚህ አይነት ነገርም ሁሉም ጋር ቢለመድ ጥሩ ነው አቅምህን አውጥተክ እንድትጫወት ያደርግካል ። ስለዚህ አሰልጣኞች ደፈር ብለው የሀገር ውሰጥ ግብ ጠባቂዎችን ቢጠቀሙ እላለሁ ጥቅሙ ለሀገርም ስለሆነ ።
ሀትሪክ : ከእግር ኳስ ውጪ ያለ ጊዜክን በምንድነው የምታሳልፈው ?
ዳንኤል : ከልምምድ በኋላ ብዙም በቀን መተኛት አልወድም ሆቴል አካባቢ ከጓደኞች ጋር ምናምን ቁጭ ብለክ ታወራለክ ። ቡና እየጠጣክ እንዲሁ በወሬ መሀል እንዲህ የተጎዳ ሰው እርዳታ የሚፈልግ ሰው ምናምን የሚል ወሬ ይኖራል እዛ ሄደክ ለመጎብኘች ትጥራለክ ። በነገራችን ላይ እኔ እንደ በጎ አድራጎት ሳይሆን ህሊናዬ የፈቀደውን ነገር ነው የባለፈውን ካዩ በኋላ እንኳን ብዙ ሰው ደውሎልኛል ። እንደዚህ አይነት ቦታ ሰው አለ እንዲህ ብናደርግ ሄድን ብንጎበኝ እንዲህ ቦታ ምስኪን እናት አሉ ሲባል እኔ አልችልም ። ለምን ? ለእናቴ የምሆንላትን አውቃለሁ እዛጋር የአንድ ሰው እናት ሲባል የኔስ እናት ብትሆን ብዬ ነው የማስበው ብዙ ነገር ባላደርግም እዛ ቦታ እሄዳለሁ ብዙ ጊዜ ሄደህ አይዟችሁ ስትል እንኳን በጣም ደስ ይላቸዋል እነሱም አንትም ትልቅ የህሊና እርካታ ይሰማካል ። ብዙ ጊዜ ከሰው ጋር ቶሎ እግባባለሁ እና በሄድኩባቸው አካባቢዎችም እንደዚህ አይነት ነገሮችን አደርጋለሁ ።
ሀትሪክ : ለወደፊት የያዝከው ዕቅድ አለ ከዚህ ጋር በተያያዘ ?
ዳንኤል : ወደ ፊት እግዚአብሔር ከፈቀደ ቤተሰብ አልባ የሆኑ ልጆችን የማስተማር የመደገፍ ተግባር በሰፊው መስራት እፈልጋለሁ ። አሁን ላይ ባሉበት ሆነው የምደግፋቸው ልጆች አሉ ወደ ፊት ግን ልጆቹን በአንድ ቦታ ሰብሰብ አድርጌ የመርዳት ትልቅ ሀሳብ አለኝ ፈጣሪም እንደሚረዳኝ እርግጠኛ ነኝ ።
ሀትሪክ : ፕሮጀክት ላይ እያለክ አንድ ቅፅል ስም እንደወጣልክ ሰምቼ ነበር ?
ዳንኤል : አዎ ቡስኬ ነው የሚሉኝ ። ብዙም ከፍ ያለ ባይሆንም እዛው ወሊሶ ከተማ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ ምግብ ቤት ነገር ነበረን እና ብስኩት ሳምቡሳ አይነት ነገሮች አሉ ልጅ እያለሁ ለጓደኞቼ ይዤላቸው እሄድ ነበረ ። እና በዚህ ነው የሰፈር ልጆች ያወጡልን ስሙን ።
ሀትሪክ : በመጨረሻም ማመስገን የምትፈልገው አካል ካለ ዕድሉን ልስጥክ ?
ዳንኤል : አንድ በአንድ ከጠራው በጣም ብዙ ሊሆን ነው ። እኔ እዚህ ደረጃ ለመድረሴ ብዙ ሰዎች ደግፈውኛል ቤተሰቦቼ ፤ አሰልጣኞቼ ፤ ጓደኞቼ ፤ የቡድን አጋሮቼ በአጠቃላይ ለኔ እዚህ መድረስ አስተዋጽኦ ላበረከቱልኝ በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ ፈጣሪ ያክብርልኝ ።
ሀትሪክ : በጣም አመሰግናለሁ
ዳንኤል : እኔም አመሰግናለሁ
አስተያየት ይስጡ