በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ ቀዳሚ ጨዋታ በሀድያ ሆሳዕና እና በሲዳማ ቡና መካከል ተደርጎ ሲዳማ ቡናዎች ከእረፍት መልስ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ማሸነፍ ችለዋል ።
በ14ኛው ሳምንት በወላይታ ድቻ የተሸነፉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት አሰላለፍ ላይ ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በሄኖክ አርፊጮ እና ሚካኤል ጆርጅ ምትክ ፍሬዘር ካሳን እና ዑመድ ዑክሪን ያሰለፉ ሲሆን በሳምንቱ አዲስ አበባ ከተማን የረቱት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በጨዋታው ከነበረው ምርጥ 11 በተመሳሳይ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ ወደ ጨዋታው የገቡ ሲሆን ጊት ጋትኩት እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ተስፋዬ በቀለን እና ብሩክ ሙሉጌታን ተክተዋል ።
የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ የበዛበት ሲሆን ሁለቱም ኳሱን ይዘው በመሀል ላይ ብልጫውን ለመውሰድ ጥረቶችን አድርገው ነበር ። በተለይም ግን ሲዳማ ቡናዎች በተወሰኑ አጋጣሚወች ይገዙ ቦጋለን ኢላማ ያደረጉ ኳሶች በረጅም ሲያደርሱ የነበረ ቢሆንም በመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ከመባል አላመለጡም ።
በጨዋታው 11ኛ ደቂቃ ላይ በያኩቡ መሀመድ እግራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው የጨዋታው ዋና ዳኛ አዳነ ወርቁ ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻላቸው አቋርጠው የወጡ ሲሆን በምትካቸው አራተኛ ዳኛ የነበሩት ተከተል ተሾመ ጨዋታውን መምራት ችለዋል ።
15ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከቀኝ አቅጣጫ ወደ ግብ የመታው ኳስ በተክለማርያም ሻንቆ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከሙሉአለም መስመፍን በረጅም የደረሰውን ኳስ የግብ ጠባቂውንም መውጣቶ ተመልክቶ ወደ ግብ በከፍታ የመታው ኳስ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
36ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው የመጀመሪያ ግብ የተቆጠረ ሲሆን ካጥኑ ውጪ በቀኝ አቅጣጫ ላየሰ ባዬ ገዛኸኝ ከዑመድ ዑክሪ የተቀበለውን ኳሽ በግሬ እግሩ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ሀድያ ሆሳዕናነሰ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል ። ከግቡ መቆጠር ሶስት ደቂቃዎች በኋላ ዳዊት ተፈራ ከርቀት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው የቅጣት ምት በመሳይ አያኖ ተመልሶ የማዕዘን ምት የሆነ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽም በሀድያ ሆሳዕና መሪነት ተጠናቋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ በሶሰት ደቂቃዎች ውስጥ ሲዳማ ቡናዎች አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ አግኝተዋል ። ይገዙ ቦጋለ ከመሀል ሜዳ የነጠቀውን ኳስ የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾችን አልፎ ሳጥን ውሰጥ በመግባት ግብ ጠባቂው ለማለፍ ሲሞክር በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት ወደ አንድ እኩል ቀይሮታል ።
ከግቡ በኋላ ሀድያ ሆሳዕናዎች ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለማለፍ ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረው ነበር ። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ የሚገኙ ኳሶችን በፈጣን መልሶ ማጥቃት እና ወደ ፊት በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
58ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ሌላ ግብ ለማከል ተቃርቦ የነበረ ሲሆን ከርቀት የግብ ጠባቂው የመሳይ አያኖን መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል ። 67ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከቀኝ አቅጣጫ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ የሙሉጌታ ምህረት ተጫዋቾች በአጋማሹ ያደረጉት የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ነበር ።
በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ በተደጋጋሚ ሲጥሩ የቆዩት የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ተጫዋቾች 80ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ሀብታሙ ገዛኸኝ ዳዊት ተፈራ ያቀበለውን ኳስ በፍጥነት ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ከመሳይ አያኖ መረብ ላይ ያሳረፈ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ታላቅ ወንድሙ ባዬ ገዛኸኝም ለሀድያ ሆሳዕና ግብ ማስቆጠሩ አስገራሚ አድርጎታል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ኳሱን ይዘው በመጫወት ጨዋታውን በማቀዝቀዝ መሉ ሶሰት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 25 በማድረስ ከወላይታ ድቻ የአራተኝነት ደረጃውን የተረከበ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ በ17 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ16ኛ ሳምንት ( አዳማ ከተማ ) ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ፋሲል ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ