ከሁለት ሳምንታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከዩጋንዳ አቻቸዉ ጋር ላለባቸው የደርሶመልሰ ጨዋታ ዝግጅታቸዉን በካፍ የልህቀት ማዕከል እያደረጉ የሚገኙት ሉሲዎቹ ነገ ረፋድ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ታዉቋል።

በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛዉ እየተመሩ ከሳምንት በፊት አያት አካባቢ በሚገኘዉ የካፍ የልህቀት ማዕከል ልምምዳቸዉን በመስራት ላይ የሚገኙት ሉሲዎቹ ከዋናዉ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አስቀድሞ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን የዝግጅታቸዉ አንድ አካል የሆነዉ የአቋም መፈተሻ ጨዋታም ከኢትዮጵያ 15 አመት በታች ታዳጊ ወጣቶች ጋር በነገዉ ዕለት ረፋድ 3:00 የሚያደርጉ ይሆናል።

ከጨዋታው አስቀድሞ ዛሬ አመሻሽ አስራ አንድ ሰዓት ላይ ሀያ ሰባት ተጫዋቾችን የያዘዉ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ስብስብ ለአንድ ሰዓት ከአስር ገደማ በዘለቀዉ ልምምድም ከኳስ ጋር ቀለል ያሉ ንክኪዎችን የሰሩ ሲሆን ወደ በኋላ ላይ ደግሞ አሰልጣኙ ቡድኑን ለሁለት በመክፈል የተለያዩ የጨዋታ መንገዶችን ለተጫዋቾች ሲያሰሩ ተመልክተናል።

ሉሲዎቹ ልምምዳቸዉን አጠናክረው ቀጥለዉ በወርሀ ጥቅምት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታቸዉን ወደ ዩጋንዳ አምርተዉ የሚያደርጉ ሲሆን ከሳምንት በኋላ ደግሞ የመልሱን ጨዋታ በባህርዳር አለምአቀፍ ስታዲየም ላይ የሚያደርጉ ይሆናል።

አስተያየት ይስጡ