በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አዘጋጅነት በባቱ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተዉ ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ውድድር በ16 የክልል እና የኘሪሚየር ሊግ ክለቦች (በአዳማ ከተማ፣በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማ ፣ በጋምቤላ ክልል፣ በወልቂጤ ከተማ፣ በኢትዮጵያ ቡና፣ በባሕር ዳር ከተማ፣ በደቡብ ክልል፣ በሲዳማ ክልል፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ፣ በሶማሌ ክልል፣ በወላይታ ድቻ ፣ በሐዋሳ ከተማ፣ በድሬደዋ ከተማ ፣ በሀረሪ ክልል እና በአርባ ምንጭ ከተማ) መካከል በአራት ምድብ ተደልድሎ ከነሐሴ 16/2013 ጀምሮ ለአስራ ሰባት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ጳጉሜ 2/ 2013 በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ፍፃሜውን አጊኝቷል።
የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሸን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ አበበ አሽኔ፣ የባቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ አደም ኡመር ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክ አቶ ሲያምረኝ፣ የሼር ኢትዮጵያ የሰው ሃይል አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አቶ ገመቹ ባቱ፣ የሼር ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ የዝና አያሌው እና የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የትምህርት ሥልጠናና ውድድር ቡድን መሪ በባቱ ከተማ የተፈጥሮ ሳር በተሸፈነው የሼር ኢትዮጵያ ሜዳ በመገኘት ጨዋታውን የተከታተሉ ሲሆን ለውድድሩ የተዘጋጁትን ሸልማቶች ለተሸላሚዎች አበርክተዋል።
በማጠቃያ ውድድሩ ለፍፃሜ የደረሱት የአዳማ ከተማ እና የአርባ ምንጭ ከተማ የዋንጫ ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ አቻ በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቶ አርባ ምንጭ ከተማ ሁለት ግቦችን በማስቆጠሩ 2 ለ0 በሆነ ውጤት አርባምንጭ ከተማ አዳማ ከተማን በማሸነፍ ሻምፒዮና በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ እና የውድድሩን አሸናፊ ዋንጫ ተሸላሚ መሆኑን በማረጋገጡ ተጋጣሚው አዳማ ከተማ 2ኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳልያ ተሸላሚ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ቡና እና ሐዋሳ ከተማ ባደረጉት የደረጃ ጨዋታ የሐዋሳ ከተማ 18 ቁጥሩ አማኑኤል ሞገስ ከእረፍት በፊት ባስቆጠራቸው 2 ግቦች ሐዋሳ ከተማ 2ለ0 በሆነ ውጤት ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ የ3ኛ ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን ችሏል።

በውድድሩም ለኮከብ ተጨዋችና አሰልጣኞች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚህም
ኮከብ ተጫዋች – ሰይፈዲን ረሻድ
ከአዳማ ክለብ ፣ ኮከብ ጎል አስቀሰጣሪ- ሙሉቀን በቀለ
ከአዲስ አበባ ፣ ኮከብ አሠልጣኝ – አሠልጣኝ አዱኛ ገላነህ ከአርባ ምንጭ ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ – ሠራዊት ሳያ- ከአርባ ምንጭ ፣ ኮከብ ተከላካይ- አመንቲ አበት ከኦሮሚያ ፣ ኮከብ የመሀል ተጫዋች- ሚኪያስ አፋይስ ከደቡብ ክልል ፣ ኮከብ አጥቂ – ዮሴፍ ታረቀኝ – ከአዳማ ከተማ
በመሆን ተሸልመዋል።


በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩት 16 ክለቦች 50 የሚሆኑ የተሻለ አቅምና ክህሎት ያላቸው ተተኪ ታዳጊዎች ለዚህ ውድድር የተዋቀረው የቴክኒክ ኮሚቴ ከውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በጋራ መርጠዋል። ከተመረጡት 10 የግብ ጠባቂዎች ሲሆኑ አርባዎቹ በተለያዩ ፖዚሽን የሚጫወቱ ናቸው።
በተጨማሪም ውድድሩ በርካታ ክለቦች ለቀጣይ የውድድር ዓመት የሚፈልጓቸውን ወጣት ተጫዋቾች ለመመልከትና ለመመልመል የሚችሉበትን ጥሩ እድል ለመፍጠር የቻለ ውድድር ሆኖ እንደተጠናቀቀ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየት ይስጡ