መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ዘገባ | ሰራተኞቹ ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግኢትዮ-ኤሌክትሪክወልቂጤ ከተማ

የጨዋታ ዘገባ | ሰራተኞቹ ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

አጋራ
አጋራ

በሊጉ የመጀመሪያ ሁለት መርግብሮችን ካሸነፉ በኋላ በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎች ከድል ጋር ተራርቀው የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 አሸንፈዋል ።

ወልቂጤ ከተማዎች በአምስተኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ ላይ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ጀማል ጣሰው ፤ ፍፁም ግርማ እና ጌታነህ ከበደን በሮበርት አዶንካራ ፤ ብርሀኑ ቦጋለ እና ተመስገን በጅሮንድ ተክተው ሲገቡ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በሳምንቱ ከአዳማ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ የተጠቀሙትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመዋል ።

ፈጠን ባለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ ገና ከጅምሩ ግብ ሊያስተናግድ ነበር ።

የጨዋታውን የመጀመሪያ የግብ ሙከራ በሁለተኛው ደቂቃ ለዬ ሲደረግ የኢትዮ ኤሌክትሪሱ ተከላካይ አንዳርጋቸው ይላቅ በአግባቡ ማራቅ ያቃተውን ኳስ ጌታነህ ከበደ አግኝቶ ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።

ወልቂጤ ከተማዎች የተሻሉ በነበሩበት በዚህ ጨዋታ በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ አደጋ ክልል ኳሶችን ማድረስ ችለው ነበር ።

በአንፃሩ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ቀደም ብለው ከነበሩት ጨዋታዎች መጠነኛ መቀዛቀዝ ታይቶባቸዋል ።

ወልቂጤ ከተማዎች በፋሲል አበባየሁ አማካይነት በ16ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ያደረጉት ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።

በ25ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታው የመጀመሪያውን ግብ አስተናግዷል ። ጌታነህ ከበደ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር በመግጨት ወልቂጤ ከተማን ቀዳሚ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።

ወልቂጤ ከተማዎች ከግቡ በኀላም እስከ አጋማሹ መጠናቀቂያ ድረስ ተጭነው መጫወት ችለዋል ።

በጨዋታው 39ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ሚክያስ መኮንን ጉዳት አጋጥሞት ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል ።

የመጀመሪያው አጋማሽም በወልቂጤ ከተማ የ1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ በፈጣን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሲጀመር ወልቂጤ ከተማዎች አጋማሹ በተጀመረ ሰባተኛ ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ አክለዋል ።

ከሳጥኑ አቅራቢያ በየኋላሸት ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ አስቆጥሮታል ።

ከግቡ በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተጭነው ለመጫወት ጥረቶችን አድርገዋል ። ። በተደጋጋሚም በተለይም ከማዕዝን ምቶች ዕድሎችንም ለመፍጠር ችለው ነበር ።

ወልቂጤ ከተማዎች በአንፃሩ ከኳስ ጀርባ በመሆን ጥንቃቄ ላይ ያተኮረ አጨዋወትን የተከተሉ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ያደረጓቸው ሂደቶች ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል ።

የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናው ቡድን በተለይም በግራ መስመር በኩል በፀጋ ደርቤ አማካኝነት የወልቂጤ ከተማን የኋላ ክፍል ሰብረው ለመግባት ጥረቶችን አድርገዋል ።

ያለ ጠንካራ የግብ ሙከራ እስከ መጨረሻው ደቂቄ በተጓዘው ጨዋታ በ90ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ነጋሽ ከአድናን ፈይሰል የደረሰውን አስደናቂ ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።

የጨዋታው መጠናቀቅ ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቀት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን በቀጥታ ወደ ግብ የተመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ያገኘው ታፈሰ ሰርካ በግንባር በመግጨት ከመረብ አሳርፏል ።

በመጨረሻም ወልቂጤ ከተማ ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥቦችን ይዞ መውጣት ችሏል ።

በሰባተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ህዳር 1(ሐሙስ) 10:00 ላይ ወልቂጤ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ህዳር 2(አርብ) በተመሳሳይ ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ መድኅን ይገጥማል ።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች