በሀያ ስድስተኛዉ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ወልቂጤ ከተማን ማሸነፍ ችሏል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በጀመረዉ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የጀመሩ ሲሆን ገና በመባቻዉም ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። በዚህም ግብ ጠባቂዉ ፋሪስ አለዊ ቻርልስ ሙሰጌ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን የፍፁም ቅጣት ምት ሱራፌል ጌታቸው ወደ ግብነት ቀይሯል።
በዚህ ሁኔታ በጀመረዉ ጨዋታ በ14ተኛዉ ደቂቃ ላይም አማካዩ ሱራፌል ጌታቸዉ ያመቻቸለትን ኳስ ካርሎስ ዳምጠዉ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል። ገና በጊዜ ሁለት ጎሎችን ያስተናገዱት ክትፎዎቹ ከግማሽ ሰዓት በኋላ በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይ በተመስገን በጅሮንድ አማካኝነት ከቅጣት ምት ሙከራ ማድረግ ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከዚች ሙከራ በተጨማሪም በ45+ ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በዳንኤል ደምሱ አማካኝነት ከርቀት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂዉ አብዩ ካሳየ ተቆጣጥሮባቸዋል። ከዕረፍት መልስ በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በቀጠለዉ ጨዋታ በ62ተኛዉ ደቂቃ ላይ ኳስ በዕጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠዉ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሶስት ለዜሮ ከፍ አድርጓል። በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴን ቢያደርጉም ነገር ግን ግብ ሳይቆጠር ጨዋታዉን ድሬዳዋ ከተማ 3ለ0 አሸንፏል።
በዝናብ በታጀበዉ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ተከታታይ ስድስተኛ ድሉን አሳክቷል !!
በተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክር አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ ምንም እንኳን በአጋማሹ በሜዳ ላይ እንቅሰቃሴ ጥሩ ፉክክር ቢደረግም ነገር ግን በሙከራ ረገድ በተቃራኒው ተቀዛቅዞ ተመልክተናል። በአብዝሀኛዉ የአጋማሹ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድም ተጠቃሽ ሙከራ ስንመለከት ከዘለቅን በኋላ በመጠናቀቂያዉ ላይ የአዳማ ከተማዉ ዮሴፍ ታረቀኝ ከቅጣት ምት ድንቅ ሙከራ አድርጎ አቡበከር ኑራ እንደምንም ኳሷን አውጥቷት ክለቦቹ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ተጋግሎ በዝናብ ታጅቦ በቀጠለዉ ጨዋታ በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ሞሐመድ ከቀኝ መስመር በኩል ከሚሊዮን ሰለሞን በተቀበለዉ ኳስ ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ግን ወደ ዉጭ ወጥታለች። ከዚች ሙከራ በኋላ በ63ተኛዉ ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ ላይ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ የተሰጠዉ ቅጣት ምት አምበሉ ሀይደር ሸረፋ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በመሐል የስታዲየሙ መብራት ጠፍቶ ጨዋታዉ ተቋርጦ ከቀጠለ በኋላ በ74ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቻርልስ ሪቫኑ ድንቅ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂዉ አቡበከር ኑራ ሲያወጣበት በ75ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን መድኖች ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል።በዚህም በተጠቀሰዉ ደቂቃ ከቀኝ መስመር በኩል አብዱልከሪም መሐመድ ያቀበለዉን ኳስ አለን ከይዋ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር ጫና ፈጥረዉ መጫት የቀጠሉት መድኖች በ77ተኛዉ ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል ከአቡበከር ሳኒ በተቀበለዉ ኳስ ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በ80ኛዉ ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ታረቀኝ የመታዉን የቅጣት ምት ኳስ ጀሚል ያዕቆብ ወደ ግብነት በመቀየር ወደ ጨዋታዉ ቢመልስም በ86ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን አቡበከር ሳኒ ከማዕዘን የተሻገረን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ኢትዮጵያ መድንን 4ለ1 እንዲያሸንፉ አስችሏል።