በሀያ ስድስተኛዉ ሳምንት ሁለተኛ ዕለት ጨዋታ መቻል እና ሻሸመኔ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።
ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በተጀመረዉ እና የመቻልን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ባስመለከተን የጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በተቃራኒው በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ሻሸመኔ ከተማዎች ምንም እንኳን ወደ ኋላ አፈግፍገዉ በአብዝሀኛዉ መከላከል ላይ ያዘነበለ የጨዋታ መንገድ ይከተሉ እንጅ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሶስተኛዉ የሜዳ ክፍል አልፎ አልፎ በመድረስ ረገድ ግን የሚታሙ አልነበሩም።
በዚህ ሁነት በጀመረዉ ጨዋታ ብልጫ የነበራቸዉ መቻሎች ከቀኝ መስመር በኩል ግርማ ዲሳሳ አሻምቶት ከንዓን ማርክነህ በግንባሩ በገጨዉ ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩ ቢሆንም ፤ ነገር ግን በ30ኛዉ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በዚህም አማካዩ ሙልጌታ ወልደየስ ያቀበለዉን ኳስ የፊት መስመር ተጫዋቹ አብዱልቃድር ናስር በሚገርም ብቃት ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን ሻሸመኔ ከተማ መሪ ማድረግ ችሏል።
ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ ተጋግሎ በቀጠለዉ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዉ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ሻሸመኔ ከተማዎች ሁለተኛ ግብ በአማካዩ ሙልጌታ ወ/ጊዮርጊስ አማካኝነት አስቆጥረዉ መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ቢያደርጉም ፤ በ45+1 ላይ ግን መቻሎች በሳሙኤል ሳሊሶ አማካኝነት ያሻሙትን ኳስ ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት አለመቻላቸዉን ተከትሎ በረከት ደስታ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቦቹ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ጨዋታዉ በተመሳሳይ ቴምፖ ቀጥሎ ሻሸመኔ ከተማዎች በሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ እና ማይክል ኔልሰን አማካኝነት ተከታታይ ሙከራን ማድረግ ቢችሉም በ57ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን የአቻነት ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር በኩል የመጣለትን ኳስ አማካዩ ሽመልስ በቀለ ለአጥቂዉ ምንይሉ ወንድሙ ወደ ኋላ አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ አድርጓል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጫና ፈጥረዉ መጫወት የቀጠሉት መቻሎች በከንዓን ማርክነህ እና አጥቂዉ ምንይሉ አማካኝነት ድንቅ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ በመጨረሻዉ ደቂቃ ግብ ቢያስቆጥሩም ግብ ጠባቂዉ ላይ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ ግቡ ተሽሮ ጨዋታዉ ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት ተገባዷል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ከወላይታ ዲቻ ጋር መርሐግብራቸዉን ያለ ግብ በአቻ ዉጤት ፈፅመዋል ።
በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅ አገኘሁ ፊሽካ የምሽት 12:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ባህርዳር ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ብልጫ በመዉሰድ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ በተቃራኒው ተጋጣሚያቸዉ የጦና ንቦቹ ወላይታ ዲቻዎች ደግሞ ገና ከጅምሩ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት አልፎ አልፎ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት ኳሶች አደጋዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
በዚህ የታክቲክ ሂደት ጅማሮዉን ባደረገዉ ጨዋታ ላይም በ18ተኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራ ተደርጓል። በዚህም ከቀኝ መስመር በኩል የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ ፍራኦል መንግስቱ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ አግዳሚዉ የመለሰበት አጋጣሚ በባህርዳሮች በኩል የተደረገ አስቆጪ ሙከራ ነበር ፤ በአጋማሹም የጦና ንቦቹ የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቡድኖቹ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስም ቡድኖቹ እንደ መጀመሪያዉ አጋማሽ ሁሉ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ቀጥለዉ የጠሩ የግብ ሙከራዎችን ለመመልከት ሳንችል ቀርተናል ፤ ጨዋታዉ ሊጠናቀቅ አስር ያህል ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅት ግን ባህርዳር ከተማዎች በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ጥሩ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ነገር ግን የገብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ቅልጥፍና ኳስ ተቆጣጥሯታል። አጠቃላይ በጨዋታዉ ቀሪ ደቂቃዎች ግብ ሳንመለከት መርሐግብሩ ያለ ግብ 0ለ0 ተጠናቋል።