በስድስተኛው ሳምንት ሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ዲቻ መቻልን 1ለ0 በሆነ ዉጤት አሸንፏል።
በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ፉክክርን በተመለከትንበት ጨዋታ ቀዳሚዉን ሙከራ በማድረግ ረገድ መቻሎች ቀዳሚ ነበሩ። በዚህም በ15ኛዉ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ግርማ ዲሳሳ ከአማካዩ ፍፁም አለሙ የተቀበለውን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ኳሷን ተቆጣጥሮታል።
በድጋሚ በ23ኛዉ ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ያሻማዉን የማዕዘን ኳስ አማካዩ ከንዓን ማርክነህ በጭንቅላቱ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
የመጀመሪያ ሙከራቸዉን ለማድረግ 28ኛ ያህል ደቂቃዎች የፈጁባቸዉ ዲቻዎች በዚሁ ደቂቃም የመስመር አጥቂዉ ያሬድ ከአማካዩ ቢኒያም የተቀበለውን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ የሞከረ ቢሆንም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ በግቡ አናት ላይ ወጥታለች።
ነገር ግን በ30ኛዉ ደቂቃ ላይ የመከላከያ ተከላካዮች ሳጥን ዉስጥ ንጋቱ ገ/ስላሴ ላይ ጥፋት መስራታቸውን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ቃልኪዳን ዘላለም ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ቻለ።
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ መቻሎች በመልሶ ማጥቃት በ41ኛዉ ደቂቃ ላይ የመስመር ተጫዋቹ በረከት ደስታ ከግርማ ዲሳሳ የተቀበለዉን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክርም ኢላማዉን ሳይጠብቅ ወደ ዉጭ ወጥቷል።
ከዕረፍት መልስ ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ የተመለሱት መቻሎች ተደጋጋሚ መኩራዎችን ማድረግ ችለዋል ከነዚህ መካከልም በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ ከሳጥን ዉጭ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ የወጣችበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ስትሆን።
በተጨማሪም በ72ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ከቀኝ መስመር ተጫዋቹ ግርማ ዲሳሳ የተቀበለዉን ኳስ በረከት ደስታ ለተስፋ አለባቸዉ አቀብሎት አማካዩ ቀጥታ ወደ ግብ የሞከራት ኳስም በመቻሎች በኩል አስቆጭ ነበረች።
ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቀጠሉት መቻሎች በ88ኛዉ ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በድጋሚ ከርቀት ጥሩ ኳስ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥቷል። በዚህ ሂደቴ በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በጨዋታው መገባደጃ ወቅት ግብ ጠባቂዉ ቢኒያም በ2ተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዶ ጨዋታዉ በወላይታ ዲቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።