” ሁለቱ ጨዋታዎች ትርጉም ባይኖራቸውም
ብሄራዊ ቡድኑ ግን ይቀጥላል”
ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ ማሪያም
/የዋሊያዎቹ ጊዜያዊ አሰልጣኝ/
“የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለብሄራዊ ቡድኑ የሚጠበቅበትን በማድረጉ ከዋሊያዎቹ ውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ ሃላፊነቱን የሚወስደው መልቀቂያ ያቀረበው ወገን ነው” ሲል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን እንደተናገሩት “ፌዴሬሽኑ የሚጠበቅበትን አድርጓል ጥሩ ስታዲየም አስፈላጊ አቅርቦትና የሚፈለገውን በጀት በማቅረቡ ሀላፊነቱን ተወጥቷል ከዋሊያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ መሆን ጋር ተያይዞ ሃላፊነቱን የሚወስደው መልቀቂያ ያቀረበው ወገን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ስለ አሰልጣኞቹ የቅጥር ሂደት የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው “አሰልጣኛቹን የሾምነው በጊዜያዊነት ነው ከማላዊ ፣ በአሜሪካ ጉዞ ላይ ለሚኖረው ጨዋታና ከግብጽ ብሄራዊ ቡድን ግን እስካለው ጨዋታ ድረስ ይመራሉ የደመወዝ ክፍያ የለውም በፌዴሬሽኑ የሚፈጸምላቸው ክፍያዎች ግን ይኖራሉ ከቋሚ አዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ጋር ተያይዞ በቀጥይ አዲስ አሰልጣኝ የመሾም እቅድ ይዘን እየሰራን ነው ለአሁኑ ግን አንቸኩልም…” ሲሉ ገልጸዋል።
- ማሰታውቂያ -
ስለ ሞዛምቢክ ስታዲየም መስተንግዶ ምርጫ የተጠየቁት አቶ ባህሩ ጥላሁን ” ሱዳንን ብናይ በውስጥ ጉዳይዋ በመታመሷ ታንዛኒያም ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ቢኖርም ሜዳው ተደጋጋሚ ውድድር በማስተናገዱ እየተጎዳ በመሆኑ ተከለከልን በመጨረሻም የሞዛቢክ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ከፌዴሬሽናችን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጋር ባላቸው አግባብ ተፈቅዶልን ቀድሞ የተጠየቅነው 12 ሺህ ብር ቅናሽ ተደርጎልን 8 ሺህ ብር እንድንከፍል ተስማምተናል አሁንም ቡድኑ ከሀገር ውጪ በመጫወቱ ዋጋ እየከፈለ ያለው ፌዴሬሽኑ ነው ባለሜዳ በመሆናችን ሌሎች ወጪዎችም ከፌዴሬሽኑ ካዝና የሚወጣ ነው” ሲሉ አብራርተዋል። አቶ ባህሩ “ከተጨዋቾች ምርጫ ጋር ተያይዞ ለብሄራዊ ቡድን አልጫወትም ማለት በዲሲፕሊን መመሪያው መሰረት ቅጣት ይኖረዋል.. ነገር ግን የዝግጁነት ጥያቄ የተነሳበት እንጂ አልመጣም ያለ ተጨዋች እስካሁን አልገጠመንም” በማለት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከማላዊና ከግብጽ አቻቸው ጋር ለመርሀግብር ማሟያ የማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርጉት የዋሊያዎቹ ስብስብ ከ41 ተጨዋቾች 23ቱን በመያዝ ጠንካራ ልምምድ መስራታቸውን አሰልጣኙ ተናገሩ።
ጊዜያዊው የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ዳንኤል ገ/ማሪያም በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በመገኘት በሰጡት መግለጫ “ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ለማካተት ሞክረናል…ጌታነህ ከበደ ዝግጁ አለመሆኑን አቡበከር ናስር በጉዳት ዳዋ ሁቴሳም ከጉዳቱ እንዲያገግም እንዲያርፍ በማሰብ ሳይካተቱ ቀርተዋል ከ41 ተጨዋቾች 23ቱን መርጠን ጠንካራ ዝግጅት አድርገን ለማላዊ ጨዋታ ተዘጋጅተናል” ሲሉ ገልጸዋል።
” ከአሰልጣኝነቴ ውጪ የቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆኔ ታዳጊዎች ሀገራቸውን ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ በማሰብ ወጣቶቹን ጠርተናቸዋል ለመጀመሪያ ጊዜም የተጠሩ ለነገ ተስፋ የሚጣልባቸው ተጨዋቾችን መርጠን አካተን ልምድ ካላቸው ጋር አዋህደን ለማላዊ ጨዋታ ተዘጋጅተናል” ሲሉ አሰልጣኝ ዳንኤል ተናግረዋል።
ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ዙሪያ የተጠየቁት አሰልጣኙ “ትላንት ለነበረው የወዳጅነት ጨዋታ ቀድመን የፈለግነው ወላይታ ድቻን ቢሆንም እረፍት በመሆናቸው ከአርባ ምንጭ ጋር ልንጫወት ችለናል ጨዋታው ደግሞ አቋም መመልከቻ ቡድን ማዋቀሪያ እንጂ የውጤት አይደለም” ሲሉ መልሰዋል።
” ከኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ በመሆናችን ጨዋታዎቹ ትርጉም ላይኖራቸው ይችላል ብሄራዊ ቡድኑ ግን ይቀጥላል ” ያሉት አሰልጣኝ ዳንኤል ገ/ ማሪያም
” የመርሃግብር ማሟያ የሆነና ትርጉም የሌለው ጨዋታን መምራት ቢከብድም በዚህ መሰሉ ጨዋታ ላይ እድል አግኝቶ ቡድን መምራትም ጥንካሬነው” ሲሉ መልሰዋል።
ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ የሆኑት ዋሊያዎቹ ሞዛምፒክ መዲና ማፑቶ ላይ የፊታችን ማክሰኞ የማላዊ ብሄራዊ ቡድንን ያስተናግዳሉ።