” ለሀገር ዉስጥ በረኞች ትኩረት ለሚሰጡ አሰልጣኞች ትልቅ ክብር አለኝ”
” ከዚህ በፊትም በበርካታ በክለባችን አባላት እንደሚባለዉ ወራጅ ወንዝ እንጂ ወራጅ ክለብ የለንም”
” ወደፊት የበረኞች ፕሮጀክት የመክፈት እቅድ አለኝ”
” በተከፋሁባቸዉ ግዜያት ልጄን ሳገኛት ሁሉን እረሳለሁ” መክብብ ደገፉ /የሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ/
- ማሰታውቂያ -
ትዉልድ እድገቱን በዱራሜ ከተማ አድርጎ እግር ኳስን በፕሮጀክት ታቅፎ በመጫወት ጀምሮ ከዱራሜ ፕሮጀክት አንስቶ እስከ ሀገራችን ትልቁ የዉድድር እርከን እስከ ሆነዉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድረስ መጫወት ከቻለዉ እና በርካታ ክለቦች ላይ በግብ ጠባቂነት ካገለገለዉ እንዲሁም በአሁን ግዜ በሲዳማ ቡና ከሚገኘዉ መክብብ ደገፉ ጋር ሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚከተለዉን ቃለ መጠየቅ አድርጋለች።
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ ራስህን ለሀትሪክ ቤተሰቦች አስተዋውቅልን ?
መክብብ :- መክብብ ደገፉ እባላለሁ ተወልጄ ያደኩት ዱራሜ ነዉ።
ሀትሪክ :- እስኪ እግር ኳስን የጀመርክበትን አጋጣሚ አጫውተን ?
መክብብ :- እግር ኳስን የጀመርኩት የዱራሜ u15 ፕሮጀክት ላይ በመጫወት ነበር።
ሀትሪክ :- ብዙዉን ግዜ አብዛኞች ተጫዋች መሆንን እንጂ ግብ ጠባቂ መሆንን አይመርጡም እና አንተ በረኝነቱን እንዴት መረጥቅ ?
መክብብ :- በረኝነቱን የጀመርኩት በዋናነት ለበረኝነት ፍቅር ስላለኝ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ብዙ ግዜ ብዙሀን ከሚመርጡት ነገር የተለየ ነገር ማድረግ ስለሚያስደስተኝም ጭምር ነዉ ብዙሀኑ ማይመርጡትን በረኝነቱን የመረጥኩት።
ሀትሪክ :- ከዱራሜ ፕሮጀክት በኋላስ ወዴት አመራክ ?
መክብብ :- ከፕሮጀክት በኋላ ወደ ወላይታ ዲቻ ነበር ያመራሁት።
ሀትሪክ :- እስኪ ከፕሮጀክት ወደ ወላይታ ዲቻ ልታመራበት ስለቻልከዉ አጋጣሚ አጫዉተን ?
መክብብ :- የዱራሜ ፕሮጀክት ዉስጥ እየተጫወትኩ በነበረበት ወቅት የዱራሜ ከነማ ዋናዉ ቡድን ከወላይታ ዲቻ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሊያካሂድ ቀጠሮ ይዞ እያለ እንደ አጋጣሚ የዱራሜዉ በረኛ በግል ጉዳይ ምክንያት በጨዋታው ላይ ሊገኝ ስላልቻለ በወቅቱ እዛ አከባቢ ካሉ በረኞች ዉስጥ ለጨዋታው ብቁ ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ በረኛ ይምጣ በሚባልበት ወቅት ካሉ በረኞች ዉስጥ ፕሮጀክቱ ዉስጥ ያለሁት እኔ የተሻልኩ ሆኜ ተገኘሁና ለዱራሜ ከነማ ዋናዉ ቡድን ተሰልፌ ከወላይታ ዲቻ ጋር ተጫዉተን ጥሩ አቋም በማሳየቴ በወላይታ ዲቻ አሰልጣኞች አይን ዉስጥ ገብቼ በመሳይ ተፈሪ ተመርጬ ወደ ወላይታ ዲቻ ተጠባባቂ በረኛ ሆኜ ላመራ ችያለሁ።
ሀትሪክ :- እስኪ ስለ ወላይታ ዲቻ ቆይታህ አጫዉተን ?
መክብብ :- ከዱራሜ ፕሮጀክት በኋላ ወደ ወላይታ ዲቻ ካመራዉ በኋላ ለሁለት ዓመት በወላይታ ዲቻ ቤት የቆየሁ ሲሆን መጀመሪያ ላይ የክለቡ አራተኛ በረኛ ነበርኩ በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ የነበረዉ መሳይ ተፈሪ በሜዳ ዉስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ብቻ የሚያምን አሰልጣኝ ነበርና ሳሳይ በነበረዉ አቅም የክለቡ ሶስተኛ ፣ ሁለተኛ እያልኩ አንደኛ በረኛ ልሆን የቻልኩ ሲሆን በሁለተኛዉ አመቴ ወላይታ ዲቻ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ባደገበት በ2005 ዓ/ም ላይ በ21 ጨዋታ 1 ጎል ብቻ ገብቶብኝ የዉድድር አመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂም ሆኜ ያጠናቀኩበት እና ጥሩ የዉድድር ዘመን ያሳለፍኩበት ክለብ ነዉ።
ሀትሪክ :- ከወላይታ ዲቻ በኋላስ ወዴት ክለቦች አመራክ ?
መክብብ :- ከወላይታ ዲቻ በኋላ 2007 ላይ ወደ ሀዋሳ ከነማ ያመራዉ ሲሆን ከአንድ አመት ተኩል በኋላ ወደ አዳማ ከነማ አመራሁ ከአዳማ ቆይታ በኋላ ወደ ሀምበሪቾ ዱራሜ ያመራሁ ሲሆን ከእሱ በመቀጠል ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያድግ ደቡብ ፖሊስን የተቀላቀልኩ ሲሆን ከእዛ በኋላ ዳግም ወደ ወላይታ ዲቻ ቤት ተመልሻለሁ።
ሀትሪክ :- እስኪ በአጠቃላይ የሀዋሳ ፣ የአዳማ ፣ የሀምበሪቾ ፣ የደቡብ ፖሊስ እንዲሁም የወላይታ ዲቻ ቆይታህ ምን ይመስል ነበር ?
መክብብ :- እንደ አጠቃላይ በሀዋሳ ፣ በአዳማ ፣ ጥሩ ግዜ አሳልፌያለሁ ብዬ አላምንም ለእዛም እንደገና ወደታች ተመልሼ እራሴን ብቁ አድርጌ እና አዘጋጅቼ ልመለስ ብዬ ዳግም ለመስራት ብዬ ወደታችኛዉ ሊግ በመዉረድ የቡድኑ አምበልም ጭምር በመሆን ለሀምበሪቾ የተጫወትኩ ሲሆን ከእዛ በኋላ እራሴን ፈትሼ ከመጀመሪያው የተሻለዉን መክብብን በመያዝ ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪሚየር ባደገበት አመት እኔም ከደቡብ ፖሊስ ጋር ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ድጋሚ የተመለስኩ ሲሆን በደቡብ ፖሊስ ጥሩ የሚባል ግዜን በማሳለፍ ድጋሚ ወደ ቀድሞ ቤቴ ወላይታ ዲቻ በመመለስ የተጫወትኩ ሲሆን በወላይታ ዲቻ ቤትም ጥሩ የሚባል ጊዜን ማሳለፍ ችያለሁ ብዬ አምናለሁ።
ሀትሪክ :- ከወላይታ ዲቻ በኋላስ ወዴት አመራክ ?
መክብብ :- ከወላይታ ዲቻ በኋላ አሁን ወደምገኝበት ወደ ሲዳማ ቡና ነዉ የመጣሁት።
ሀትሪክ :- እስኪ በሲዳማ ቡና ቤት እያሳለፍከዉ ስለምትገኘዉ ቆይታ አጫዉተን ?
መክብብ :- በሲዳማ ቡና እያሳለፍኩ በምገኘዉ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነኝ። አምና ሶስተኛ የወጣን ሲሆን የዘንድሮዉን የዉድድር ዘመን ስንጀምር ሻምፒዮን ለመሆን ወይም ሁለተኛ ሆነን ለማጠናቀቅ አቅደን የዉድድር ዘመኑን የጀመርን ቢሆንም በኳስ ላይ አንዳንዴ ከታሰበዉ በተቃራኒ ይሆናልና በጥሩ አቋም ያልጀመርን ቢሆንም በግዜ ሂደት እየተሻሻልን አሁን ላይ ጥሩ የሚባል አቋም ላይ ነን። የዚህም ማሳያ ቡድናችን ሲዳማ ቡና በሀዋሳ ከተማ ካደረጋቸዉ 6 ጨዋታዎች ዉስጥ አራቱን በማሸነፍ ሁለቱን በአቻ ዉጤት በማጠናቀቅ የነበረዉ ደረጃ ላይ ትልቅ መሻሻልን ማድረግ ችሏል።
ሀትሪክ :- ሲዳማ ቡና የመዉረድ ስጋት አለበት ብለህ ታስባለህ ?
መክብብ :- በፍፁም !! ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሲባል እንደነበረዉ እኔም ልል የምችለዉ ወራጅ ወንዝ እንጂ ወራጅ ክለብ የለንም። የክለቡ አጠቃላይ አባላት እንዲሁም የበላይ ጠባቂዎች የቦርድ አመራሮች ፣የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አቡሽ አሰፋ እንዲሁም ደጋፊዎች ለሲዳማ ቡና ከሚችሉት በላይ እያደረጉ ነዉና ሲዳማ ቡና ከወራጅ ቀጠና ይበልጥ ርቆ አሁን ያለበትን ደረጃ ይበልጥ አሻሽሎ የተሻለ ደረጃ ይዞ የዉድድር ዘመኑን ያጠናቅቃል ብዬ አምናለሁ።
በዚህ አጋጣሚ በዉጤት ማጣት ቀዉስ ዉስጥ በምንገባት ወቅት የክለቡ የበላይ የቦርድ አመራሮች እና ስራ አስኪያጁ አቶ አቡሽ አሰፋ ሁሌም ባለንበት ሁሉ ከጎናችን እየተገኙ አይዟችሁ በርቱ ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል አሁን ካለንበት የዉጤት ማጣት ከዉስ ዉስጥ እንወጣለን እያሉ ያበረታቱናል። እንዲሁም የክለባችን ደጋፊዎች ሁሌም የጀርባ አጥንታችን ሆነዉ በዉድቀታችንም በከፍታችንም ግዜ አብረዉን ናቸዉና ምስጋናዬ ከልብ ይድረሳቸዉ።
ሀትሪክ :- በእስከዛሬዉ የእግር ኳስ ህይወት የሚያስደስት እና የሚያስከፋ ግዜን አሳልፌበታለሁ ብለህ የምታስበዉን አጋጣሚ አስታዉሰን ?
መክብብ :- በእግር ኳስ ህይወት ዉስጥ ብዙ የሚያስደስቱ እና እንዲሁም የሚያስከፉ ነገሮች ገጥመዉኝ ያዉቃሉ ከእነርሱም ዉስጥ ለእኔ ልዩ እለት ነበር ብዬ የተደሰትኩት ግዜ 2005 ዓ/ም ላይ በወላይታ ዲቻ ቤት እያለሁ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስንገባ በ21 ጨዋታ አንድ ጎል ብቻ ገብቶብኝ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብዬ የተሸለምኩበትን እለት መቼም አልረሳም እንዲሁም አሁን ባለሁበት ክለብ በሲዳማ ቡና ቤት የሶስተኝነትን ደረጃ ይዘን የዉድድር ዘመኑን ያጠናቀቅንበት እለት እጅግ በጣም አድርጌ የተደሰትኩበት ቀን ነበር።
እንዲሁም የተከፋሁበት በኳስ ህይወቴ ዉስጥ እንደዚህ ባይሆን ብዬ የምቆጭበት አጋጣሚ ቢኖር ወደ ሀዋሳ ከተማ በመጣሁበት ግዜ የሚጠበቅብኝን ማድረግ ያለብኝን ሳላደርግ መጥፎ የዉድድር ዘመንን አሳልፌ ወደ ታችኛዉ ሊግ የወረድኩበት ግዜ እጅግ በጣም አድርጎ የሚያስቆጨኝ እና ወደኋላ ተመልሼ ባስተካከልኩት የምልበት ግዜ ነዉ።
ሀትሪክ :- የዉጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን ከመጠቀም አንፃር የአንተ ምልከታ ምን ይመስላል ?
መክብብ :- ዘንድሮ እስካለሁበት ሲዳማ ቡና ድረስ ከአምስት የዉጪ ሀገር በረኞች ጋር ሰርቻለሁ። እዉነቱን ለመናገር የዉጪ ሀገር በረኞች ጋር ጥሩ ነገር አለ ነገር ግን በእዛዉ ልክ ከዉጪ ሀገር በረኞች የተሻለ ነገር ያላቸዉ የሀገር ዉስጥ በረኞችም አሉ።
ሀገራችን ዉስጥ ብዙ ግዜ ለዉጪ ሀገር በረኞች ቅድሚያ የመስጠት ነገር ይስተዋላል። እንደ እኔ በአሁኑ ወቅት በሊጋችን ዉስጥ ከሚገኙ የዉጪ ሀገር በረኞች ዉስጥ እኔን ሊያሳምኑኝ ይችላሉ የምለዉ ሁለት ክለብ ዉስጥ የሚገኙ በረኞች ብቻ ናቸዉ። ለአብነትም የሀዲያ ሆሳዕናዉን ግብ ጠባቂ ልጠቅስ እችላለሁ እንደዚህ አሳምነዉ ለእኛም ጥሩ ለመማር የሚሆኑን በረኞች ብቻ ቢመጡ ጥሩ ይመስለኛልና።
ሀትሪክ :- ለሀገር ዉስጥ በረኞች ትኩረት በመስጠት ዙሪያ እንደ አጠቃላይ መፍትሄዉ ምንድነዉ ብለህ ታምናለህ ?
መክብብ :- በመጀመሪያ ደረጃ ለሀገር ዉስጥ በረኞች ትኩረት በመስጠት እያሰለፉ ለሚገኙ አሰልጣኞች ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። በመቀጠልም ለማለት የምፈልገዉ የኢትዮጵያ በረኞች በአሁን ወቅት ከዜጎች በረኞች ያልተናነሰ አቅም አላቸዉና ትኩረት ሊሰጣቸዉ ይገባል። አንድ ከዉጪ ሀገር የመጣ ዜጋ በረኛ ዜጋ ስለሆነ ብቻ መሰለፍ የለበትም ከሀገር ዉስጥ በረኞች ጋር በችሎታ ተወዳድሮ ነዉ ሊሰለፍ የሚገባዉ። እንዲሁም የሀገር ዉስጥ በረኞች ከዉጪ ሀገር በረኞች የተሻለ አቅም እንዳላቸዉ ለማሳየት ጠንክረዉ ሊሰሩ ይገባል።
የሀገር ዉስጥ በረኞች ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን ጠንክረዉ መስራት እና መስራት ብቻ ነዉ የሚጠበቅባቸዉ።
የክለብ አሰልጣኞች አሁን ላይ ዉጤትን ስለሚፈልጉ የሀገር ዉስጥ በረኞች የተሻሉ ከሆኑ የማይመርጧቸዉ ምክንያት የለም። ለዚህም እንደ አብነት ዜጎች በረኞችን አስቀምጠዉ የሀገር ዉስጥ በረኞችን የሚጠቀሙ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ባህርዳር ፣ አዳማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም አሁን የምገኝበት ሲዳማ ቡና ተጠቃሽ ክለቦች ናቸዉ።
ሀትሪክ :- በበረኝነት ህይወትህ በጣም የሚፈትንህ የተቃራኒ ቲም ተጫዋች ማነዉ ?
መክብብ :- ብዙ ግዜ የሚፈትነኝ ተጫዋች ቢኖር ጌታነህ ከበደ ነዉ።
ሀትሪክ :- ለእግር ኳስ ህይወቴ አርአያዬ ነዉ የምትለዉ ተጫዋች ማን ነዉ ?
መክብብ :- ለእግር ኳስ ህይወቴ አርአያዬ ነዉ የምለዉ ተጫዋቾች የወላይታ ዲቻዉ ግብ ጠባቂ ዘላለም ማቲዎስ ነዉ።
ሀትሪክ :- ከሀገር ዉስጥ እና ከሀገር ዉጪ የምታደንቃቸዉ ተጫዋቾች ?
መክብብ :- ከሀገር ዉስጥ የወልቂጤ ከተማዉ አጥቂ የጌታነህ ከበደ አድናቂ ስሆን እንዲሁም ከሀገር ዉጪ የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን እና የኢንተር ሚላን ግብ ጠባቂ የሆነዉ የአንድሬ ኦናና አድናቂ ነኝ።
ሀትሪክ :- ትርፍ ጊዜህን የት ነዉ የምታሳልፈዉ ?
መክብብ :- ትርፍ ጊዜዬን በመዝናኛ ቦታዎች ቪዲዮ ጌሞችን ፣ ቴኒስ ፣ ፑል በመጫወት ነዉ የማሳልፈዉ።
ሀትሪክ :- ስለ ቤተሰብ ሁኔታ አጫዉተን ?
መክብብ :- ሀዘኔን ጭንቀቴን የምረሳባት አልፎ ተርፎ ጨዋታ ተሸንፈን ጎል ተቆጥሮብኝ እንኳን መጥፎ ስሜት በሚሰማኝ ወቅት ሳያት ፣ ሳገኛት የምደሰትባት መከፋቴን ሁሉ የምረሳባት የደስታዬ ሚስጥር የሆነች ላኪ መክብብ የምትባል የሁለት አመት ከስምንት ወር ልጅ አለችኝ።
እንዲሁም መጥፎም ሆነ ጥሩ ግዜ በማሳልፍበት ወቅት በስኬቴም በዉድቀቴም ግዜ ሁሌም ቤተሰቦቼ ከጎኔ ናቸዉ። በተለይ ወንድሞቼ እንደ ወንድም ብቻ ሳይሆኑ ለእኔ እንደ ጓደኛም ጭምር ናቸዉ።
ሀትሪክ :- የወደፊት እቅድህ ምንድነዉ ?
መክብብ :- የወደፊት እቅዴ ከፈጣሪ ጋር የማስባቸዉ ፣ የማቅዳቸዉ ከተሳኩልኝ የበረኞች ፕሮጀክት የመክፈት እና ብቁ ታዳጊ በረኞችን በማፍራት እና በማብቃት እቅድ አለኝ።
ሀትሪክ :- መክብብ ተጫዋች ባይሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር ?
መክብብ :- ረዥም ሳቅ በመሳቅ ፈገግ ካለ በኋላ ከባድ ጥያቄ ነዉ በማለት ለሰከንዶች በማሰብ “ነጋዴ እሆን ነበር” ብሏል።
ሀትሪክ :- ኤኬሮ በሚል ቅፅል ስም ስትጠራ ይደመጣልና ይሄ ቅፅል ስም እንዴት ሊወጣልህ ቻለ ? ትርጉሙስ ምን ማለት ነዉ ?
መክብብ :- ኤኬሮ የሚለዉን ስም ጓደኞቼ ያወጡልኝ ሲሆን ትርጓሜዉም ‘ደስ ሲል’ ማለት ነዉ። ይሄም ስያሜ ሊወጣልኝ የቻለበት ምክንያት ብዙ ግዜ ሌሎችን ባላስከፋ መልኩ ለየት ያለ ነገር ማድረግ ለምሳሌ ከአለባበስ ጀምሮ እስከ ፀጉር ቁርጥ ድረስ እንዲሁም በፀጉሬ ላይ በምቀባዉ ቀለም ምክንያት የወጣልኝ ስያሜ ነዉ።
ሀትሪክ :- መክብብ በተሰለፈባቸዉ ጨዋታዎች <ሰአት ያቃጥላል> የሚል ዉዝግብ ይነሳልና ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ ?
መክብብ :- ማንኛዉም ተጫዋቾች ባለበት ክለብ ዉስጥ አሸንፎ መዉጣትን ብቻ ነዉ የሚፈልገዉ። እኔም ለሲዳማ ቡና በተሰለፍኩባቸዉ ጨዋታዎች አሸንፎ የመዉጣት ፍላጎት ስላለኝ ማድረግ ያለብኝን በሙሉ አደርጋለሁ። ከእዛ ዉጪ ሆን ብሎ ሰአት ለመግደል እንደዚህ ያደርጋል የሚባሉ ነገሮች በሙሉ ከእዉነት የራቁ እና እኔን የማይወክሉ ጭምር ናቸዉ።
ሀትሪክ :- በተቀያሪ ወንበር ላይ በምትሆንባቸዉ ግዜያት በሜዳ ዉስጥ ስህተቶች ተፈጥረዋል ተብለዉ በሚታመኑበት ግዜያት ስሜታዊ ሆነህ ከዳኞች ጋር ሰጣ ገባ ዉስጥ ስትገባ እና የካርድ ሰላባ ስትሆን እንመለከታለንና ይህ ስሜት ከምን የመነጨ ነዉ ?
መክብብ :- እኔ የምኖርባቸዉ ክለቦች ዉስጥ ተጫዋች ብቻ ሳልሆን ደጋፊም ጭምር ነኝ። ስለዚህ ኳስን በዉጪ በኩል ሆኜ ስመለከት በሜዳ ዉስጥ ያሉ የቡድን አባላቴ ላይ ስህተት ሲፈጠር መታገስ አልችልምና በእዛ ግዜ ስናገር ነዉ የካርድ ሰለባ የምሆነዉ።
ሀትሪክ :- ከመቻል ጋር ባደረጋችሁት ጨዋታ ተጎድተህ ወተህ ነበርና ነገር ግን በፍጥነት አገግመህ ወደ ሜዳ ልትመልስ የቻልክበት ሚስጥር ምን ይሆን ?
መክብብ :- በመጀመሪያ ደረጃ የምለዉ እድለኛ ነን ነዉ። ምክንያቱም ብሩክ ደበበ የተባለ እጅግ በጣም በብዙ ነገር ብቁ የሆነ እና ጎበዝ ፊዚዮቴራፒ አለን። ለሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ለሌላ ክለብ ተጫዋቾች ቶሎ ከጉዳት አገግሞ ወደ ሜዳ ለመመለሳቸዉ ምክንያት የሆነዉ ብሩክ ደበበ ነዉ።
ሀትሪክ :- ብዙ ግዜ ሌሎች በረኞች ከሚመርጡት ቁጥር የተራራቀ ቁጥር ያላቸዉን ማለያዎች ለብሰህ ነዉና ጨዋታዎችን የምትሰለፈዉ ስለዚህ ጉዳይ አስረዳን ?
መክብብ :- አዎን። ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩት የሌላዉን ምቾት እና ፍላጎት ባልተጋፋ መልኩ ለየት ያለ ነገር ማድረግ ያስደስተኛል። በእዛም ምክንያት ብዙ ግዜ በረኞች ከሚለብሱት ማለያ ቁጥር የተራራቀ 99 ቁጥር እና 50 ቁጥር ማለያዎችን ነዉ ለመልበስ የምመርጠዉ።
በፊት እንደሁም ምርጫዬ 99 ቁጥር ነበር። አሁን ላይ DSTV ከ50 ቁጥር በላይ ያላቸዉን ማለያዎች መልበስ አይቻልም በማለቱ ምክንያት ነዉ 50 ቁጥር ማለያ የምለብሰዉ።
ሀትሪክ :- በስተመጨረሻም ማመስገን የምትፈልጋቸዉ አካላት ካሉ እድሉን ልስጥህ ?
መክብብ :- በመጀመሪያ ፈጣሪን ሲሆን ከእዛ በመቀጠል በጣም በጣም እናቴን የማመሰግን ሲሆን እንዲሁም ለዚህ መብቃት እንድችል መሰረቱ የሆነኝን መሳይ ተፈሪን እና ስማቸዉን ያልጠቀስኳቸዉ ከእነርሱ ስር የእግር ኳስን ህይወት ላሳለፍኩባቸዉ አሰልጣኞችና የቡድን አባላቴ ጓደኞቼ እና ቤተሰቦቼ በሙሉ ምስጋናዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ።
ሀትሪክ :- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
መክብብ :- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ አመሰግናለሁ።