👉…. ከሃላፊነት ለመነሳት እንደማይቸኩሉ ገልጸዋል…
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ እየተካፈሉ ያሉት ዋሊያዎቹ ወደ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድላቸው መጥበቡን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተናገሩ።
አሰልጣኝ ውበቱ ከፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጳሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር በመሆን በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከጊኒ አቻቸው ጋር በነበራቸው የ180 ደቂቃ ጨዋታ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ” ከጊኒ ጋር ማሳካት የፈለግነውን ውጤት አላሳካንም የመጀመሪያው ጨዋታ ደካማ አቋም አሳይተናል ሁለተኛው በንጽጽር የተሻለ ነበር ያም ሆኖ በተገኘው ውጤት መሰረት ወደ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድላችን ጠቧል” ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል። አሰልጣኙ እንደሚሉት ” በመጀመሪያ ጨዋታ በጣም አዝኛለሁ ሁለተኛው የተሻልን ነበርን ነገር ግን ለመጀመሪያው ደካማ አቋም አሰልጣኝ እንደማያስፈልግ ለተጨዋቾቼ ነግሬአቸዋለሁ” ሲሉ መልሰዋል።
” ከመጀመሪያው የኒጀር ጨዋታ ጀምሮ ቡድኑ ጥሩ መደላደል ላይ ነበር ማለት አይቻልም በሁለቱ አመታት ውስጥ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መገኘት በራሱ ስኬት ነው እኛ እንደ አልጄሪያ ግብጽና ናይጄሪያ በየአፍሪካ ዋንጫው የምንገኝ አይደለንም እናም በሻምፒዮናው ላይ መገኘታችንን እንደ ስኬት እቆጥራለሁ ውድድሩ ላይ ገብተን ያሳየነው ድክመት ግን መሻሻል አለበት” ሲሉ ስኬታማ ነኝ ብለው ያስባሉ ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። አሰልጣኙ “ወደ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድላችን ጠቧል በቀጣይ ግብጽን ስንገጥም የምንችለውን እናደርጋለን ለወደፊትም ሽንፈት ቢገጥመን ዋናው ጉዳይ ከሽንፈት መነሳት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ቡድኑ እየተመራ ይስቁ ስለነበሩ ተጨዋቾች የተጠየቁት አሰልጣኙ ” እንኳን ተጨዋቾቼ ማንም በቡድኑ ሽንፈት አይስቅም ለምን ሳቁ የሚለው ግን መታየትና መመርመር አለበት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ስለ ስንብት አስበው ያውቃሉ ተብለው የተጠየቁት አሰልጣኙ ” ቀሪ ኮንትራት አለኝ በድንገት ተነስቼ የምወስነው ነገር የለም ከቀጣሪዎቼ ጋር መነጋገር ይኖርብኛል ምንም የሚያስቸኩል ነገር የለም” ሲሉ መልሰዋል።
በሊጉ የሚታየው እንቅስቃሴ ቡድኑ ውስጥ ስላሳረፈው ጫና የተጠየቁት አሰልጣኝ ውበቱ “ሊጉም ይቋረጣል ወጥ የሆነ እንቅሳቃሴ የሚያደርጉ ክለቦች ማነስ አይተናል የተጨዋቾች ወጥ አቋም ማየት ላይ አስቸጋሪ ሆኖብናል ሌሎች ሀገሮች ወጥ ብሄራዊ ቡድን አባላት ይኖራቸውና አንድ ሁለት ሊቀይሩ ይችላሉ እኛ ግን ሁለት አመት የሚቆዩ ወጥ ተጨዋቾች ማግኘት ተቸግረናል በአጭር ቀናት ውስጥ መጫወት ጫና አለው ሜዳ በተመለከተ አሁንም ችግር ነው በመጥፎ ሜዳ ላይ የሚጫወቱ ወደ ጥሩ ሜዳ ሲመጡ ክፍተት ይፈጠራል ይሄም አንድ ችግር ነው ከጊኒ ጋር በነበረው ጨዋታ ግን ከሜዳውና ከሊጉ ይልቅ ተጠያቂ የማደርገው የኛን ዝግጅት ነውም ” በማለት ተናግረዋል።
“ሁሉንም ሚዲያ በጋራ መፈረጅ አልፈልግም ተገቢ የሆነ ትችት የሚሰጡ የሚያርሙኝ ጋዜጠኞች አሉ
የኔንም የቤተሰቤን ክብር የሚነኩ አስተዳደጋቸውን በራሳቸው ሚዲያ የሚያሳዩ ከተቀጠርኩበት ጊዜ ጀምሮ በአላማ የሚያጠቁኝ ጋዜጠኞች አሉ የምችለውን እሸከማለሁ በዚሁ ከቀጠለ ግን አንድ ቀን ከጫንቃዬ መወርወሬ አይቀርም” ሲሉ ከሚዲያ ጋር ያለዎት ግንኙነት ምን ይመስላል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከተጨዋቾችዎ ጋር ያልዎት ግንኙነት ምን ይመስላል የተባሉት አሰልጣኝ ውበቱ “የማስገባቸው ተጨዋቾች ደስ ሊላቸው የማይገቡት ደግሞ ቅር ሊላቸው ይችላል ነገር ግን ሁሉም ለህግና ስርዓት ሊገዙ ይገባል ከዚያ ውጪ በግሌ ከማንም ጋር ችግር የለብኝም ” በማለት ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ስላለው ውል ዝርዝር የተጠየቁት የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው ” ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር መነጋገራችን አይቀርም ከአሰልጣኙ ጋር በነበረው ውል ዙሪያ የቱ ተሳካ ..? ምኑስ አልተሳካም የሚለውን የፌዴሬሽኑ የስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ አይቶ በቀጣይ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል አሁን ላይ ግን ምንም መናገር አልችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አስተያየት ይስጡ