በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ7ተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
እጅግ ጭቃማ በነበረዉ እና ለመጫወት አዳጋች በነበረዉ ሜዳ ላይ ሁለቱንም ክለቦች በረጃጅም ኳሶች ከጨዋታው እንዳች ነገርን ይዘዉ ለመዉጣት ሲጥሩ ተስተውሏል። በዚህም በጨዋታዉ ገና በ6ኛዉ ደቂቃ ላይ አብዱልባሲጥ ከማል ከቀኝ መስመር በኩል ያሻገራት ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ ስታመራ የግቅ ዘቡ ፍሊፕ ኦቮኖ ለጥቂት ተቆጣጥሯታል።
በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ኳስን ተረጋግቶ በአንድ ሁለት ቅብብል ለመጫወት ሜዳው ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት ረጃጅም ኳሶችን ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመላክ ግብ ለማግኘት ሲጥሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በተቃራኒው በራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ27ኛዉ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም ከግራ መስመር በኩል ከኤፍሬም አሻሞ የተሻገረለተን ኳስ አጥቂዉ አሊ ሱለይማን ያመከናት ኳስ በሀይቆቸቹ በኩል አስቆጭ ሙከራ ነበረች።
በ42ኛዉ ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ ፍሬዉ ሰለሞን ቀጥታ ወደ ግብ ሲል ግብ ጠባቂዉ መሐመድ ሙንታሪ እንደምንም አዉጥቷታል።
ከዕረፍት መልስ በጥቂቱም ቢሆን ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ ገብተዉ የነበሩት ሲዳማዎች በ55ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂያቸዉ ፍሊፕ ኦቮኖ ኳስን ከሳጥን ዉጭ ነክቷል በሚል በቀይ ካርድ ተወግዷል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ67ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዶበታል። በዚህም ጊት ጋት ኩት ሙጅብ ቃሲም ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘዉን ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው እዮብ አለማየሁ ወደ ግብነት ቀይሮ ሀዋሳ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ተጫዋቾች ግብ ካስቆጠረ ከደቂቃዎች በኋላም በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በ73ኛዉ ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ክፍል የተሻገረውን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ በጥሩ ቅልጥፍና ገፍቶ ወደ ሳጥን ገብቶ የሞከራት ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭታ ገባች ሲባል ተከላካዩ ደግፊ ደርሶ እንደምንም አዉጥቷታል።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በመጣ ቁጥር የድካም ስሜት እየተስተዋለባቸዉ የመጡት ሀዋሳ ከተማዎች በይበልጥ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት ዉጤታቸዉን አስጠብቀው መዉጣት ችለዋል። በዚህም በብዙ ትዕይንት የታጀበዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።