” ከሲዳማ ቡና ጋር መለያየቴን ለረዥም ግዜ አምኖ መቀበል ከብዶኝ ነበር ”
” በኢትዮጵያ ዉስጥ ለሀገር ዉስጥ በረኞች ትኩረት አይሰጥም። ኢትዮጵያ ከግብፅ ልትማር ይገባል”
” አዳነ ግርማ እንደታላቅ ወንድሜ ነዉ” መሳይ አያኖ /የሀዲያ ሆሳዕና ግብ ጠባቂ/
- ማሰታውቂያ -
ትዉልድ እድገቱን በሀላባ ከተማ አድርጎ የልጅነት እድሜዉን በእግር ኳስ አሳልፎ ከክፍለከታማዎች ዉድድር ጀምሮ እስከ ሀገራችን ትልቁ የዉድድር እርከን እስከ ሆነዉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድረስ መጫወት ከቻለዉ እና በርካታ ክለቦች ላይ በግብ ጠባቂነት ካገለገለዉ እንዲሁም በአሁን ግዜ በሀዲያ ሆሳዕና ከሚገኘዉ መሳይ አያኖ ጋር ሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚከተለዉን ቃለ መጠየቅ አድርጋለች።
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ ራስህን ለሀትሪክ ቤተሰቦች አስተዋውቅልን ?
መሳይ :- መሳይ አያኖ እባላለሁ ተወልጄ ያደኩት ሀላባ ከተማ ሲሆን ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ።
ሀትሪክ :- እስኪ እግር ኳስን የጀመርክበትን አጋጣሚ አጫውተን ?
መሳይ :- እግር ኳስን ሰፈር ዉስጥ በመጫወት የጀመርኩ ሲሆን ከእዛን በሀላባ ከተማ የሚዘጋጅ የክረምት የክፍለ ከተማዎች ዉድድር ላይ ተጫዉቼ ባሳየሁት ጥሩ አቋም ከተማዋን ወክዬ እንድጫወት ለሀላባ ከተማ ጥሪ ተደረገልኝ ከእዛን የእግር ኳስ ህይወቴ አንድ ብሎ ጀመረ ማለት ነዉ።
ሀትሪክ :- ብዙዉን ግዜ የሰፈር ጨዋታ ላይም ሆነ ሌሎች ላይ አብዛኞቹ ተጫዋች መሆንን እንጂ ግብ ጠባቂ መሆንን አይመርጡም እና አንተ በረኝነቱን እንዴት መረጥቅ ?
መሳይ :- እንደ እዉነታዉ እኔም ኳስን ስጀምር ተጫዋች ነበርኩ ከእዛን እንደ አጋጣሚ በአንድ ጨዋታ ላይ በረኛችን ተጎድቶ በመዉጣቱ በእሱ ምትክ በገባሁበት በእዛሁ ቀጠልኩ እንጂ እኔም ኳስን ስጀምር ፍላጎቴ በረኝነት አልነበረም ያዉ የፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ በረኛ ሆኜ ልቀር ችያለሁ።
ሀትሪክ :- ከሀላባ በኋላስ ወዴት አመራክ ?
መሳይ :- ከሀላባ በኋላ ለሀገረ ማሪያም ጥሪ ተደርጎልኝ 2004 ዓ.ም ላይ ወደ እዛ አመራሁ። ከእዛን በኋላ በሀገረ ማሪያም ለ1 አመት ያህል ነበር የቆየሁት።
ሀትሪክ :- ከሀገረ ማሪያም በኋላስ ወዴት ክለቦች አመራክ ?
መሳይ :- ከሀገረ ማሪያም በኋላ ወደ ደቡብ ፖሊስ ያመራሁ ሲሆን እዛም አንድ አመት ከቆየሁ በኋላ ወደ አርባምንጭ ከነማ በ2006 ዓ.ም አምርቼ እስከ 2008 ዓ.ም እዛ ቆይቻለሁ።
ሀትሪክ :- እስኪ በአጠቃላይ የሀላባ ፣ የሀገረ ማሪያም ፣ የደቡብ ፖሊስ እንዲሁም የአርባምንጭ ቆይታህ ምን ይመስል ነበር ?
መሳይ :- በጣም ጥሩ ግዜ ያሳለፍኩባቸዉ ክለቦች ናቸዉ። እንዲሁም እራሴን ለመጪው ግዜ ብቁ ያደረኩባቸዉ ክለቦችም ጭምር ናቸዉ።
ሀትሪክ :- ከአርባምንጭ በኋላስ ወዴት አመራክ ?
መሳይ :- ከአርባምንጭ በኋላ ብዙ ግዜ ወደቆየሁበት እና ብዙ ነገሮችን ወዳሳለፍኩበት ወደ ሲዳማ ቡና 2009 ዓ.ም ላይ አመራሁ።
ሀትሪክ :- እስኪ በሲዳማ ቡና ቤት ስለነበረህ ቆይታ አጫዉተን ?
መሳይ :- ስለ ሲዳማ ቡና ቤት ቆይታዬ አዉርቼ አልጠግብም። የእዉነት ለመናገር ስኬታማ ግዜ ያሳለፍኩበት ክለብ ነዉ ብዬ መናገር እችላለሁ።
ሀትሪክ :- ስለ ሲዳማ ቡና ቤት ቆይታህ ብዙ እያልከን ነዉና እስኪ ሲዳማ ቡና ቤት በነበርክበት ወቅት የማትረሳዉ ገጠመኝ ከኖረህ አጫዉተን ?
መሳይ :- በሲዳማ ቡና ቤት በነበርኩበት ወቅት የማልረሳዉ ገጠመኝ ቢኖር 2010 ዓ.ም ላይ ከሀዋሳ ከነማ ጋር በአዲስ አበባ እየተጫወትን እስከ 93ኛ ደቂቃ ድረስ ያለ ጎል 0-0 እያለን 93ኛ ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡና የፍፁም ቅጣት ምት (ፔናሊቲ) አግኝቶ አዲስ ግዴ መቶ ኳሷ ተመልሳበት ወደ ዉጪ ወታ ኮርና አግኝተን ወዲያዉ አዲስ ሞሮቾ አሻምቶ አዲስ ግዴ ብቻዉን ከ10 የሀዋሳ ከነማ ተጫዋቾች ጋር ተሻምቶ በግንባሩ ኳሷን ከመረቡ አገናኝቶ ጨዋታዉን 1-0 ያሸነፍንበትን አጋጣሚ ሁሌም የማስታዉሰዉ ገጠመኝ ነዉ።
ሀትሪክ :- በሲዳማ ቡና ቤት ቆይታህ በጣም የተከፋህበትን እንዲሁም በጣም የተደሰትክበትን ልዩ ግዜ ታስታዉሳለህ ?
መሳይ :- አዎን ! በጣም የተከፋሁበት ግዜ 2010 ላይ ላለመዉረድ እየተጫወትን አዲስ ግዴ 5 ቢጫ እያለበት ሳናዉቅ አሰልፈነዉ 3 ነጥባችን የተቀነሰበት ግዜ እጅግ በጣም ያዘንኩበት ግዜ ነዉ። እንዲሁም በመደሰቱ ረገድ እያንዳንዱ ለእኔ በሲዳማ ቡና የነበርኩባቸዉ ግዜያት ከምነግርህ በላይ አስደሳች ናቸዉ።
ሀትሪክ :- እስኪ ከሲዳማ ቡና ጋር ስለተለያየህበት አጋጣሚ አጫዉተን ?
መሳይ :- ስለ እሱ ብዙ ማለት ብፈልግም ከአሰልጣኙ ጋር ባለመስማማት ብቻ በሚለዉ ያዝልኝ።
ሀትሪክ :- በወቅቱ ከሲዳማ ቡና ጋር ስትለያይ ምን ተሰማህ ?
መሳይ :- የእዉነት ነዉ የምልህ ከሲዳማ ጋር መለያየቴን ለረዥም ግዜ ማመን አልቻልኩም ነበር። ብቻ ስሜቱ በጣም ከባድ ነዉ።
ሀትሪክ :- ከሲዳማ ቡና ጋር ከተለያየህ በኋላ ወዴት አመራህ ?
መሳይ :- ከሲዳማ ቡና ጋር ከተለያየሁ በኋላ ቀጥታ አሁን ወደምገኝበት ሀዲያ ሆሳዕና አመራሁ።
ሀትሪክ :- የሀዲያ ሆሳዕና ቆይታህ እስኪ ምን ይመስላል አጫዉተን ?
መሳይ :- የሀዲያ ቆይታዬ በአሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት (ሙሌ) ግዜ እጅግ በጣም ስኬታማ እና ጥሩ የሚባል ነበር።
ሀትሪክ :- አሰልጣኝ ሙሌ ሀዲያን ከለቀቀ በኋላስ ?
መሳይ :- አሪፍ ግዜ እያሳለፍኩ አይደለም።
ሀትሪክ :- ምክንቱ ምንድነው ብለህ ታስባለህ ?
መሳይ :- እሱ ለእኔም ጥያቄ የሆነብኝ ነገር ነዉ ግን ሲመስለኝ ለዜጎች በረኞች ብቻ ትኩረት ስለሚሰጥ ይመስለኛል።
ሀትሪክ :- ለዜጎች በረኞች ብቻ ትኩረት ስለሚሰጥ ያልከዉን እስኪ አብራራልን ?
መሳይ :- ሀገሪቷ ዉስጥ የበረኛ ችግር አለ ይባላል ነገር ግን እድሉን አግኝተዉ የሀገር ዉስጥ በረኞች ጥሩ አቋም ሲያሳዩ ከማሰለፍ ይልቅ ዜጎች በረኞች መቀመጥ የለባቸዉም ተብለዉ እነሱ ቋሚ ተሰላፊ እየሆኑ የሀገር ዉስጦቹ አቅሙም ችሎታዉም እያላቸዉ ተቀያሪ ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋል።
ሀትሪክ :- መፍትሄው ምንድነው ብለህ ታስባለህ ?
መሳይ :- መፍትሄው ከጎረቤት ግብፅ መማር ነዉ። ጎረቤታችን ግብፅ እንደእኛ ለረዥም አመት የበረኛ ችግር ነበረባት። ብሄራዊ ቡድኗም ለበርካታ ግዜያት አንድ በረኛ ብቻ ነበረዉ። ነገር ግን ሊጋቸዉ ላይ የዉጪ ሀገር በረኛ ስለከለከሉ በርካታ የሀገር ዉስጥ በረኞችን ማፍራት ችለዋል። አሁን ላይ ብሄራዊ ቡድናቸዉ በርካታ በረኞች ነዉ ያሉት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ዉስጥም ለሀገር ዉስጥ በረኞች ትኩረት መስጠት ቢጀመር እና ሊጋችን ዉስጥ የዉጪ ሀገር በረኞች እንዳይኖሩ ቢደረግ ለሀገራችን በርካታ ባለ ተስጥኦ በረኞች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ።
ሀትሪክ :- ቀጣይ አመት ሌላ ቡድን እንጠብቅህ ወይስ እዛዉ ሀዲያ ትቀጥላለህ ?
መሳይ :- ሁሌም ዉስጤ የሚያስበዉ አንድ ክለብ አለ እሱን ግዜዉ ሲደርስ የምናየዉ ይሆናል።
ሀትሪክ :- በበረኝነት ህይወትህ በጣም የሚፈትንህ የተቃራኒ ቲም ተጫዋች ማነዉ ?
መሳይ :- አሁን ላይ አንድ ቡድን ብንሆንም በፊት ላይ ብዙ ግዜ የሚፈትነኝ ተጫዋች ባዬ ገዛኸኝ ነዉ።
ሀትሪክ :- በእስከዛሬው የእግር ኳስ ህይወትህ ጥሩ እና መጥፎ የዉድድር ዘመን አሳልፌበታለሁ የምትልበት ግዜ ?
መሳይ :- ጥሩ የዉድድር ግዜ አሳልፌበታለሁ የምለዉ ግዜ 2011 ላይ ሲዳማ ቡና በነበርኩበት ግዜ ሲሆን መጥፎ የዉድድር ዘመን እያሳለፍኩ ያለሁት ደግሞ ዘንድሮ በሀዲያ ሆሳዕና ቤት ነዉ።
ሀትሪክ :- ለእግር ኳስ ህይወቴ አርአያዬ ነዉ የምትለዉ ተጫዋች ማን ነዉ ?
መሳይ :- ለእኔ ለእግር ኳስ ህይወቴ አርአያዬ ነዉ የምለዉ አዳነ ግርማን ሲሆን ለእኔ እንደ ወንድምም ጭምር ነዉ። ብዙ ግዜ ይመክረኛል ያበረታታኛል ብቻ በአጠቃላይ ከጎኔ ነዉ።
ሀትሪክ :- ከሀገር ዉስጥ እና ከሀገር ዉጪ የምታደንቃቸዉ ተጫዋቾች ?
መሳይ :- ከሀገር ዉስጥ የሀዲያ ሆሳዕናዉ የሳምሶን ጥላሁን አድናቂ ስሆን ከሀገር ዉጪ ደግሞ የክርስቲያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ።
ሀትሪክ :- ትርፍ ግዜህን የት ነዉ የምታሳልፈዉ ?
መሳይ :- ከእግር ኳሱ ዉጪ ያለዉን ግዜዬን ከባለቤቴ ጋር ነዉ የማሳልፈዉ ምክንያቱም በጣም ነዉና የምወዳት።
ሀትሪክ :- ስለ ቤተሰብ ሁኔታ አጫዉተን ?
መሳይ :- ባለትዳር ስሆን ሁለት ልጆችንም አፍርተናል። ልጆቻችንም አንድ ሴት እና አንድ ወንድ ሲሆኑ ሴቷ 12 አመቷ ወንዱ ደግሞ 8 አመቱ ነዉ።
ሀትሪክ :- የወደፊት እቅድህ ምንድነዉ ?
መሳይ :- የወደፊት እቅዴ እራሴን በደንብ አስተካክዬ ብቁ ሆኜ ሀገሬን ማገልገል።
ሀትሪክ :- መሳይ ተጫዋች ባይሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር ?
መሳይ :- ነጋዴ እሆን ነበር።
ሀትሪክ :- በስተመጨረሻም ማመስገን የምትፈልጋቸዉ አካላት ካሉ እድሉን ልስጥህ ?
መሳይ :- በመጀመሪያ ፈጣሪን ሲሆን ከእዛ በመቀጠል ባለቤቴን እንዲሁም ቤተሰቦቼን እና አድናቂዎቼን በሙሉ ላመሰግን እፈልጋለሁ።
ሀትሪክ :- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
መሳይ :- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ አመሰግናለሁ።