THE BIG INTERVIEW WITH GEZAHEGE KETEMA
“ኢትዮጵያ ቡናን ከምንም በላይ እወደዋለው ክለቡ እንጂ ግለሰቦች የበላይ ሊሆኑ አይችሉም”
“ደጋፊዎቹ ቢቃወሙኝም ሆነ ቢደግፉኝ ቅር አልሰኝምተጨዋቾቹን ግን ቢያበረታቱ ደስ ይለኛል”
የአሰልጣኝነት ታሪኩ በ1997 ይጀመራል…..በኢትዮጲያ ቡና የፕሮጀክት አሰልጣኝነት የተጀመረው ታሪኩ ቡና ቡና ይላል…..በ1998 እና 1999የቡናን ሲ ይዞ በ1998ቱ ሻምፒዮን ሆኗል…ከ2000-2002 ድረስ ወጣት ቡድኑን ይዞ ከቆየ በኋላ በ2003 ጊዜውን ለትምህርት ሰጠ…ታሪኩ ይቀጥላል….በ2004 እና 2005 የመድንን ታዳጊ ቡድን አሰለጠነ….2006 እና 2007 ትምህርቱን ቀጠለና ከስልጠናው ራቀ….2008 ግን ወደሚወደው ኢትዮጲያ ቡና ተመለሰ…ተስፋ ቡድኑን ይዞ ከቆየ በኋላ የዋናው ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ የህዳሴ ግድብ ዋንጫን አነሳ….2009 ይላል ጊዜው…ቡናን በዋና አሰልጣኝነት ይዞ የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ደገመ….2010 ምክትል ቢሆንም ሳይቆይ ዋናውን ቡድን ይዞ በሲቲ ካፕ 2ኛ ሆኖ ጨረሰ…ነገር ግን ፕሪሚየር ሊጉ ሳይጀመር ቦታውን ለዲዲየር ጎሜዝ ዳሮሳ አስረክቦ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኖ ሰኔ 30/2010 ድረስ ከሰራ በኋላ ኮንትራቱ በመጠናቀቁ ለ7 ወራት ራሱን ከአሰልጣኝነት አግልሏል…. ይህ ቡናን ወዳድ አሰልጣኝ ዳግም ክለቡን እንዲይዝ በየካቲት 2011 ተሹሞ በ2ኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ወደ ምስራቅ ኢትዮጲያ በማቅናት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በሚደረገው ፍልሚያ የሚወደውን ክለብ መምራት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል…… ይህ ሰው ማነው ትላላችሁ ብዬ አልጠብቅም….አሰልጣኙ የቡናማዎቹ ቤተኛ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ መሆኑ እርግጥ ነውና…. አዲሱ አሰልጣኝ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር የነበረው ቆይታ ይህን ይመስላል……
ሀትሪክ፡-ኮ/ል አወል አብዱራሂም ደደቢትን እየመሩ የችግር ጊዜ ደራሻቸውኮከቤ ነው አሉ.. ለመቶ አለቃ ደግሞ ገዛኸኝ ሆኗል….አንተስእንዲህ ይስማሃል?
ገዛኸኝ፡- በርግጠኝነት እከሌ ስላለ የሚሆን ነገር አይደለም የሚያስከብረኝ ስራዬ ነው ስራው ጥሩ ከሆን ብቻ የምትቀጥልበት ሙያ ይመስለኛል ይሄ ነው የሚሰማኝኝ… ቡናን ስለምወድ ብቻ ነው የተመለስኩት በቃ እውነቱ ይህ ነው
ሀትሪክ፡- የዳግም መመለስህን ጠብቀኸው ነበር?
ገዛኸኝ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ከምንም በላይ እወደዋለው ክለቡ እንጂ ግለሰቦች የበላይ ሊሆኑ አይችሉም ምንጊዜም የሚበልጠው ክለቡ ነው፡ ክለቡ ጥሪ ሲየደርግልኝ ችላ ማለት አልቻልኩም እኖርበታለሁ እሰራበታለሁ የምለው ክለብ በመሆኑ ቅድሚያ ሰጥቼዋለው፡፡ በርግጥ እመጣለው ብዬ አልጠበኩም በመጠራቴ ተደስቻለው መጀመሪያ አካሄዱ አሪፍ ነበር በኋላ ግን እየተንሸራተተ ሲመጣ ተሰምቶኛል በዚህ አጋጣሚ እድሉን ለሰጡኝ በመሉ አመሰግናለው በክለቡ ውስጥ ላሉ ሰዎች እድሉን ያመቻቻሉ ትልቅም ስፍራ አላቸውና መቶ አለቃና ቦርዱን አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ሁለቴ ወስደሃል…..…ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረከውን ጨዋታ እንዴት አገኘኸው?
ገዛኸኝ፡- ትልቁ አላማችን ለወጣቶች ዕድል መስጠት በመሆኑ ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው…የህዳሴው ዋንጫ እነ ሚኪና አቡበከርን ያስተዋወቀን በመሆኑ ያየናቸው ወጣቶች ጥሩ ተስፋ እንዳላቸው አይተናል…. ልጆቹ ወደፊት ክለባችንን እንደሚጠቅሙ ተስፋ አደርጋለሁ…..
ሀትሪክ፡-ረብሻው ቅር የሚያሰኝ ነበር…. ምን ማለት ትፈልጋለህ?
ገዛኸኝ፡- ቅር የሚል ነው…ፌዴሬሽኑ ግን በቀጣይ ማስተካከል አለበት ጨዋታዎቹን ሃሙስና አርብ ማድረግ እየቻለ እንዲህ ማድረጉ ልክ አይደለም …ለተጎዱት አዝኛለው…ስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ክለቦች ብዙ መስራት እንዳለባቸው ያየንበት ሆኗል….
ሀትሪክ፡ ከቤተሰቦችህ መሃል እግር ኳስ ተጨዋቾች አሉ እንዴ?
ገዛኸኝ፡- እን ኔ በመከተል ወንድሞቼ ኳስ ይጫወቱ ነበር ከእግር ኳስ በኋላ ያለውን ህይወት ሲያዩት ጥሩ ስላልነበር ኳሱን ትተው ወደተለያየ የስራ ዘርፍ ሊጓዙ ችለዋል፡፡ በተለይ በኳሱ ጥሩ ደረጃ ይደርሳል የተባለ ልጅ በአንድ መስሪያ ቤት ሱፐርቫይዘር ሆኖ እየሰራ ነው፡፡ በግሌ ለኳስ ተጨዋችነት ያበቃኝን አሰልጣኝ ሀጎስ ደስታን በጣም አመሰግናለሁ በጣም የማከብረውና ጎበዝ አሰልጣኝ ነው ተጨዋቾችን የሚረዳበት ምክንያት ደስ ይላል፡፡ከጋሽ ሀጎስ በመቀጠል ጋሽ ታዴ፣ ሁለቱ ኢንስትራክተሮች አብርሃም ተ/ሃይማኖትና አብርሃም መብራቱ፣ አሰልጣኝ ስዩም አባተ፣አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ፣ አሰልጣኝ ሃይሌ ዱባ፣ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞና የክለቡ የቦርድ አባላት፣ የቀድሞ የፌዴሬሽኑ አመራሮች አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ፣አቶ አፈወርቅ አየለ፣አቶ ብርሃኑ ከበደ፣ኮሎኔል አምሳሉ…..በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ
ሀትሪክ፡-አሰልጣኝ እሆናው ብለህ አስበህ ነበር?
ገዛኸኝ፡-ወደ ስልጠው እመለሳለሁ ብዬ አላስብኩም ምክንያቱም በትምህርት ብቻ ጥሩ እንድንሆን ነበር ቤተሰቦቼ ጫና ሲያደርጉ የነበረው፡፡ በዚህ አቋማቸው አንስማማም ነበር፡፡ እኔ ኳሱን እነርሱ ደግሞ ትምህርቱን ይመርጡ ነበር፡፡ የኢትዮጵያዊያን ወላጆች ፍላጎት ትልቅ የሚኮነው በትምህርት እንጂ በኳስ አይመስላቸውም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-ዋና የአሰልጣኝ መነሻህ የሆነ ባለሙያ አለ?
ገዛኸኝ፡- ወደ ስልጠና እንድመጣ ያደረገኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ምርጥን ይዞ በተጨዋችነት አሳልፌያለው፤… ብዙ ነገር አድርጎልኛል.. ኳሱን አቁሜ ወደ ስልጠና ስመጣ ትልቅ ዕገዛ አድርጎልኛል የርሱ ድጋፍ ታክሎበት ለዚህ በቅቻለሁ፡፡ 72 የምንሆን የቀድሞ ተጨዋቾች ተሰብስበን ስልጠና ተሰጥቶን ነበር፡፡ አሰልጣኙ ሰውነት ቢሻው ሲሆን 36 አሰልጣኞች አልፈን ለዚያ ስልጠና ደረስን ጥሩ ጊዜና እውቀት ያገኘሁት እዚያ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-7 ወር እንዴት ታለፈ?
ገዛኸኝ፡-የራሴን ማሟላት የነበረብኝ ጉዳይ ላይ ነው ጊዜ ያጠፋሁት…. ስልጠናም ወስጃለው ራሴን ለመቀየር ኮርስ ስወስድ ቆይቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-በ7ቱ ወራት ውስጥ ወደ ሌላ ክለብ ተዛውረህ ለምን አላየንህም?
ገዛኸኝ፡- ፈላጊ ክለቦች መጥተዋል…. ነገር ግን ወቅታዊው የሃገሪቱ ችግሮችወደ ክልል እንዳልሄድ አድርጎኛል… በዚያ ላይ ቤተሰቤን ትቼ ሄጄ እንዲሰጉ አልፈለኩም… በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ክለብ ባገኝ ግን ወደ ኋላ አልልምነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-አንድ ጊዜ ከዚህ በኋላ አበሻ አሰልጣኝ አንሾምም ብለው መቶ አለቃ ፈቃደ ተናግረው እንደነበር አልዘነጋውም አሁን ይህን ታሪክ ትተውት አበሻ አሰልጣኝ ተቀጠረ… ምን ተሰማህ?
ገዛኸኝ፡-ያለውን ሁኔታ አልሰማሁም ከሆነ ግን በርግጥም ትልቅ ለውጥ ነው አቅም ያላቸው ተጨዋቾችን በደንብ የሚያውቁ ምን መስራት እንዳለበት የሚረዱ ጎበዝ አሰልጣኞች አሉ፡፡ ለውጪ የሚመጡና የሀገር ውስጥ አሰልጣኞች በንፅፅር ማየትም ጥሩ ነው ደስ ይላል ጥሩ አስተውሎት ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-በ7 ወር ውስጥ ኢትዮጵያ ቡናን አይተሃል?
ገዛኸኝ፡-የክልል ጨዋታ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ የአዲስ አበባ ጨዋታ አላመለጠኝም
ሀትሪክ፡-ጫና ውስጥ ያለ ክለብን ተረክበሃል… ወቅቱ ላንተ ትክክል ነው?
ገዛኸኝ፡-ወቅቱ ትክክል ነው ወይንም አይደለም ከማለታችን በፊት ቡድኑን ስታይ የክለቡን ውሳኔ ታከብራለህ ተጨዋቾች ጋር የሚሉትን ስትሰማ የአመራሮቹ ውሳኔ ትክክል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለኔ ምንም አያስፈራኝም፡፡ ነገር ግን መቅደም ያለበት ስራዬ ነው አምነው ስራውን እስከሰጡኝ ድረስ ጠንካራ የማልሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ከአመራሩና ደጋፊው ጥሩ እገዛ ካለ የተሻለ ውጤትና ለውጥ ይኖራል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- ልምምድ ሰርታችኋልና.. ውስጡን እንዴት አገኘኸው?
ገዛኸኝ፡- በኢትዮጵያ ቡና የመልበሻ ቤት ውስጥ ያለ ስርዓት አለ፡፡ከዚያ ውጪ ያሉ ስርዓቶችም አሉ፡፡ በመልበሻ ቤቱ ውስጥ ያለው ስርዓት እጅግ ያስደስታል ሁሉም ታዛዥና በፍቅር የሚሰራበት ሂደት ነው ያለው… ያን ነገር አሁንም በመልበሻ ቤቱ ውስጥ እጠብቃለው፡፡
ሀትሪክ፡-ኢትዮጵያ ቡና የሊጉን ዋንጫ ካነሳ 8 አመት ሞላው…. ቅር አያሰኝም?
ገዛኸኝ፡- ደጋፊው መብዛቱ የሚያኮራውን ያህል ዋንጫ አለማንሣቱ ያማል.. ስሜቱን አውቋለው…ችግር ነው የምለው ደጋፊው በዝቶ ለሁሉም ፈታኝ በሆነበት ሰዓት ስራዎች በትክክል የመሄዳቸው ነገር ያጠራጥራል፡፡ ብዙ ጫናዎች አሉ.. ያም ጫና ይመስለኛል የዋንጫ ጊዜውን ያራቀው፡፡ በቀጣይ ግን እግዚአብሔር ይርዳንና የተስተካከለ ቡናን እናያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ኢትዮጵያ ቡናን የት ድረስ የማድረስ እቅዱ አለህ?
ገዛኸኝ፡- መጀመሪያ ደረጃ እንደ አሰልጣኝ የራሴ ፕላን አለኝ…በአጭር ጊዜ ፕላን የተጨዋቾቹን ሁኔታ መረዳትና ቡድኑን ከአደጋ ውስጥ ማውጣት ነው፡፡ይህንን ለማድረግ ብዙ ስራና ብዙ እገዛ ያስፈልገኛል፡፡ ሁለተኛው ቡና ወዴት መሄድ አለበት የሚለውን ጉዳይ መመልከት ነው… የረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ ቀጣይነት ያለው ሁልጊዜ አሸናፊ ቡድን የመገንባትና የቡናን ባህል ማምጣት ነው፡፡ እነዚህን በ3 ከፍዬ ለመስራት ተዘጋጅቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ደጋፊው ቡናን መልሱልን እያለ ነው..ቡናን ለመመለስ ምን ያህል ተዘጋጅተሃል?
ገዛኸኝ፡- በርግጥ እኔው ራሴ የማምንበት ነገር አለ፡፡ ደጋፊውን ሲያበዛ የነበረው ሁኔታ አይረሳኝም…ጥያቄው ለእኔ አዲስ ነገር አይደለም እኔም ሆንኩ አዲሱ አሰልጣኝ ይህን መስራት አለብን፤. የአቅሜን ያህል የምጥር ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን ለኢትዮጵያ ቡና ወሳኙ… ማራክ አጨዋወት? ወይስ ውጤት?….አንተ የቱን ትመርጣለህ?
ገዛኸኝ፡- ማራኪ አጨዋወት ያለውጤት ምንም ማለት አይደለም… ማራኪ ጨዋታ ከውጤት ጋር ሲሆን ደጋፊም ይረካል አሰልጣኙም በስራው ይደሰታል፡፡ በእርግጥ አሁን ግን የሚያስፈልገው ማሸነፍ ነው… ካለው እውነት አንፃር ደጋፊው ይህን በማሰቤ ቅር ይለዋልብዬ አላስብም፡፡ ወደኋላ ዞር ብሎ ማየት ይገባል….ከፖዘቲቩም ሆነ ኔጋቲሹም መማርና ማስተዋል ይቻላል…. በማስተዋል ደግሞ ጥሩ ነገር ማግኘት ይቻላል፡፡
ሀትሪክ፡-ከምክትል አሰልጣኞችህ ጋር በደምብአወራህ?
ገዛኸኝ፡-አዎ…. በዚህ በኩል እድለኛ ነኝ ብዬ አስባለው ቀድሞ ማመስገን ባይሆንብኝ ጥሩ ነገር አላቸው….እኔን በደምብ ማገዝ የሚችሉ ናቸው፡፡ …… (ጋምብሬ) ተጨዋች የነበረ ክለቡ ላይ የቆየ ሰው ነው…. አንተነህን ስታይ ጎበዝና አካዳሚክ አቅሙ ጥሩ የተባለ ነው ይስሃቅ፣ ሰለሞን፣ ፀጋዘሃብና ሰይፈ …አሉ ….በነርሱም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ሁሌ ከጎናችን የማይጠፋው ውብሸት ደሳለኝ.. አብሮን አለ….በዚህ ደግሞ ደስተኛ ነኝ
ሀትሪክ፡-የቀድሞ አሰልጣኝ ዲዲየር ጎሜዝ ዳሮሳ ለወጣቶች ቅድሚያ ይሰጥ ነበር.. አንተስ ይህን ታስቀጥላለህ?
ገዛኸኝ፡- ይሄ ጥያቄ መሆን የለበትም፡፡ በነ ሚኪያስና አቡበከር በማሳየቴ ደስተኛ ነኝ፤ በ2009 ከሀረር ሲቲ ያመጣኋቸው እኔ ነኝ…. ያኔ ሳመጣቸው ያገዙኝ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰዎች አሉ .. የታዳጊ አሰልጣኝ የነበረው ታደዮስ አለ… ልጆቹን ወደ ክለባችን አምጥቷል…ከዚያ ሲያነጋግረኝ ያላቸውን አቅም አየሁ፡፡ በኢትዮጲያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ላይ ጥሩ የነበሩ ናቸው…ጨዋታቸውን በቪዲዮ አየሁና ወደድኳቸው ሐረር ሲቲ ግን አለቅም አለ፡፡ ይህን ለማብረድ ጋዜጠኛ መላኩ ወ/ሰንበት መሃል ገብቶ ከአሰልጣኞቹ ጋር ለድርድር ቀረብን ልጆቹን ታጫውታላችሁ ወይ አሉ… አጫውታለሁ አልኳቸውና ቃል ገብቼ አመጣኋቸው…. ከዚያ የሚከፈለውን ገንዘቡ እንዲከፈል ተደረገናቡናን ተቀላቀሉ በዚህ አጋጣሚ የተባበሩንን በሙሉአመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ለኢትዮጲያ እግር ኳስ እድገት ወሳኙ ታዳጊ ላይ ማመን ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…..አንተስ ትስማማለህ?
ገዛኸኝ፡- አዎ ታዳጊ ላይ መታመኑማ የግድ ነው….ዕድገት ከታሰበ ወጣቶቹ ላይ መሰራት አለበት፡፡ ለአገሪቱ እግር ኳስ ብቸኛ የለውጥ ምክንያት ታዳጊ ላይ ማመን ብቻ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ገዛኸኝ ውሳኔ ሰጪ አይደለም.. ፈሪ ነው ይሉሃል… እውነት ትፈራለህ?
ገዛኸኝ፡- (ሳቅ በሳቅ) ለውሳኔ ቅርብ በመሆኔ እንዲያውም የምቸኩል ይመስለኛል፡፡ የመፍራት ሳይሆን ነገሮች የማይበት መንገድ ነው… ማየት ካለብኝ እንደ አሰልጣኝ ነው…. ከውሣኔ በፊት የሚመጣውን ቀድሞ መረዳት ይጠይቃል፡፡ እንደ አሰልጣኝ የማትረዱት ጉዳይ አለ አንድ ችግር ሲከሰት ችግሩን ወደ ሌላ ሰው የሚያሳብቡ ሰዎች አሉ…ያ ትልቅ ስህተት ይመስለኛል…መፍትሄ ላይ የሚያተኩር ሰው ደስ ይለኛል….ለውሳኔ አለመቸኮል ከጸጸት ያድናል…..እዚህ ላይ የደረስኩት ህይወቴ ላይ እየፈረድኩ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች በፍፁም አይወስኑልኝም፡፡
ሀትሪክ፡- ከትልልቆቹ አሰልጣኞች ጋር ትስማማላችሁ?
ገዛኸኝ፡- አዎ… ለሲኒየሮቹ አሰልጣኞች ክብር አለኝ…..በዚህ ደግሞ ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጠንካራ ነው ማለት ይቻላል?
ገዛኸኝ፡-ጠንካራ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም ውጤቶቹ ለዚህ መገለጫ ይመስሉኛል ጎሎቹም ሲታይ ሊጉ ጠንካራ ነው እንዳትል ያደርግሃል፡፡
ሀትሪክ፡-የተለየ ወጣ ያለብህ ክለብ አይተሃል?
ገዛኸኝ፡- እንደባለሙያ ይሄ ነው ብዬ አልናገርም… በውስጤ ግን ይዣለው… የዋንጫ እድሉ ደግሞ በዛ ባሉ ክለቦች እጅ ውስጥ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያ ዙር መጨረሻ ላይ ሆነን.. የ2ኛ ዙር መጨረሻን መናገር አይቻልም፡፡ ከኋላ የነበረው ወደፊት ሊመጣ ይችላል ብዬ አስባለውና ሁለተኛው ዙር አጓጊ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ዳኝነቱንስ እንዴት አየኸው?
ገዛኸኝ፡- ዳኝነት ላይ ምንም ቅሬታ አላቀርብም… ዳኛው ሰው ነው…ያም ቢሆን ማንም ሊሳሳት ከቤቱ አይወጣም ይሄ ሊታሰብ ይገባል፡፡ ዳኞች ላይ ቅሬታ ከማቅረብ ዳኛን የሚያሸንፍ ቡድን መገንባት ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡-አንድ ዳኛ…. የኔ ሪጎሬ መከልከል ተነቅሶ ለሽንፈት ምክንያት ሆኖ ይቀርባል አጥቂው ግን 5 ኳስ ቢያበላሽ ማንም በርሱ አያሳብብም ብሏል… አንተስ ምን ትላለህ?
ገዛኸኝ፡-እውነቱን ነው.. እኔ የምለው ነገር የለም….ዳኛ የሚረታ ቡድን መገንባት የግድ ይላል፡፡ ቫር ለምን መጣ? ፍፁም ዳኘነት ስለማይገኝ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ምን ትላለህ?
ገዛኸኝ፡- የኢትዮጵያ ቡናን ደጋፊ የማውቀው ዛሬ አይደለም፤ ደጋፊው ይወድሃል ያከብርሃል.. መንገድ ላይ መጓዝ እስከሚያቅት ድረስ ትልቅ አክብሮት አላቸውደጋፊዎቹ ቢቃወሙኝም ሆነ ቢደግፉኝ ቅር አልሰኝምተጨዋቾቹን ግን ቢያበረታቱ ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-የተጨዋች ዝውወር አሁን ሊከፈት ነው… ተሳታፊ ነህ?
ገዛኸኝ፡-እንደባለሙያ መሃል ላይ ዝውውርን መመልከት አይቻልም… የትኛውን ተጨዋች ነው ብቃት ይዞ የምታገኘው? መጀመሪያ አመት ላይ የተሻለ የተባለውንለመያዝ መሞከሩ ይሻላል….ያም ሆኖ የተሻለ ተጨዋች ካገኘሁ ማስፈረሜ ዝሙሩ አይቀርም፡፡
ሀትሪክ፡-የደጋፊ ተቃውሞ ሲበረታ ቡድኑ ይጎዳልና ይሄ እንዳይሆን ምን ይደረግ?
ገዛኸኝ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ሲኒየሮቹና ወጣቶች እኩል የሆነ የስነ ልቦና ደረጃ የላቸውም ይሄ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት ተቃውሞ ያለ ነገር ነው ጥሩ ቡድን ካጣህ ተቃውሞ ይኖራል ግን የምቃወመው የትኛውን ነው የሚለው መመለስ አለበት፡፡ ለቀጣዩ 2ኛ ዙር ላይ ትልቁሃይላችን ደጋፊያችን ነው፡፡ 2009 ስመጣ ቡድኑ ላይ ተመሳሳይነገሮች ተከስቶ ነበር፡፡ ሁኔታውን ስንቀይር ደጋፊው ከጎናችን ነበር ዛሬም የምጠብቀው ይህን ነው ወደ ተቃውሞ ይገባል ብዬ አልሰጋም፡፡
ሀትሪክ፡-ስትሰናበት በቃህ ስትባል የቀረበው ምክንያት ደካማ አቋም አሳይተህ ነው? ወይስ?
ገዛኸኝ፡-(ሳቅ) ይህን አላውቀውም ምክንያቱን የሚይውቁት ያሰናበቱኝ ሰዎች ናቸው፡፡ በቃ የስራ ዝውውር ሲሰጥህ መቀበል የግድ ነው የቡድኑ ም/ል አሰልጣኝ ተብዬ ተቀምጬ ሳለ ውሉን ማስቀጠል ወይም ማሰናበት የነርሱመብት በመሆኑ ለምን ብዬ አልጠየኩም ዋና አሰልጣኝ ብሆን ኖሮ መጠየቄ አይቀርም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-ላንተ የመኖር ምክንያት የሆነ ህልም አለ?
ገዛኸኝ፡- ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ቡናን ባለድል ማድረግና ደጋፊውን ማስደሰት ህልሜ ነው፡፡ የሀገሬን ባንዲራ ማስጠራትም ደስይለኛል፤ ወጣቶችን አሳድጎ ለቁምነገር ማብቃትም ህልሜ ነው…. በልጆች መደሰት ህልሜ ነው… ለምሣሌ አብዱራህማን (ግሪዳው)፣ አቡኪ፣ ሀብታሙ፣ አፍሪካን፣ ፍፁም … ጨምሮ ብዙ ወጣቶችን አሳድጌ ማየቴ ያስደስተኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ክልል ላይ የአዲስ አበባ ክለቦች ለማሸነፍ የሚቸገሩት ክለቦች ጠንካራ ስለሆኑ ወይስ ዳኝነቱ ጥሩ ስላልሆነ ነው?
ገዛኸኝ፡-ዳኞች ጥሩ አይደሉም አስቸጋሪ ናቸው የሚለው መቅረት አለበት፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ቡናን ይዤ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ጎንደር ላይ ፋሲልን በ4 ጎል ማሸነፍ፣ ሃዋሳንና ወላይታ ዲቻን መርታት ችያለውና ዳኝነቱ ላይ ማሳሰብ አያስፈልግም የቡድኖቹ የጨዋታ ሂደት ውጤት እንዳይገኝ ካላደረገን በስተቀር ዳኝነቱንመኮነኑ ቢቀር ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ቤተሰብ መስርተሃል?
ገዛኸኝ፡- አዎ ባለትዳርና የ2 ልጆች አባት ነኝ ባለቤቴ ዘለቃሽ ወርቁ (ዶዶ) ትባላለች…. ልጆቼ ደግሞ አርሴማና ባስልኤል ይባላሉ
ሀትሪክ፡-ባስልኤል… የመጽኃፍ ቅዱሱ ጥበበኛ?
ገዛኸኝ፡-(ሳቅ) አዎ መፅሀፍ ቅዱስ ላይ ያለው ባስልኤል ጥበበኛውን ስለምወደው ነው ልጄን ባስልኤል ያልነው፡ ቤተሰቦቼ ይደግፉኛል በዚህ በኩል ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ቤተሰቦቼን ሳስብ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ጥሩ ፊት ቤቴ ስገባ ይጠብቀኛል፡፡ ቤተሰቦቼ ጋር 7 ወር ሳሳልፍ እኔን ደስተኛ ለማድረግ የሚጥሩት ነገር ያስደስተኛል… በቤተሰቦቼ ወንድሞቼና እህቶቼ በርሷም ወንድሞችና እህቶች ተከበናል… በዚህ በኩል ደስተኛ ነኝ አበበሽብሩ በህይወቴ ትልቅ ድጋፍ ያደረገልኝ ሰው ነው…አሊ ሰይድም ከጎኔ ሆነው ይደግፉኛል….ለዚህም ሁሉንም አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ገዛኸኝ በምን ዘና ይላል?
ገዛኸኝ፡-መፅሀፍቶችን አነባለው ፊልም አያለው ከዚያ ውጭ ዋነኛ ዘና አድራጊዎቼ ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ የዘር ችግር ገብቷል ይህን እንዴት ታየዋለህ?
ገዛኸኝ፡-ቢጠፋ የምመኘው የዘር ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ወደዚህ ምድር ሲመጣ ለምድር አበባና ውበት ነው ሁሉም ሰው ይህን ማሰብ አለበት፡፡ የምድር አበቦች ተብለን እንዴት የዘር ፀብ ውስጥ እንገባለን? ይሄ ከእግር ኳሱ ውስጥ ቢጠፋ ያስደስተኛል፡፡
ሀትሪክ፡-የምትመርጠው አሰልጣኝ ማነው?
ገዛኸኝ፡-የአርሴን ቬንገርና ፔፕ ጋርዲዮላ ወዳጅ ነኝ…. የነርሱን የልምምድ ሂደት ማየት ደስ ይለኛል፡፡ እንደ አሰልጣኝ የአሰልጣኞቹንየስልጠና ሂደት መከታተል ይመቸኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ጆዜ ሞውሪንሆ? ወይስ አርሴን ቬንገር?
ገዛኸኝ፡-(ሳቅ) ምንም ጥርጥር የለውም ቬንገር ምርጫዬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ክርስቲያኖ ሮልዶ ወይስ ሜሲ?
ገዛኸኝ፡-(ሳቅ) ሁለቱንም እመርጣለው ሁለቱምኮ የእግር ኳስ ውበት ናቸው…በዘመኔ ስላየኋቸው ደስተኛ ነኝ
ሀትሪክ፡-…ጨረስኩ.. የምታመሰግነው ሰው ካለ?
ገዛኸኝ፡- በኔ ህይወት ውስጥ ብዙ የሚመሰገኑሰዎች አሉ….. ከሁሉ በላይግን ጤና ሰጥቶኝና ጠብቆኝ ለዚህ ያበቃኝ እግዚአብሔር የቅድሚያውን ምስጋና ይወስዳል ትልቁ ድርሻ የራሱ ነው…. ቤተሰቦቼ፣ ባለቤቴና ልጆቼ እናትና አባት ወንድምና እህቶቼ በኔ ህይወት ውስጥ ድርሻ አላቸውናላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡በአጠቃላይ በኔ ህይወት ውስጥ አንድ ነገር ጣል ያደረጉ በሙሉ ምስጋናዬ እንዲደርሳቸው እፈልጋለሁ፡፡
አስተያየት ይስጡ