ለገጣፎ ለገዳዲ ከወራጅ ቀጠና ለማምለጥ ራሱን ያጠናከረ ቢሆንም የሊግ ኩባንያው አዲስ የፈረሙትን ተጨዋቾች ማሰለፍ አትችሉሞ ማለቱ ቅሬታ አስነስቷል።
በተለይ ባለፈው ቅዳሜ በሊጉ 14ኛ ሳምንት መርሃግብር በሲዳማ ቡናጋ 2ለ0 በተሸነፉበት ጨዋታ 2ኛ ዙር ስላልተጀመረና የትኛውም ክለብ በተዘጋው የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጨዋቾች መጠቀም የሚችለው ከ16ኛው ሳምንት ጀምሮ ነው በሚል መከልከላቸው የለገጣፎ አመራሮችን አስቆጥቷል።
ክለቡ ከፌዴሬሽኑ ቲሴራ እስካላችሁ ድረስ መጫወት ትችላላችሁ የሚል ምላሽ ቢሰጠውም ሊግ ኩባንያው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ የጨዋታው ዳኞች በጸጥታ ሃይሎች ታግዘው አዲስ የፈረሙት ተጨዋቾች እንዳይገቡ ማድረጉ ታውቋል። ከድሬዳዋ ጋር በተካሄደውም ጨዋታ ለገጣፎዎች መጠቀም የቻሉት በ12 ተጨዋቾች ብቻ መሆኑ ቅሬታ ፈጥሯል።
- ማሰታውቂያ -
ሊግ ኩባንያው ውድድሩ በብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ምክንያት ለ20 ቀን እንደሚቋረጥ በመረዳት የዝውውር መስኮቱ አንደኛ ዙር ሳይጀመር እንዲከፈት ቢያደርግም የክለቦቹ ዕድልና መብትን ሳያከብር ያስፈረምናቸውን ተጨዋቾች አትጠቀሙ ማለቱ ተገቢ አይደለም ሲል ለገጣፎ ለገዳዲ ቅሬታውን አሰምቷል።
ክለቡ ዛሬ ለፌዴሬሽኑ ባስገባው ደብዳቤ ፌዴሬሽኑ ያስፈረምናቸውና ቲሴራ የሰጠንን ተጨዋቾች ስም ዝርዝር በአማርኛና በእንግሊዘኛ እንዲሰጠንና በ15ኛው ሳምንት ከመቻል ጋር የምናደርገው ጨዋታ ላይ መጠቀም እንድንችል ይደረግ ሲል አሳስቧል።
ክለቡ በአጽንኦት እንደገለጸው”የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ካምፓኒ ከተቋቋመበት ደንብና ዓላማ ውጪ ራሱን እንደፌዴሬሽኑ በመቁጠር ራሱን መዝጋቢ ራሱን አጽዳቂ ራሱን ፈራጅ አድርጎ የሚሰራበት ህጋዊ ያልሆነን ድርጊት ፌዴሬሽኑ እንደሚያስቆምና መብቱን እንደሚያስከብር በፌዴሬሽኑና በጽ/ቤቱ ሃላፊ ላይ እምነቱ አለን” ሲል ገልጿል።
“በፖሊስም ሆነ በአወዳዳሪ አካል ህጋዊ ተጨዋቾቼ እንዳይገቡ የተደረገበትን መንገድ በተመለከተ በህጋዊ አካሄድ እንደምንሄድ እየገለጽን የደረስንበትን ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ በግልባጭ እናሳውቃለን” ሲል ጉዳዩ ህግ እንዲመለከተው እንደሚያደርጉም የክለቡ አመራሮች ዝተዋል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁንና የሊግ ኩባንያው ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፉ ባለፈው ዓርብ በጉዳዩ ላይ ቢመክሩም ለውጥ አልተገኘም ቲሴራ የተሰጣቸውን ተጨዋቾች የመሰለፍ መብት ሊግ ኩባንያው እንዲያከብርም ፌዴሬሽኑ የሰጠው ማሳሰቢያ ተግባራዊ ሳይደረግም ቀርቷል። በእስካሁኑ የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ለገጣፎ ለገዳዲ በ6 ነጥብና 24 የግብ ዕዳ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የተዛወሩት ተጨዋቾች እንዲገቡ አለመደረጉ በአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቡድኑን የማትረፍ ጥረት ላይ ውሃ ማፍሰስ እንዳይሆንም ተሰግቷል።
ሊግ ኩባንያው በተዘጋው የዝውውር መስኮት የፈረሙ 21 ተጨዋቾች ከ16ኛው ሳምንት ጀምሮ ነው መሰለፍ የሚችሉም አለበለዚያ ውጤቱ ፎርፌ ይሆናል ብሎ ተጨዋቾችን ላስፈረሙትም ሆነ ላላስፈረሙት ክለቦች በደብዳቤ ማስጠንቀቁ ይታወሳል።