“በአንድ ግብ ብቻ ተወስኜ መቅረትን አልፈልግም፤ ወላይታ ድቻ ተሻሽሏል፤ እስከ 4ኛ ባለው ደረጃም ሊጉን ሊያጠናቅቅ ተዘጋጅቷል”በረከት ወልዴ /ወላይታ ድቻ/

በመሸሻ ወልዴ /G.BOYS/

ወላይታ ድቻን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ቡድኑን በምርጥ ብቃቱ ላይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ኳስን ከቡድኑ ጓደኞች ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል በመጫወት ወደ ተቃራኒ ቡድን የሜዳ ክልል ለመግባት የሚያደርገው ጥረት ሲያስደንቀው ታይቷል። አልሸነፍ ባይነቱና ኳስንም ለመንጠቅ የሚያደርገው ጥረትም በጥሩነቱ ይገለፃል። ይሄ ተጨዋች ወጣቱ በረከት ወልዴ ሲሆን ወደፊት አንድአንድ ክፍተቶቹን ካስተካከለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለትልቅ ደረጃ ይበቃል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።
ከወላይታ ድቻው አማካይ ጋር የሀትሪክ ስፖርት ድረ ገፅ አዘጋጅና ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጓል፤ ተከታተሉት።

ስለ ኳስ ጅማሬው

“እግር ኳስን ልጅ ሆኜ ነው መጫወት የጀመርኩት፤ ጥልቅ ፍቅርም ነው የነበረኝ። ትንሽ አደግ እያልኩ ስመጣ ለጥሩ ደረጃ መድረስን አሰብኩና ጠንክሬ መስራትን ጀመርኩ። ጠንክሬ ስለሰራውም የዛሬው ደረጃ ላይ ደረስኩኝ”።

በቤተሰብ አካባቢ ኳስ ከመጫወቱ ጋር በተያያዘ ስለነበረው አመለካከት

“ያኔ አባቴ ነበር ትምህርትን በግል ትምህርት ቤት ውስጥ አስገብቶኝ እና ከፍሎልኝም እማር ስለነበር ኳሱን ከምጫወት ይልቅ ለትምህርቴ እንዳስብ በማድረግ እንዳልጫወት ይከለክለኝ የነበረው። የሆነ ጊዜ ላይ ግን የወረዳ ጨዋታ ላይ ኳስን እንደምጫወት ሲነግሩት እዛው ሊያየኝ መጣና እንደ ብዙዎቹ ሰዎች እሱም በችሎታዬ ሊያደንቀኝ ችሎ መቶ ብርም ሰጠኝ። እኔም ለሰጠኝ ብር አመስግኜውም ለአባቴ ኳሱንም ትምህርቱንም አብሬ እንደማስኬደው ነገርኩት። ከዛ ጊዜ በኋላ እሱ እኔን ምንም ነገር ማለትን ትቶ እንደውም ሶዶ ላይ በምንጫወትበት ጊዜ ያበረታታኝና ክፍተቴን እያየም ይመክረኝም ነበር”።

በቤተሰባቸው ስፖርተኛው እሱ ብቻ እንደሆነ

“እኔ ብቻ አይደለሁም፤ እኛ ቤት ውስጥ 3 ወንድሞችና 2 እህቶች ናቸው ያሉኝ። ከእኔ ውጪ አንዱ ወንድሜም ዘላለም ወልዴ ይባላል አሁን ወደ ወላይታ ድቻ ዋና ቡድን በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አማካኝነት አድጎ ከአጠገቤ ጋርም ነው የሚገኘውም”።

በልጅነት ዕድሜው አድንቆት ስላደገው ተጨዋች

“የመጀመሪያው በእኛ የወላይታ ክልል አረካ ከተማ ውስጥ ብዙ ተጨዋቾች ጎልተው ባይወጡም ሙሉዓለም የተባለው ተጨዋች ችሎታ ግን እኔን ይስበኝ ነበር። እሱን አድንቄውም አደግኩ። ተጨዋቹ በክለብ ደረጃ ባይጫወትም አሁን አሰልጣኝ ሊሆን ችሏል። እኔንም አሰልጥኖኛል። ከእሱ በመቀጠል ደግሞ ስም ካላቸው የአገራችን ተጨዋቾች ውስጥ በችሎታው በጣም የማደንቀው ተጨዋች በእኔ ቦታም ስለሚጫወት ጭምር አዲስ ህንፃን ነው፤ ከውጪ ተጨዋቾች ደግሞ የንጎሌ ካንቴ አድናቂ ነኝ”።

ወላይታ ድቻን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሲጀመርና አሁን ላይ በምን መልኩ እንዳገኘው

“ውድድሩ ሲጀመር ቡድናችን በአብዛኛው ማለት ይቻላል በታዳጊና ወጣት ተጨዋቾች ስለተገነባ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጥሩ ብንሆንም የልምድ ማነስ ችግር ግን ውጤትን አሳጥቶናል። አሁን አሁን ላይ ግን እንደ ጋቶች ፓኖምን የመሳሰሉ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች በስኳዳችን ውስጥ ስላካተትን እና አዲስ የመጣው አሰልጣኝ ዘላለምም ጥሩ የሆነ የታክቲክ ልምምድን ስለሚሰጠን ከዛ ውጪም የቡድናችን የቲም ስፕሪትም አሪፍ መሆኑም
ባለፈው ጨዋታ በፋሲል ከነማ ብንሸነፍም በፍጥነት ከድሬዳዋ ከነማ ጋር የነበረንን ጨዋታ ረተን ወደ አሸናፊነት እንድንመለስ አድርጎናልና ይሄ በቀጣይነት ወደ ውጤታማነት ሊወስደን እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥቶናል”።

 

ቤትኪንግ ላይ ጥሩ መጫወቱን ተከትሎ ራሱን ምርጥ ተጨዋች አድርጎ ያስብ እንደሆነ

“በፍፁም ራሴን በዛ ደረጃም ላይ አልገልፀውም፤ በእግር ኳሱ ገና ነኝ፤ ብዙም ይቀረኛል። ልምድ ካላቸው ተጨዋቾች የምማረው እና ያየሁት ብዙ ነገር አለ። ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምደርስና የሀገሪቱም ምርጥ ተጨዋች እንደምሆንም በፈጣሪም እርግጠኛ ነኝ”።

ወላይታ ድቻን ውድድሩ ሲጠናቀቅ በምን ደረጃ ላይ እንደሚያገኙት

“አሁን በጥሩ አቋም ላይ ነው የምንገኘው። የሚሰጠን ልምምድም አሪፍ ነው። ከዛ በመነሳት ከዚህ በኋላ በሚኖሩን ጨዋታዎች ስኬታማ የምንሆንበት እድላችን ሰፊ ስለሆነ ቤትኪንጉን ከ2ኛ እስከ 4ኛ ባለው ደረጃ ላይ ሆነን እናጠናቅቃለን”።

ከሐዋሳ ከነማ ስለሚያደርጉት የነገው ጨዋታ

“የእዚህ ጨዋታ ውጤት ለእኛ ካሸነፍን ወደ ላይ በነጥብ ስለሚወስደን ከዛ ውጪም ደግሞ እታች ያሉትም እንዳይደርሱብን ስለምንፈልግም ይህ ግጥሚያ በእኛ የበላይነት ይጠናቀቃል”።

ስለ ወጡለት ቅፅል ስሞች

“በጣም ከሚታወቁት ውስጥ ስለ ሁለቱ ቅፅል ስሞቼ አንድ አንድ ነገርን ማለት እፈልጋለሁ፤ የእኔ ዋናና የትምህርት ቤት መጠሪያዬ ስም በረከት ሆኖ ቱኔና ድጉናው ደግሞ የወጡልኝ ቅፅል ስሞች ናቸው። ቱኔ በቤት ውስጥ የምጠራበት ነው። ግን ትርጓሜውን አላውቀውም። ድጉናውን ደግሞ እሸቱ መና ነው ያወጣልኝ”።

አንድ ጎልን ብቻ በሊጉ ስለማስቆጠሩ

“በእዚህ ቡድን ቆይታዬ በአንድ ግብ ብቻ ተወስኜ መቅረትን አልፈልግም። ሌሎች ግቦች እንዲኖሩኝ እፈልጋለሁ። እነዛን ማሳካቴም የማይቀር ነው”።

ማሻሻል ያለበት

“ብዙ ነገር አለ፤ ከእነዛ ውስጥ አንዱም ለአጥቂ የሚመች ኳስን ሁሌም በተደጋጋሚ ጊዜ መስጠት ደስ ይለኛልና ያን ብቃቴን በጣም ማዳበር እፈልጋለሁ”።

ስለ ቀጣይ ጊዜ ህልሙ

“በእግር ኳስ የእስካሁኑ ጉዞዬ ለታዳጊ ለወጣት እና ለኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን የመመረጥ እድሎችን ባገኝም ከጨዋታ መሰረዝና ጉዳት ጋር በተያያዘና በተለያዩ ምክንያቶች ከቡድኑ ውጪ ልሆን ችያለሁ። ያን የመመረጥ እድል ማግኘት ገና ወጣት ተጨዋች ከመሆኔ አኳያ ለእኔ ጥሩ መነሳሳትን ነው የፈጠረልኝ። አሁን ደግሞ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ለመመረጥና ለመጫወትም ጭምር እቅድን ያወጣሁበት አጋጣሚም ስላለ ያን እድል ማግኘቴ አይቀሬ ነው”።

ወላይታ ድቻን ሲገልፀው

“ይሄ ቡድን ለእኔ ብዙ ነገሬና አሳዳጊዬ ነው። ከወጣት ቡድኑ አንስቶ ክለብ ሳልቀይር አሁንም ድረስ ላለፉት ተከታታይ ዓመታቶች እየተጫወትኩላቸውም ነው። በእነሱ እጅ አድጌም ነው ኳስንና ብዙ ነገርንም ያወቅኩት። ይህ ስለሆነ ወላይታን ሁሌም ከውስጤ አላወጣሁትምና እነሱ ላደረጉልኝ ነገር ሁሉ ምስጋናዬን አቀርብላቸዋለሁኝ”።

በምን እናጠቃል…..

“በምስጋና ነዋ! አሁን ለወላይታ ድቻ ዋናው ቡድን ስጫወት አራተኛ ዓመቴን ይዣለሁ። ለእዚህ ደረጃ እንድበቃም እኔን ከስር ጀምሮ በማሰልጠንና ብዙ ነገርንም እንዳውቅ በወጣት ቡድኖች ደረጃ ዋንጫ ስናገኝ ጊዜ ጀምሮ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ ብዙ ያስተማረኝ ነገር አለና እሱን አመሰግነዋለሁ። ሌላ የማመሰግናቸው በእዚህ ቡድን ቆይታዬ ጥሩ ልምምድን ይሰጠን የነበረውንና ጥሩ የማሰልጠን አቅም ኖሮት በወጣት ተጨዋቾች ላይ እምነት ያለውን አሰልጣኝ ደለለኝ ዲቻሳን እና ቤተሰቦቼን ጎደኞቼን እንደዚሁም ሁሌም የሚያበረታቱኝን የወላይታ ህዝብን ደጋፊዎቻችንን ከዛ ውጪም የቡድን ጓደኞቼን ላመሰግናቸው እወዳለሁ”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website