” ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ነው ያለኝ ትምህርቴን በማይጎዳ መልኩ እጫወት ነበር ”
” ሌሎች ክለቦች የተሻሉ ጥቅማ ጥቅሞችን እያቀረቡልኝ ትቼ ነው የመጣሁት ”
” በአንደኛውም በሁለተኛውም ዙር ቃል የገባንላቸውን ነገር አሳክተን እንደምናስደስታቸው እርግጠኞች ነን ” ዋቁማ ዲንሳ /ነቀምት ከተማ/
የ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር የመጀመሪያ ዙር ውድድሮች ተጠናቀው የሁለተኛው ዙር ውድድሮች በባህርዳር ፣ ባቱ እና ሀዋሳ ከተማ ላይ እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል ። በመጀመሪያው ዙር ውድድር ላይ ድንቅ ብቃታቸውን ያስመለከቱን ወጣት ተጫዋቾችን ከየምድብ የመረጥን ሲሆን በምርጫው ላይ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ተሳትፈውበታል ።
- ማሰታውቂያ -
ከጥቂት ቀናቶች በፊት የምድብ አንድ ምርጥ ተብሎ ከተመረጠው ተጫዋች ጋር ያደረግነውን ቆይታ ወደናንት ማድረሳችን ይታወሳል ።
ዛሬ ደግሞ በምድብ ሶስት በጅማ ከተማ ተካሂዶ በነበረው የመጀመሪያ ዙር ውድድር ላይ የምድቡ ምርጥ ተብሎ ከተመረጠው የነቀምት ከተማው ተጫዋች ዋቁማ ዲንሳ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እናቀርብላችኋለን ።
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ ራስህን አስተዋውቀን ?
ዋቁማ :- ዋቁማ ዲንሳ እባላለው የነቀምት ከተማ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ነኝ ።
ሀትሪክ :- እግር ኳስ አጀማመርክ እንዴት ነበር ?
ዋቁማ :- በሰፈራችን ሜዳ ነበር ልጅ እያለሁ ሊጫወቱ የሚመጡ ልጆችን አይ ነበር ከዛ እኔም መጫወት ጀመርኩኝ ። ሰፈር ስጫወት ያየኝ በግሉ እያሰለጠነ የነበረው አሰልጣኝ ታደለ አለሙ ወደ ራሱ ፕሮጀክት አስገባኝ ። አሰልጣኝ ታደለ እኛን ማሰራት ሲያቆም ሙዲን በሚባል ልጅ ከ15 ዓመት በታች እሱ ጋር መስራቴን ቀጠልኩ ። ኋላ ላይ አሁን አብሮኝ በመሐል ተከላካይነት እየተጫወተ ከሚገኘው ኢብሮ ጉቱ ጋር ለተጨማሪ አንድ አመት ተጫወትኩኝ ።
ሀትሪክ :- ከዛ ወዴት አመራህ?
ዋቁማ :- ከዛ በ2004 ወደ 17 ዓመት በታች ነው ያመራሁት በ2005 ደግሞ ለነቀምት ከነማ መጫወት ጀመርኩኝ ።
ሀትሪክ:- የክለብ ቅይታህ እንዴት ነበር?
ዋቁማ:-የሚገርም እና የማይረሳ ጊዜ ነው የነበረኝ ምክንያቱ ደግሞ ኦሮሚያ ላይ የተደረጉት ሁለት ውድድሮች ኦሮሚያ ሊግ እና የኦሮሚያ ሻምፒዮና በመሆን ነው የጨረስነው ። ሀዋሳ ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮናም ክለባችንን ወደ ብሔራዊ ሊግ ( አንደኛ ሊግ ማለት ነው ) ማሳደግ ችለናል ።
ሀትሪክ:- በብሔራዊ ሊግ የነበረህ ቆይታ እንዴት ነበር?
ዋቁማ :- ክለባችን ብሔራዊ ሊግ ላይ መቆየት የቻለው አንድ አመት ብቻ ነው በ2008 ከፍተኛ ሊግ ሲጀመር በበጀት እና ከተማችን ላይ ባለው ኢንተርናሽናል ስታዲየም ምክንያት ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደግ ችለናል ። ብሔራዊ ሊግ እየተጫወትኩም የመላው ዩኒቨርስቲዎች ውድድር ላይም ተጫውቻለሁ ።
ሀትሪክ :- ትምህርትህ እየተከታተልክ ኳስህን አላቆምክም ነበር ማለት ነው ?
ዋቁማ:- አዎ አላቆምኩም ምክንያቱም ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ነው ያለኝ ትምህርቴን በማይጎዳ መልኩ እጫወት ነበር ።በዚህ አጋጣሚ የነቀምት ከነማ የአሰልጣኞች ስታፍ እና የወለጋ ዩኒቨርስቲ አስተማሪዎችን እና ትምህርት ቤቱን ላመሰግን እወዳለሁ ። ትምህርቴን እየተከታተልኩ የምወደውን እግር ኳስ እንድጫወት ስለፈቀዱልኝ ።
ሀትሪክ :- ትምህርት እና እግር ኳሱን አንድ ላይ ማስኬድ አልከበደህም ነበር?
ዋቁማ :- ምንም አልከበደኝም ነበር ምክንያቱ ደግሞ አሰልጣኞቼ ከትምህርቴ እንዳልሰናከል ከሜዳ ውጪ ያሉ ጨዋታዎችን እንድቀር እና እንድማር በሜዳችን ያሉ ጨዋታዎችን ደግሞ እንድጫወት ስላደረጉኝ ነው ። ትምህርት በሌለኝ ሰዓት ደግሞ ከሜዳ ውጪ ያሉ ጨዋታዎችን እየሄድኩ እጫወት ነበር ። በ2010 የቡድናቾን አምበል በመሆን ጭምር ቡድኔን ሳገለግል ነበሮ።
ሀትሪክ :- ምን ነበር ስትማር የነበረው? መቼስ ጨረስክ?
ዋቁማ :- ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪግ ነበር የተማርኩት በ2011 ከወለጋ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ድግሪ በኢንጅነሪግን ተመርቄያሉሁ ።
ሀትሪክ :- በቃ ከዚህ በኋላ ጥያቄዎችን የማቀርብልህ ኢንጅነር ዋቁማ እያልኩ ነው(ሳቅ) ?
ዋቁማ :- (ረጅም ሳቅ) ኧረ በጭራሽ እንደ መጀመሪያው ይሻለኛል ።
ሀትሪክ :- ለበርካታ አመታት ከፕሮጀክት ጀምሮ ለነቀምት ከነማ ስትጫወት ነበር በ2013 ግን በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለሆነው ሀምበሪቾ ዱራሜ ፊርማህን አኖረህ ነበር ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከነቀምት ከተማ ወተህ አዲስ ከተማ አዲስ ባህል እና አዲስ ጓደኛ መተዋወቁ አልከበደህም ነበር ?
ዋቁማ:- ለሀምበሪቾ መፈረሜን የሰሙ ጓደኞቼም ሆኑ የሰፈር ሰዎች እንደሚከብደኝ እና መሄድ እንደሌለብኝ ይነግሩኝ ነበር ። እኔ ግን ለፈተናዎች ራሴን በሚገባ ስላዘጋጀው ምንም አልፈራሁም ነበር። የሀምበሪቾ አመራሮች ተጫዋቾችና ደጋፊዎች በደንብ ነበር የተቀበሉኝ በተለይ ደጋፊዎች እና አመራሮች ቶሎ ከልጆች ጋር እንድግባባ አግዘውኛል ።
ሀትሪክ:- ከመምጣትህ በፊት የተለየ ዝግጅት አድርገህ ነበር ?
ዋቁማ :- የተለየ ዝግጅት አላደረኩም እግር ኳስ ለመጫወት የሚያስፈልጉ ስራዎችን ግን በተጨማሪነት ስሰራ ነበር።
ሀትሪክ :- የሀምበሪቾ ቆይታህስ እንዴት ነበር?
ዋቁማ :- እጅግ በጣም ደስ የሚል ቆይታ ነበረኝ ወደ ፕሪምየር ሊጉም ለመግባትም ተቃርበን ነበር በመጨረሻ አልተሳካም እንጂ ።
ሀትሪክ :- በ2013 ወደ ሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ይመጣሉ ከተባሉ ክለቦች በዋናነት ሀምበሪቾ ነበር የተጠበቀው ያልገባችሁበት ምክንያት ነበር ?
ዋቁማ :- እንዳልከውም ወደ ፕሪምየር ሊግ ያድጋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ክለቦች ነበርን መሐል ላይ በተፎካካሪዎች የጣልናቸው ነጥቦች እና በርካታ የዳኝነት በደሎችም ይደርስብን ነበር በዛ ምክንያት መግባት አልቻልንም።
ሀትሪክ :- በ2013 በከፍተኛ ሊጉ ወጥ አቋማቸውን ካሳዩን ጥቂት ተጫዋቾች አንዱ አንተ ነበርክ የትግራይ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ አለመሳተፋቸውን ተከትሎ ከፕሪምየር ሊጉ ከወረዱ እና በከፍተኛ ሊጉ ሁለተኛ የወጡ ክለቦች ሀዋሳ ላይ ውድድር አድርገው ነበር ። በውድድሩ ላይ ራሳቸውን በሚገባ ያሳያሉ ብለን ከጠበቅናቸው ተጫዋቾች አንዱ አንተ ነበርክ ነገር ግን በውድድሩ ላይ የተጠበከውን ያክል ራስህን አላሳየክም ምክንያቱ ምንድነው?
ዋቁማ :- በርካታ ጨዋታዎችን በምወደው የአጥቂ አማካይነት ነበር አመቱን የጨረስኩት ይሄ ውድድር ድንገት ሲመጣ የተከላካይ አማካይ ይጫወት የነበረ የውጭ ዜጋ ሳይመጣ ቀረ በዛ ምክንያት በውድድሩ ላይ የተከላካይ አማካይ ሆኜ ነው የተጫወትኩት እና ያ ይመስለኛል ራሴን እንዳላሳይ ያደረኝ ።ሀትሪክ :- በ2014 ወደ ቤትህ ተመልሰህ ከአምናው የተሻለውን ዋቁማን እያሳየከን ነው ቡድናቹም ከአንደኛው ዙር ጀምሮ ወጥ አቋም በማሳየት ምድቡን በአንደኝነት እየመራ ይገኛል ።የዘንድሮውን የውድድር ዓመት እንዴት አገኘኸው ?
ዋቁማ :- ዘንድሮ ወደ ቤቴ የተመለስኩበት ምክንያት ከተማችን ኢንተርናሽናል ስታዲየም ኖሮቶ የፕሪምየር ሊግ ተወካይ አላገኘም እናም በዛ ቁጭት ሌሎች ክለቦች የተሻሉ ጥቅማ ጥቅሞችን እያቀረቡልኝ ትቼ ነው የመጣሁት ።እኔ ጋር የነበረው መንፈስም የቡድኑ አባላት ጋር ነበር ። የሁላችንም አላማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደግ ስለሆነ የሚከፈለውን መስዋዕት ከፍለን ቡድናችንን እዚህ አድርሰነዋል ።
ሀትሪክ :- በሜዳ ላይ ወጥ አቋም የምታሳዩበት መንገድስ ምንድነው?
ዋቁማ :- ነቀምት ከነማ ተጫዋቾችን በመያዝ ነው የሚታወቀው ዘንድሮ እንኳን አምስት ልጅ ብቻ ነው የተጨመረው ሌሎቹ ሁለት አመት ሶስት አመት ከቡድኑ ጋር የቆዩ ናቸው እናም ምክንያቱ እሱ ነው ።
ሀትሪክ:- ወደ አንተ ስመለስ ጅማ ላይ በነበረው የአንደኛ ዙር ውድድር በአሰልጣኞች እና በተጫዋቾች ምርጫ የአንደኛ ዙር ምርጥ ተጫዋች ተብለህ በሀትሪክ ስፖርት ተመርጠኻል ። የተለየ ዝግጅት አድርገኻል ለዘንድሮ ውድድር ?
ዋቁማ :- ክረምት ላይ ራሴን በሚገባ ሳዘጋጅ ነበር ወደ ቡድኑ ከተቀላቀልኩ በኋላም አሰልጣኞቼ ከሚሰጡኝ ልምምዶች በተጨማሪ በግሌም እሰራለው ያ ይመስለኛል ወጥ አቋም እንዳሳይ ያደረገኝ ።ሀትሪክ :- የዘንድሮ እቅድህ ምንድነው?
ዋቁማ :- ትልቁ እቅዴ የወለጋ ነዋሪዎች የናፈቁትን ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ገብተን ማሳየት ነው በግሌ ደግሞ ሀገራችን ላይ የተሻሉ የተባሉ ክለቦች መግባት ነው ።
ሀትሪክ :- ስለዚህ የወለጋ ህዝብ ከእናንተ ምን ይጠብቅ ?
ዋቁማ:- በአንደኛውም በሁለተኛውም ዙር ቃል የገባንላቸውን ነገር አሳክተን እንደምናስደስታቸው እርግጠኞች ነን ።
ሀትሪክ :- ማስተላለፍ የምትፈልገው ነገር ካለ ?
ዋቁማ:- ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር ያለኝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው ። እኛ የወለጋ ህዝቦች ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተዋደን ተፋቅረን እየኖርን ያለን ሰዎች ነን አሁን ደግሞ ወደ ሀገራችን ትልቁ ሊግ አድገን አንድነታችንን እናጠናክራለን ። ለሀገራችን ሰላም ፍቅር እና አንድነት አስፈላጊ ነገር ስለሆነ ሀገራችንን እንጠብቃት እላለው ።ሀትሪክ:- በመጨረሻም ማመስገን የምትፈልገው አካል ካለ ዕድሉን ልስጥክ
ዋቁማ :- በመጀመሪያ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ በመቀጠል ቤተሰቦቼን በጣም አመሰግናለሁ ። በፀሎት የሚያግዙኝ ጓደኞቼ እና የቤተክርስቲያን አገልጋዮችንም ማመስገን እፈልጋለሁ ። በመጨረሻ ከፕሮጀክት ጀምሮ አሁን እስካለሁበት ድረስ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ ። እናንተም አክብራቹ እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ክበሩልኝ ።