THE BIG INTERVIEW WITH SHEWAREGA DESTA
በይስሐቅ በላይ
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- …ፊትህን ትኩር ብዬ ሣየው ንግግርህንም ስታዘብ ብስጭጭት ብለሃል…ስሜትህም በጣም የተቆጣ…በጣም የጋለም ይመስላል…፤…ምነው በሠላም ነው…?
ሸዋረጋ፡- …ምን ሠላም አለ…?…እንደዚህ አይነት አመራር እያለ…?
ሀትሪክ፡- …እንዴ…!…እንዴ…!…ሰውዬ ወዴት እየሄድክ ነው…?…ብለህ…ብለህ ደግሞ…ከመንግስት ጋር ልታጣላኝ ነው እንዴ…?…ስፖርቱን ትተህ…ፖለቲከኛ ሆንክ እንዴ…?
ሸዋረጋ፡- …አንተ…ደግሞ…የምን ፖለቲካ አመጣህ…?…እኔ የማወራው ስለ ስፖርትና ስፖርት ብቻ ነው…ሳንባዬ ራሱ ከስፖርት ውጪ አይተነፍስም…፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን እኮ በአንድ ወቅት ”…አክቲቪስት…” ነኝ ብለህ በሚዲያ ስትናግር የሰማሁህ መሰለኝ… ?
ሸዋረጋ፡- …አዎን…ብያለሁ…!…አሁንም እደግመልሃለሁ አክቲቪስት ነኝ…!…ይሄንን ስልህ ግን የስፖርቱ…በተለይ የእግር ኳሱ አክቲቪስት ነኝ ማለት እንደፈለኩ አንተም ሌላውም እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- “…የስፖርቱ አክቲቪስት ነኝ…”…ማለት ምን ማለት ነው…?…እስቲ ግልፅ አድርግልኝ…?
ሸዋረጋ፡- …በቃ…የደማሁለት…፣…የለፋሁለት ስፖርት…፣…የስፖርት ባለ ድርሻ አካላት…ተጨዋቾች፣…አሰልጣኞች ሲበደሉ ፍትህ ሲነፈጉ አይቼ ዝም የማልል…ለስፖርቱ ፍትህ፣ ለእግር ኳሱ እድገት፣ለለውጡ የምታገል ታጋይ ነኝ ማለት ነው…፡፡…እነዚህ ነገሮች እስኪመጡ በአገኘሁት መድረክ ሁሉ የምፋለም፣ድምፄን ከፍ አድርጌ የማሰማ አክቲቪስት ነኝ…፤…አሁንም ድምፄን ከፍ አድርጌ ለሙያው፣ለስፖርቱ እየጮሁኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን ምን የሚያስጮህ ነገር ተፈጠረ…?
ሸዋረጋ፡- …እንዴ አንተ በአገር ውስጥ የለህም እንዴ…?…እኛ ለእግር ኳሱ የለፋን፣የደከመን፣የደማን ሰዎች ከቤታችን ተገፍተን እየተጣልን ነው…፤…ገና አንድ ሸማ ብቻ የለኮሰው አመራር ማህበራትን ከጠቅላላ ጉባኤ ውጪ ለማድረግ እየለፋ ነው…ይሄ በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡ፌዴሬሽኑ በማን አለብኝነት ይሄንን እየፈፀመ እንዴት አንጮህ…?እንዴትስ ድምፃችንን ከፍ አድርገን አናሰማ…?
ሀትሪክ፡- …ከየአቅጣጫው ከፍተኛ ተቋውሞ እየዘነበበት ያለው ፌዴሬሽኑ በ2011 አሻሽሎ ያወጣውና በጠቅላላ ጉብኤው ለማፅደቅ እየተዘጋጀበት ያለው የመተዳደሪያ ደንብ ማህበራትን በጠቅላላ ጉባኤው ያላቸውን ድምፅ የሚነጥቀውን የመተዳደሪያ ደንብን ነው የምትለው…?
ሸዋረጋ፡- …አዎን…!…ፌዴሬሽኑ አሁን በማን አለብኝነት ያዘጋጀውና በጠቅላላ ጉባኤው ለማፀደቅ እየሮጠ ያለው ቀደም ሲል በጠቅላላ ጉብኤው እንደ ዋና ባለድርሻ ሲሳተፉ የነበሩ ማህበራትን ማለትም የአሰልጣኞች ማህበርን፣የዳኞች ማህበርን፣ የሴቶች እግር ኳስ ማህበርን፣የወንዶች እግር ኳስ ተጨዋቹ ማህበርን ድምፅ አልባና የእግር ኳሱን ዋነኛ ተዋናዮች ባይተዋር ለማድረግ ነው እንቅስቃሴ አውጥቶ እየሠራ ያለው፤ይሄ ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ነው፡፡ አንተ እንዴት ለእግር ኳሱ የቅመም ያህል የሚታዩ ዳኞችን ባይተዋር ታደርጋለህ…?…እንዴትስ ለእግር ኳሱ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አሰልጣኞች፣ ተጨዋቾች ያሉበትን ማህበር እንዴት ድምፅ አልባ ታደርጋለህ…?…ይሄ ለእኔ ተጫውቶ እንዳለፈ፣ ለእግር ኳሱ እንደደማ ሰው በጣም ያማል፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን እኮ ይሄ ገና ረቂቅ ነው…፤… አልፀደቀም…?
ሸዋረጋ፡- …እዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርቦ ያልፀደቀ ነገር የለም…፤…ይቅርታ አድርግልኝና ሁሉንም ብዬ ለመደምደም ቢቸግርኝም አብዛኛው የጉባኤ አባላት ከህጉ ይልቅ የሚያሳስበው የሚያገኘው አበል ነው፡፡ ከዚህ በፊት ትልቅ አጀንዳ…ለእግር ኳሱ ጠቃሚ የሆነ አጀንዳ ተነስቶ እሱን እንኳን የመጨረስ አቅም የማይታይባቸው አበሉ ላይ ብቻ የሚሮጡ የጉባኤ አባላት…የቀረበውን አጀንዳ ፈትሾ፣መርምሮ ከመቃወም ይልቅ አጨብጭበው ሲያፀድቁ ለበርካታ አመታት ማየታችን ነው ቀድመን እንድንጮህና የሚመለከተው አካል ይሰማልን እያልን ያለነው፡፡ በ2006 ዓ.ም ተሻሽሎ የፀደቀው መተዳደሪያ ደንብ ማህበራትን በተመለከተ ያስቀመጠው ነገር አለ፤የክልልና የከተማ አሰተዳደር፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የፕሪሚየርና የብሔራዊ ሊግ ክለቦች፣የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የክብር ፕሬዚዳንት፣ የክብር አባላት፣የአገር አቀፍ ደኞች፣የአልጣኞች፣የሴትና የወንድ ተጨዋች ማህበር አባላት ናቸው፤ እያንዳንዳቸው በሁለት ድምፅ ይወከላሉ ይላል፡፡ አሁን ፌዴሬሽኑ ለማስፀደቅ ያዘጋጀው ደግሞ እነዚህን ማህበራት ከጨዋታ ውጪ የሚደረግ ነው…እንደ 2006ቱ በደንብ የተብራራ ነገር የለውም…፤…ተሻሻለ በተባለው አዲሲ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 2 ትርጓሜው “አባል ማለት በፌዴሬሽኑ ተመዝግቦ የጠቅላላ ጉባኤው አባል የሆነ ማለት ነው” ካለ በኋላ “ማህበራት ያለ ድምፅ ጠቅላላ ጉባኤውን ይሳተፋሉ” ብሎ ለእግር ኳሱ መቆም የማገር ያህል የሆኑትን፣ከማህበራት ውጪ ፌዴሬሽኑ ራሱ ፌዴሬሽን እንደማይሆን እየታወቀ እነሱን ከጨዋታ ውጪ አድርጓል፤ይሄ ለእኔ እብደት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ማለት…?
ሸዋረጋ፡- …በቃ…ይሄ የእውቀት ሥራ አይደለም ለእኔ…ከእውቀት ነፃ፣ትርጉም አልባ አስተሳሰብ ነው ብዬ ነው የማስበው…፤…ምክንያቱም የእግር ኳሱን ዋነኛ ተዋናዮች የሆኑትን ማህበራት ድምፅ ነፍገህ ምን አይነት ጉባኤ…?…ምን አይነት እግር ኳስ ልትመራ ነው…?…እግር ኳስ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞችና ዳኞች ድምፃቸውን የማያሰሙበት፣ የማይወከሉበት ጠቅላላ ጉባኤ እኔ በአለም ላይ አላየሁም ወይም አልሰማሁም፡፡ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ወደዚህ ቦታ የመጡት፣እግር ኳሱም እግር ኳስ የሆነው በዳኞች፣በተጨዋቾች፤በአሰልጣኞች ጠብ ብሎ በፈሰሰው ላባቸውና ደማቸው መሆኑን ሊያውቁት ይገባል፡፡ ትናንት በአሰልጣኞች ቅጥር ላይ ያሻውን ሲያደርግ የነበረው ፌዴሬሽን አሁን ደግሞ ወደ ሙያተኞች መጥቷል፤እንደውም ይሄ ነገር ምን ትርጉም እንደሚሰጠኝና እንደሚያስታውሰኝ ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡- …ምን ያስታውስሃል…?…ምን ትርጉም ይሰጥሃል…?
ሸዋረጋ፡- …ቀደም ሲል ፌዴሬሽኑ የብ/ቡድኖች አሰልጣኞች፣የጽ/ቤት ኃላፊ ሲቀጥር መቅጠር ላለባቸው ሰዎች በልካቸው የተሰፋ ጃኬት ይመስል በልካቸው ነበር መስፈርት የሚያወጣው…፤…ይሄን ሲያደርግ ዝም የተባለው ፌዴሬሽን አሁን ደግሞ በራሱ በሚመቸው መልኩ ጃኬት አሰፍቶ መልበስ ያማረው ይመስለኛል፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ድርጊት ለእኔ የሚሰጠኝ ትርጉም ይሄ ነው፤ዳኞች፣ተጨዋቾች አሰልጣኞችን ያሰባሰቡ ማህበራት እንዴት በጠቅላላ ጉባኤው ያለ ድምፅ እንዲሳተፉ የመተዳደሪያ ደንብ ተረቆ ይቀርባል…?…ይሄ የጤነኛ አዕምሮ ውጤት ነው ለማለት ይቸግረኛል…፤…ደግሞም የአለምንና የአህጉሪቱን እግር ኳስ በበላይነት ከሚመሩት ፊፋና ካፍ መርህና አስተሳሰብ ውጪ ነው…አሁንም እደግመዋለሁ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ወደ ስልጣን የመጡት በዳኞች፣በአሰልጣኞችና በተጨዋቾች ላብና ደማቸውን አፍስሰው ባቆሙት ፌዴሬሽን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ነገሩን አክርሮ ከመቃወም በዘለለ ምን መደረግ አለበት ነው የምትለው…?
ሸዋረጋ፡- …በመጀመሪያ የዳኞችን፣የተጨዋቾኝና የአልጣኞች ማህበርን ያገለለ፣ድምፅ የነፈገ እነሱን ያላቀፈ ጠቅላላ ጉባኤ ለእኔ የተሟላ ጠቅላላ ጉባኤ አይደለም…፤…እዛ ውስጥ ካሉት ከሁሉም በላይ ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም…ዋነኛው ተዋናዮችና ባለ ድርሻ አካላት እነዚህ ማህበራት ናቸውና እነሱን ከሚያገለው ረቂቅ የመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ይሄ ከወዲሁ እንዲታረም…፤…ፌዴሬሽኑ ወይም ይሄንን አጠናን የሚሉ አካላት ለማረም የሚረዳ ቅን ልቦና ካጡ ጠቅላላ ጉባኤው ወድቅ በማድረግ እግር ኳሱን የሚታደግ ሥራ እንዲሠራ ከወዲሁ ለማሳስብ ነው የምወደው ፌዴሬሽኑ ማህበራትን ከጉባኤው ውጪ በማድረግ ያለ ድምፅ እንዲሳተፉ ውሳኔ መወሰን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?
ሀትሪክ፡- አንተ ንገረኝ እንጂ እኔ ምን አውቃለሁ…?
ሸዋረጋ፡- …ቤታቸው ያልሆኑ ሰዎች ሰው ቤት መጥተው ቤታቸው የሆኑ ሰዎችን ውጡ የማለት ያህል ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁንም አልገባኝም….?
ሸዋረጋ፡- …አማርኛ አይደለም እንዴ የምናወራው…?…እንዴት አልገባህም…?…እንግዲህ ካልገባህ…ምን አደርጋለሁ…በደንብ ግልፅ እንዲሆንልህ…የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለእኛ ቤታችን ነው…ተጫውተን፣ ላባችንን ደማችንን አፍስሰን ላለፍን፣አሁንም እግር ኳሱን በተለያየ መንገድ ላገዝን ሰዎች ቤታችን ነው፡፡ የእኛን ያህል ኢምንት አስተዋፅኦ የሌላቸው፣ ቤታቸው ያልሆኑ ሰዎች ቤታችን ውስጥ ገብተው እኛ ባለቤቶቹን አባረውናል፤ ድምፃችንን ነፍገውናል፡፡ ለደከምንለት፣ለለፋንለት፣ለደማንለት እግር ኳስ ድምፃችንን ነጥቀው ተቀምጣችሁ የበይ ተመልካች ሁኑ አይነት ሕግ አውጥተው ሊያፀድቁብን እየሮጡ ነው፤አሁን አምርረን እየተቃወምን ያለነውም ይሄንኑ ነው፡፡ የፊፋና የካፍን መርሀ ጥሳችኋል ተው ታቀቡ…ዋነኛ ተዋናዮቹ እኛ ሆነን ድምፃችን አትንጠቁን በሚመለከተን ጉዳይ አይመለከታችሁም አትበሉን እያልን እየጮህን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የፌዴሬሽኑ አካሄድ ወይም ማህበራትን ያገለለው ረቂቅ ሕግ ልክ ነው የሚል አቋም ባይኖረንም…ግን እኮ እናንተ ማህበራትም ጠቅላላ ጉባኤ ሲመጣ ድምፅ ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር በጉባኤው የሚጠቀስ ተሳትፎ የላችሁም ደካማ ናችሁ በሚልም ትታማላችሁ እኮ…?
ሸዋረጋ፡- …በዚህ በኩል ክርክር መግጠም አልፈልግም…ክፍተት ሊኖር ይችላል ግን መፍትሔው ማማለል ወይም ድምፅን መንጠቅ ነው ብዬ አላምንም…፤…እንደተባለው ክፍተቶች በማህበራት ላይ ሊኖር ይችላል…ፌዴሬሽኑ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት ማገዝ፣መደገፍ ነው ያለበት፡፡ ይበልጥ አክቲቭ እንዲሆን…፣…ይበልጥ እንዲንቀሳቀስ ማገዝ እንጂ ይሄንን ምክንያት አድርጎ ድምፅ መንጠቅ ወይም ማህበራትን በጉባኤው የበይ ተመልካች የሚያደርግ ሕግ ለማስፀደቅ መሯሯጥ ማለት ለእኔ መኪናንን ያለ ሞተር እንድትሄድ የማሰብ ያህል ነው፡፡ የተጨዋቾች፣የአሰልጣኞችና የዳኞች ማህበራትም ለጠቅላላ ጉባኤውም ሆነ ለፌዴሬሽኑ የመኪና ሞተር ያህል ወሳኝ ናቸውና ይሄንን ስህተታቸውን ሳይመሽ በጊዜ ማረም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ውሳኔውን ባስተላለፉት በሙሉ ባዝንም በዋናነት በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በጣም አዝኛለሁ…
ሀትሪክ፡- …በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ላይ እስከማዘንና እስከመውቀስ ያደረሰህ ምንድነው….?
ሸዋረጋ፡- …በመጀመሪያ ደረጃ ከወቀሳው በፊት አንድ ነገር ላስቀድምልህ፤ ለኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ትልቅ አክብሮት አለኝ፤ይሄ ክብሬ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ከኢንስትራክተር ሰውነት የተጠበቀውን ባለማግኘቴም በጣም አዝኛለሁ፡፡ ለማዘን ያበቃኝ ደግሞ ኢንስትራክተር ሰውነት ማህበራት ላይ እንደዚህ አይነት ፍትሀዊ ያልሆነ ውሳኔ ሲወሰን በዝምታ ማለፉ አልነበረበትም፤መቃወም ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆን መታገል ነበረበት፡፡ ይሄን ባለማድረጉ እንደ ግልም ሆነ እንደ ማህበር በጣም አዝኜያለሁ፡፡ ምናልባት ያደረገው ትግል ቢኖር እሰማ ነበር እሱም “ታግዬ ነበር አልቻልኩም” ብሎ ይናገር ነበር፤ይሄን ባለማየቴ ሰውነት ውሳኔው ሲወስን ዝምታን በመምረጡ አዝኛለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ኢንስትራክተር ሰውነት አንድ ግለሰብ ነው…ብቻውን የፌዴሬሽኑን ውሳኔ እንዴት ማስቀረት ይችላል…?…ደግሞስ ከሌላው ሥራ አስፈፃሚ በተለየ ለምን እሱን በተናጠል መውቀስ አስፈለገ…?…ሌላ ነገር አያስመስልም….?
ሸዋረጋ፡- …ይቅርታ አድርግልኝና ሰውነት ሙያተኛ ነው…፤…ተጫውቶ፣በአሰልጣኝነት ለዚህች ሀገር ብዙ የለፋ የደከመ ሰው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሰውነት ራሱ የማህበራት ማለትም የአልጣኞች ማህበር አመራርም አባልም ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፈ ወይም ያለ ሰው እንዴት ማህበራት ድምፃቸውን ሲነጠቁ ዝም ይላል?ሰውነት ወደ ፌዴሬሽኑ እንዲመጣ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ማህበራት ዋነኞቹ ናቸው፤ያላቸውን ሁለት ድምፅ ሰጥተው እንዲመረጥ ምክንያት የሆኑት እነዚሁ ማህበራት ናቸው። እነዚህ ማህበራት ለሰውነት ድምፅ የሰጡት እኮ ድምፃችን ይሆናል እኛን ወክሎ ለእግር ኳሱ እድገት ይታገላል ብለው ነው፤ ሰውነት ግን ይሄን ውለታ የዋሉ ማህበራት ድምፃቸው ሲነጠቅ ዝም ማለቱ ድምፁን ባለማሰማቱ እንደግልም እንደ ማህበርም አዝናለሁ፡፡ ምክንያቱም ይታገለልናል ብለን ነው እኔንም ጨምሮ ሌሎችም ማህበራት ድምፃችንን ያለስስት የሰጠነው። ለሰውነት ክብር ቢኖረኝም የዳኞች፤ የተጨዋቾችና እሱ አባልና አመራር ሆኖ የለፋበት የአሰልጣኞች ማህበር ድምፁን ሲነጠቅ ዝምታን መምረጡ እንዳሳዘነኝ መደበቅ አልፈልግም፡፡
ሀትሪክ፡-… ፌዴሬሽኑ 24 ክለቦችን በሁለት ምድብ ከፍሎ ሊያካሄድ የነበረው ውድድር ምስጋና ለስፖርት ኮሚሽን ይሁንና ውድቅ ሆነ እንጂ በዚህ መልኩ የማወዳደር ሃሣብ ነበረው…፤…ይሄንን የፌዴሬሽኑን የተሳሳተ አሰራርስ እንዴት ታዘብከው…?
ሸዋረጋ፡- …በቃ…ይሄ እኮ ነው…የፌዴሬሽኑ አመራሮችን ገመና ወይም ማንነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው…፤…እነማን ይሄንን ፌዴሬሽን እንደሚመሩ…እውቀታቸው የት ድረስ እንደሆነ አጋልጦ የሰጣቸው ይሄ አስፈሪ ውሳኔያቸው ነው…፡፡…አንተ እንዴት የምትተዳደርበትን የፊፋና የካፍ ሕግ ትጥሳለህ…?…እንዴት ሠላም፣ፍቅር፣አንድነት ይኑር፣በዘር በጎሣ መከፋፍል ይቅር እየተባለ በሚሰበክበት…መንግሥትም በዚህ ዙሪያ ሌት ተቀን እየሠራ ባለበት ሰዓት እንዴት አንዱ ክልል ከሌላው ክልል እንዳይገናኝ አድርገህ የውድድር ፎርማት ትቀርፃለህ…?…አማራና ትግራይ፣ወላይታና ሲዳማ አንድ እንዲሆኑ፣በመካከላቸው ልዩነት እንኳን ቢኖር ፊትተህ ወደ አንድነት ታመጣለህ እንጂ እንዴት ዳግም እንዳይገናኙ አድርገህ ውድድር ትቀርፃለህ…?…ይሄ ለእኔ የክፍለ ዘመኑ አሳፋሪ ውሳኔ ነው…፤…የፌዴሬሽኑ ሰዎች እንዴት እግር ኳሱን እየመሩት እንደሆነ ያጋለጠ ውሳኔ ነው።…ከሁሉም በላይ ፌዴሬሽኑ ይሄንን የፎርማት ለውጥ ሲያስብ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑትን ክለቦች ጠርቶ ወንበር ስቦ እስኪ እንወያይ ምን እናድርግ? ብሎ እንኳን ሳያማክር ነው እንዳለ ሊጭንባቸው የሞከረው…። መንግሥት (ስፖርት ኮሚሽን) ግን በክለቦች መካከል የአንድነት ሳይሆን የልዩነት ግንብን የሚገነባውን ይሄንን ፎርማት ውድቅ አደረገው እንጂ በታሪካዊ ሥህተት የተሞላ ውሳኔ ነበር፡፡ እንደዚህ አይነት የመንግሥትን ፍላጎት የሚጋፋ፣ልዩነትን የሚያሰፋ የሚመስል ውሳኔን በደንብ ሳያጠኑ የሚመለከታቸውን ዋነኛ ተዋናዮች ሳያማክሩ ዝም ብለው ሊጭኑ የነበሩ አመራሮች ይሄ ውሳኔያችን በአደባባይ ተዋርዶ ኮሚሽኑ በጠራው ስብሰባ ላይ ውድቅ ከተደረገባቸው በኋላ ተመልሰው ወደ ፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት መግባት አልነበረባቸውም…
ሀትሪክ፡- …ይሄን…ያህል…?
ሸዋረጋ፡- … በቃ… ከዚህ በላይ የእግር ኳስ ትልቅ ኪሣራ ወይም ውድመት የለም…፤…ወቅቱን፣ ስፖርት ለልዩነት ወይም ለሠላም ያለውን ትልቅ ዋጋ ካለመገንዘብ፣ ከእውቀት ማነስ የወሰኑት ውሳኔ ውድቅ ሲደረግባቸው ትልቅ ስህተት መስራታቸውን አምነው መክሰራቸውንም ተቀብለው ከኃላፊነት ይነሣሉ (ሪዛይን) ያደርጋሉ ብዬ ነበር የጠበኩት፡፡ የአለም እግር ኳስ ገዢ ፊፋ ስፖርት ከፖለቲካ፣ ከዘር፣ ከጎሣ፣ ከሃይማኖት ከልዩነት የፀዳ መሆን አለበት እያለ እንዴት የአማራና የትግራይ…፣የሲዳማና የወላይታ ክለቦች እንዳይገናኙ ብለህ የውድድር ፎርማት ትቀርፃለህ…?ይሄ በክለብ መካከል ችግር እንኳን ቢኖር ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ውሳኔ ነው…?…ከዚህ የተሻለ መፍትሔስ የለም…? ፌዴሬሽኑ የሚተዳደርበትን የራሱን ብሎም የዓለም አቀፉን ሕግ የጣሰስ አይሆንም…?…ከሁሉም በላይ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ የአማራና የትግራይ ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮችን እስከማነጋገር የደረሱት ልዩነቱን ለማጥበብ አልነበረም እንዴ…?…ይሄን ያህል ርቀት ሄደው አሁን እነሱ እንዳይገናኙ አድርገው ከማቀራረብ ይልቅ የሚያለያይ ፎርማትን መቅረፅ ለእኔ በህይወት ዘመኔ ያየሁት አሣፋሪ ስህተት ነው፡፡ ደግነቱ ኮሚሽኑና ክለቦች ይሄ የደካማ አስተሳሰብ ውጤት የሆነን ፎርማት ውድቅ አድርገውታል፡፡
ሀትሪክ፡- 24 ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚያደርጉት የውድድር ፎርማት ሳይጠነሰስ መጨንገፉ ቢያስደስትም ይሄን ተከትሎ የተፈጠረው ሌላ ስህተትስ የተዘነጋ አይመስልህም…?
ሸዋረጋ፡- …የትኛው ስህተት…?
ሀትሪክ፡- …ቀጣዩ ውድድር በ24 ክለቦች መካከል የሚደረግ በመሆኑ ከፕሪሚየር ሊጉ የወረዱ ክለቦች እንደማይወርዱ ከታች ወደ ላይ የመጡትን ጨምሮ ሌሎች የተሻሉ ቡድኖች በፎርማቱ ይታቀፋሉ የሚል ባዶ ተስፋ ተሰጥኦቸው ሜዳ ላይ የቀሩ አይመስልህም…?
ሸዋረጋ፡- … እንግዲህ ከእውቀት፣ከጥናት ውጪ ወቅታዊ ሁኔታን ሳያገናዝቡ ሣይመክርበት በስሜት ፈረስ ጋልቦ የሚወሰን ውሳኔ ብዙ መዘዞችን ይዞ ነው የሚመጣው…፤…አሁን በ24 ክለቦች መካከል ለማካሄድ የታሰበው ውድድር ሣይፀነስ ጨንግፏል፡፡ በዚህ በኩል ያለው ፋይል ቢዘጋም ከፕሪሚየር ሊጉ አትወርዱም የተባሉትና ባዶ ተስፋ የተሰጣቸው የእነ መከላከያ ጉዳይ ምን እንደሚሆን በግልፅነት የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርደው ሊጉ በ24 ክለቦች መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ ስለሚካሄድ አትወርዱም ተዘጋጁ ከተባሉት ውጪ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመቀላቀል ያልታሰበ ሲሳይ የወረደላቸው የሚመስሉት የእነ መድን፣ አርባ ምንጭ እና ሌሎች ክለቦች ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ምክያቱም ፌዴሬሽኑ ለእነዚህ ክለቦች ባዶ ተስፋ ከ24 ክለቦች ጋር በአዲሱ ፎርማት ነው የምንወዳደረው ብለው ለዚያ የሚሆን በጀት መደበው ተጨዋች አስፈርመው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በዚህ የጋለ ስሜት ውስጥ ያሉ ክለቦችን እንዲሁም ከሊጉ አትወርዱም የሚል ባዶ ተስፋ የተሰጣቸውን ክለቦች አሁን ደግሞ ፎርማቱ ውድቅ ስለተደረገ እዛው ነው የምትወዳደሩት ሲባሉ ምን ሊሠማቸው እንደሚችል መገመቱ ያን ያህል ከባድ አይሆንም፤ብዙ ውዝግብና ሌላ ጭቅጭቅ እንደሚያስነሣ ነው… የምጠብቀው፡፡
ሀትሪክ፡-…ከዚህ ያለጥናት ከተቀረፀው ፎርማት ውጪ ፌዴሬሽኑ የተጨዋቾች ከፍተኛው የደሞዝ ጣራ 50 ሺህ ብር እንዲሆን የወሰነው ውሳኔ ሌላው የዓመቱ ውዝግብ የፈጠረ ጉዳይ ነው… ቀደም ሲል ተጨዋች እንደነበረ…ለተዋቾችእንደሚቆረቆር በዚህ ላይስ ምን አስተያየት አለህ…?
ሸዋረጋ፡- …የተጨዋቾች ደሞዝ ላይ እናውራ ከተባለ …የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጨዋቾችን ደሞዝ ከመቀነሱ በፊት ወይም የደሞዝ ጣራ ከማስቀመጡ በፊት የሚመለከታቸውን አካላት ማማከር ነበረበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከዚህ ውጪ በመደረጉ በተለይ ጉዳዩ በዋናነት ለሚመለከታቸው ተጨዋቾች ዱብ እዳ ነው የምለው…፤…ለተጨዋቾቹ ብቻም አይደለም በእነሱ ሥር ለሚተዳደሩ ቤተሰቦቻቸውም ዱብ እዳ ነው…ለዚህም ነው ተጨዋቾች ውሳኔውን ለመቀበል እስከመቸገር የደረሱት፡፡ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከታቸው ተጨዋቾቹን በመሆኑ የእግር ኳሱም ዋነኛ ተዋናይ ከመሆናቸው አንፃር ጠርቶ ማነጋገር ማወያየት ሃሣባቸው ይምረርም ይጣፍጥም ማዳመጥ ማነጋገር ነበረበት፤ፌዴሬሽኑ ግን ይሄንን አላደረገም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ 90% እና ከዚያ በላይ የመንግሥት ክለቦች ናቸው፤የሚተዳደሩትም በመንግሥት ነው፡፡ በእነሱ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ቢያስቸግርም ከመንግሥት ድጎማ ውጪ በራሣቸው የሚተዳደሩ ክለቦች እጣ ፈንታስ…ምን መሆን አለበት…?…ሕጉ እነሱ ላይስ እንዴት ነው ተግባራዊ የሚሆነው…?…በሚለው ዙሪያ ከእነሱም ጋር መነጋገር ያስፈልግ ነበር፤ይሄ የተደረገ አይመስለኝም፤ይሄ ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ ይሄንን ሣያደርግ የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናዮች ድምፅ ሳይሰማ ለመጫን መሞከሩን እንደ ተጨዋቾች ማህበር በመቃወም ደብዳቤ እስከመፃፍ ደርሰናል፡፡
ሀትሪክ፡- ለተጨዋቾች የሚከፈለውና እግር ኳሱ ያለበት ደረጃ አይመጣጣንም ብለው ሃሣቡን እንደ ሃሣብ የሚደግፍ አሉ…አንተስ የተጨዋቾችን ደሞዝ ወደ 50 ሺህ ብር ማውረድ ብቻውን እግር ኳሱን ያሳድገዋል…የተፈለገውን ለውጥ ያመጣል ትላለህ…?
ሸዋረጋ፡- …ደሞዝ መቀነስም መጨመርም ብቻውን እግር ኳስን ሊያሳድግ አይችልም፣ እግር ኳስ የወጣቶች ስፖርት እንደመሆኑ መጠን ቀጣይነት ያለው እድገት ወይም ውጤት እንዲኖረው ከተፈለገ ቃሉ ቢያስለችም በወጣቶች ላይ ብዙ መሰራት አለበት፡፡ ክለቦች ከስፖርት ቤት ለተገዛ ዋንጫ ሲሮጡ ነው የምታየው። እግር ኳሱ አላደገም እየባሰበት ነው ከሚሉ ሰዎች ጋር የሃሳብ ፀብ የለኝም እስማማለሁ፤እግር ኳሱ በሚፈለገው ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ ደመወዙን በተመለከተ ከራሳችን ኢኮኖሚ አንፃር ብዙ መስሎ ሊታየን ይችላል ግን ከሌሎች አለማት እግር ኳስ ጋር ካነፃፀርከው በጣም አንሶ ነው የሚታየው፤እኔ ለተጨዋቹ ገንዘብ መስጠቱ ላይ ፀብ የለኝም፣ በዝቷል አንሷል ውዝግብ ውስጥም መግባት አልፈልግም፡፡ ግን እግር ኳሱ ተመልካቹን የሚመጥን ቢሆን ነው የምለው። ከዚህ አንፃር ደሞዝ ቅነሣ የተገባው እግር ኳሱ ስላላደገ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ደመወዙን በማሳነስ እድገቱን ስለማናመጣው በዚህ ውስጥ ሆኖ ማሰብ አልፈልግም፡፡ ከደሞዙ በፊት ወይም ከእሱ ባልተናነሰ ክለቦች ቢ እና ሲ በቡድን እንዲያቋቋሙ ማስገደድ ለእግር ኳሱ እድገት ይጠቅማል፤ደመወዙ መቀነስ ከተፈለገ ቢያንስ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ተጨዋቾች ብናወያያቸው ፍትሀዊ ይሆን ነበር፡፡ የመዘጋጃ ጊዜ ሳይሰጥ ዱብ እዳ መሆኑ ለባሰ ችግር እንዳይደረገን እሰጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከፍ ያለ ገንዘብ ስንሰጥ የኖርነው ከተጫዋቾች ከፍ ያለ ነገር ከመጠበቅ ነው። ምን አልባት ይሄን ነገር ካለ ውይይት ስለተጫነ የተጨዋቾቹ የመጫወት ስሜት ላይ ጫና ፈጥሮ ያላሰብነውን ጉዳት እግር ኳሱ እንዳያስተናግድ እሰጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ቀደም ሲል በተደረጉ ጠቅላላ ጉባኤዎች፣ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ምርጫ በአስመራጭ ኮሚቴነት እንዲሁም በተለያየ ተጨዋቹን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከፊት ትገኛለህ…ሸዋረጋ ምን ቤት ነው…?…ማንን ወክሎ ነው የሚናገረው…?ቢሉህ ምን መልስ አለህ…?
ሸዋረጋ፡- …ማለት አልገባኝም…?…(ግር እንደማለት እያለ)…እኔ ከዚህ በፊትም በጠቅላላ ጉባኤም በአስመራጭ ኮሚቴም ይሁን ተጨዋቹን በሚመለከት ጉዳይ የምገኘውና ድምፄን ከፍ አድርጌ የማሰማው በኢትዮጵያ ተጨዋቾች ማህበር ተወክዬ ነው፡፡ ከዚህ ሌላም ቀደም ሲል የተጨዋቹ እርዳታ ማህበር ፕሬዚዳንትም በመሆኔ ነው፡፡ ደሞም ይሄ ብቻ አይደለም ለእግር ኳሱ የደማሁ የቆሰልኩ ላቤን ጠብ አድርጌ ያፈሰስኩ ሰው ነኝ።በዚህም በእግር ኳሱ ላይ የሚሰራው ሸፍጥ ያንገበግበኛል የተጨዋቾች መጠቃት የእኔ መጠቃት በመሆኑ እጮሃለሁ ድምፄንም ከፍ አድርጌ አሰማለሁ።ማንም አይመለከተውም ሊለኝ አይችልም።እግር ኳሱን እያመሱት ያሉት እኮ የማይመለከታቸው ናቸው።
ሀትሪክ፡- በቅርቡ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር ከተቋቋመ በኋላ የኢትዮጵያ የተጨዋቾች ማህበር ከስሟል ጭራሸ በህይወት የለም በሚል የአንተና የማህበራችሁ ህጋዊነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አሉ እውነት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ማህበር ከስሟል…?
ሸዋረጋ፡- …እዚህ ላይ ሰዎች ስህተት ውስጥ የገቡ ይመስለኛል…፤…የኢትዮጵያ የተጨዋቾች ማህበር አልከሰመም…በህይወትም አለ።ምናልባት አክቲቭ አይደለም በተፈለገው ልክ አልተንቀሳቀስንም ከሆነ ልክ ነው፤ከዚህ ውጪ ግን ከስሟል ብሎ መናገር ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም በአለመሰራትና በከስሟል መካከል በጣም ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ይሄንን ማህበር እኮ ያቋቋሙት ወይም የመሠረቱት ደጉ ደበበ ከደቡብ፣ አሰግድ ተስፋዬ (ነፍሱን ይማረውና) ከድሬዳዋ፣ ፀጋዬ ኃይሉና ክበበው ገ/የስ ከአዲስ አበባ፣ አሊ ሚራህ ከአፋር እንዲሁም ዑመድ ኡኩሪ ከቤንሻንጉል ናቸው፤እነሱ ናቸው ቃለ ጉባኤ ተይዞ ያቋቋሙት፡፡ እነዚህ ታዋቂ ሰዎች ያቋቋሙትን ማህበር ከስሟል ማለት ለእኔ ክሬዲታቸውን (ልፋታቸውን) የመካድ ያህል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በቅርቡ የፕሮፌሽናል ተጨዋች ማህበር የሚል በይፋ ተቋቁሟል የእናንተ ነባሩ አለ፣ በአንድ ሀገር፣በአንድ እግር ኳስ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ሁለት የተለያዩ ማህበራት እያደረጋቸውም…?…ይሄስ ብዥታ አይፈጥርም…?
ሸዋረጋ፡- …ልክ ነህ በቅርቡ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጨዋች ማህበር የሚል ተቋቁሟል… ብዙው የእግር ኳስ ተጨዋች ስለማህበሩ ባይገባውም፡፡ አሁን አንተ በጥያቄህ ያነሳኸው የእኛም ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ በአንድ ሀገር ላይ እንዴት ሁለት ፍቃድ ሊሰጥ እንደቻለ አልገባኝም፤በአንድ ሀገር ውስጥ ለሁለት ማህበር ፍቃድ እንዴት ሊሰጥ ቻለ?የሚለውን በተለያየ መንገድ እያጣራሁ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …የእናንተም አሁን በቅርቡ የተቋቋመው ማህበርም ለመስራት የምታስቡት በአንድ ጉዳይ ያውም በተጨዋቾች ዙሪያ ነው፡፡ በተለያየ መንገድ ከመሮጥ ለምን በአንድ ላይ በምትሰሩበት ዙሪያ ላይ ተቀራርባችሁ ለመነጋገር አልሞከራችሁም…?
ሸዋረጋ፡- …እንዳልከው ነው አለማችን አንድ ነው፤ አንድ ሆነን መስራት በምንችልበት ዙሪያ በተለይ ከግርማ መስፍን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየተነጋገርን ነው፡፡ ሲገባኝም አንድ ሆነን መስራቱ ነው ስፖርቱንም ተጨዋቹንም የሚጠቅመው፡፡ ግን አንድ ሆነን ለመስራት በፊት የነበረውን ማህበር ደፍጥጦ ወይም የበፊቱ ከስሟል የሚል ታፔላ ለጥፎ አይደለም፡፡ የህግ ሰው ባልሆንም በፊት የነበረውን በታላላቅ ተጨቾች የቆመውን ማህበር ደፍጥጦ ፕሮፌሽናል የተጨዋቾች ማህበር ብሎ ማቋቋም አይቻልም፡፡ የነበረውን ደፍጥጦ እንለፍ ሲባል ነው ልዩነቱ የሚሰፋው፡፡ የእኛ ማህበር በተፈለገው መጠን አልተንቀሳቀሰም የሚለው እንጂ ከስሟል የሚለው አያስማማንም፡፡ ስለዚህ ማህበራችን ሕጋዊ ሰውነት ያለው ነው፤አላማችን አንድ በመሆኑ አብሮ በመስራቱ ላይ ችግር የለብንም፡ ከግርማ መስፍን ጋር በተደጋጋሚ አውርተናል፤እጅና ጓንት ሆነን አብረን የምንሰራበትን እንፈልግ ነው ያልኳቸው እነሱም ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውንና ችግር እንደሌለባቸው ገልጾልኛል፡፡ እዚህ ላይ ግን ሌላ አንድ መጨመር የምፈልገው ነገር አለ…..
ሀትሪክ፡-…ምን…. ?
ሸዋረጋ፡-…የፕሮፌሽናል የተጨዋችነት ማህበር መመስረቱ በጣም ደስ ይላል፤ማህበሩ እንዲመስረት ጥረት ያደረጉ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የእኛ ማህበርና የእነሱ ማህበር እጅና ጓንት ሆነን አብረን እንሰራ ሲባል መጥራትና መስተካከል ያለበት ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ አንድ የሚሰማ ሐሜት አለ፤ማህበሩን መስርተው ስልጣኑን እንደ ቅርጫ ተከፋፈሉት የሚል ሀሜት ስፖርት ቤተሰቡ ጋር ይሰማል። ማህበሩን መስርተህ ራስህ ፕሬዚዳንት፣ጋደኛህን ምክትል፣ሌላውን ፀሐፊ አድርገህ ስልጣን ከተቀራመትክ አላማውን መሣት ብቻ ሣይሆን ሌላ ጥርጣሬንም ያጭራል፡፡ ማህበሩን ለመመስረት የተነሣኸው ለተጨዋቹ አዝነህ፣ተቆርቋሪ ሆነህ አይደለም እንዴ? አላማው ያ ከሆነ ታዲያ አሁን ያሉትን (አክቲቮችን) የሚንቀሳቀሱ ተጨዋቾችን ወደ አመራርነት ለምን አናመጣቸውም? በግልፅ እንነጋገር ከተባለ 40 አመት ከጨዋታ የራቀን ሰው ያውም አሁን በአሰልጣኝነት ሙያ ላይ ያለን የአሰልጣኞች ማህበርን በአባልነት የሚያገለግልን ሰው እንዴት ፕሬዚዳንት አድርገህ ታስቀምጣለህ?…ከዚህ ውጪ ዋናውን የአመራርነት ቦታ የያዙት በሙሉ ከውጪ የመጡ ዲያስፖራ የሚባሉ ናቸው፤እነዚህ ተጨዋቾች ለሀገሪቱ አለፉም ሳይሆን እነሱ ብቻ ስልጣኑን ሲይዙት ማህበሩን የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር ሳይሆን የዲያስፖራዎች ማህበር የሚል ስያሜ እንዳያሰጠው እሰጋለሁ፤ስለዚህ ማህበሩ መቋቋሙ መልካም ቢሆንም ይበልጥ ተአማኒነት እንዲኖርው የተሻለ አቅም ላላቸውና በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ተጨዋቾች በዋናነነት እንዲሳተፉ እኛ ከኋላ ሆነን ብናግዛቸው መልካም ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግን እኛ ማህበሩን መስርተን እኛ ስልጣኑን ከተቀራመትነው ያሳማናል ብቻ ሣይሆን እምነትም ያሳጣናል፡፡