በመጪው ነሀሴ ወር ላይ በኮስታሪካ ለሚደረገው 10ኛው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የአለም ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የመጨረሻ ዙር ቀዳሚ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጋና አቻው 3 ለ 0 ተሸንፏል ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም በማጣሪያው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 7 ግቦችን በማስቆጠር የማጣሪያውም ጭምር ኮከብ ግብ አግቢ የሆነችውን ረድኤት አስረሳኸኝ በጉዳት ምክንያት ያጣት ሲሆን የወሳኟ አጥቂ በጨዋታው ላይ አለመሰለፍም በግልጽ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ።በጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በተወሰነ መልኩ ያለመረጋጋት ሁነቶች ተስተውለውባቸው ነበር ። ኳሶችን በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ፊት ለማድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶችም በቀላሉ በጋና ተከላካዮች ይከሽፉባቸው ነበር ።
በጋና ብሄራዊ ቡድን በኩል ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች እና ረጃጅም ኳሶች በመልሶ ማጥቃት የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ውጤታማ መሆን ችለዋል ። በጨዋታው የተደረገው ቀዳሚ ሙከራ በ22ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ግሬስ አኒማ ከሳጥን ውጪ አክርራ ወደ ግብ የላከችው ኳስ የግቡን አግዳሚ መልሶ ወጥቷል ።
በ25ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከመሳይ ተመስገን የተቀበለችውን ኳስ በሳጥኑ የግራ መስመር ይዛ በመግባት ወደ ግብ የቀነሰችውን ኳስ የጋና ተከላካዮች እንደምንም ተረባርበው ከግብ ክልል አርቀውታል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ጋናዎች በመልሶ ማጥቃት ይዘው የገቡትን ኳስ ሳማቱ አብዱላሂ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ስህተትን በመጠቀም የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠራለች ።
- ማሰታውቂያ -
በ36ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ የጋና ተከላካዮችን በመንጠቅ ለገነት ለማቀበል ያደረገችው ጥረት በጋና ተከላካይ የተባለሸ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቀዳሚውን ግብ ያስቆጠረችው ሳማቱ አብዱላሂ በግል ጥረቷ የኢትዮጵያ ተከላካዮች አልፋ ሁለተኛ ግብ ማከል ችላለች ። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ የጋናዋ አማካይ ሲሲኒያ ኒያማ ከሳጥን ውጪ የመታችው ኳስ በእየሩሳሌም መረብ ላይ አርፏል ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም በጋና ብሄራዊ ቡድን 3 ለ 0 መራነት ተጠናቀቀ ።በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ጋና የግብ ክልል መቅረብ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን ለግብ የቀረቡ አስቆጪ ኳሶችንም አምክነዋል ። የጋና ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአንፃሩ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በርከት ብለው በመገኘት በመጀመሪያ አጋማሽ ያስመዘገቡትን ውጤት ይዘው ለመውጣት ጥረቶችን አድርገዋል ።
60ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት ወደ ግብ የላከቸውን ግሩም ኳስ በግብ ጠባቂዋ ለጥቂት ተጨርፎ የማዕዘን ምት ሆኗል ። በ70ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይረው የገቡት ማዕድን ሀይሉ እና ገነት ኤርምያስ በግሩም ቅብብል ወደ ግብ ክልል ይዘው የሄደቱ ኳስ ለቱሪስት ለማ ቢደርስም ቱሪስት የመታችው ኳስ ጠንካራ ባለመሆኑ በቀላሉ በጋናዋ ግብ ጠባቂ ተይዟል ። እንዲሁም 84ኛው ደቂቃ ላይ በጋና ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ስህተት የተገኘውን ኳስ መሳይ ተመስገን አግኝታ አስቆጠረችው ተብሎ ሲጠበቅ ከግቡ አናት ባለይ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
ጨዋታውም በጋና ብሄራዊ ቡድን የ 3 ለ 0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆኖ የመልሱ ጨዋታ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ በጋና ኬፕ ኮስት ላይ ይደረጋል ።