በተስተካካይነት ተይዞ በነበረዉ እና በዛሬዉ ዕለት በተደረገዉ በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ጨዋታቸዉን አጠናቀዋል።
በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ጨዋታዉ የገቡት ባለሜዳዎቹ የጣና ሞገዶቹ በአምስተኛዉ ሳምንት ለገጣፎን ሁለት ለዜሮ ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾችን ለዉጥ አድርገው ወደ ሜዳ ሲገቡ በተቃራኒው አፄዎቹ በሳምንቱ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲረቱ ከተጠቀሙት የሁለት ተጫዋቾችን ለዉጥ አድርገዉ በ433 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካ የጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ባለሜዳዎቹ ባህርዳር ከተማዎች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ በሙከራ ረገድ የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል። በተቃራኒው አፄዎቹ በሙከራም ሆነ በሜዳ ላይ እንቅሰቃሴ ያን ያህል ነበሩ ማለት አይቻልም ነበር በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ማለት በሚቻል መልኩ የበላይነት የነበራቸዉ ባህርዳሮች የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በ10ኛዉ ደቂቃ ላይ ማድረግ ችለዋል። በዚህም ከፈቱዲን ጀማል የተሻገረለትን ኳስ የመስመር ተጫዋቹ ዱሬሳ ሹቤሳ እገፋ ሳጥን ዉስጥ ገብቶ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በሳማኪ ሚካኤል ቅልጥፍና ኳሷን ተቆጣጥሯታል።
በተደጋጋሚ ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች በድጋሚ ከደቂቃዎች በኋላ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም በ21ኛዉ ደቂቃ ላይ ይሁን እንዳሻዉ የአጥቂ አማካዩ ፉአድ ፈረጃ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን ቅጣት ምት ሰላምላክ ተገኝ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ የነበረ ቢሆንም የአፄዎቹ የግብ ዘብ እንደምንም ኳሷን መልሷታል።
ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያዉ አጋማሽ በንፅፅር ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ የተመለሱት አፄዎቹ በእንቅስቃሴም ሆነ በሙከራ ረገድ ተሻሽለዉ መመለሳቸውን ተገንዝበናል። በተለይ በ52ኛዉ ደቂቃ ላይ ጋይራ ዩፍ ከግራ መስመር ተከላካዩ ሔኖክ የቀማዉን ኳስ ለሽመክት አቀብሎት የመስመር ተጫዋቹ ኳሷን ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የጣና ሞገዶቹ ግብ ጠባቂዉ እንደምንም ኳሷን አዉጥቷታል።
ናትናኤል ዘለቀን እና ፍቃዱ አለሙን በጋይራ ዩፍ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ቀይረዉ ወደ ሜዳ ያስገቡት አፄዎቹ በተለይ የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በመጣ ቁጥር በቀኝ መስመር እና በሜዳዉ የመሐል ክፍል ላይ ይጣሉ በነበሩ ኳሶች የግብ ዕድል ለማግኘት ሞክረዉ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸዉ ቀርተዋል።
በጨዋታዉ 70ኛ ደቂቃ ላይ አፄዎቹ ትልቅ የግብ ዕድል ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህም ያሬድ ባየ የፊት መስመር አጥቂዉ ፍቃዱ አለሙ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት የአፄዎቹ አምበል አስቻለዉ ታመነ ቢመታም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በሁለቱም ቡድኖች ረገድ ጨዋታዉን ለማሸነፍ ካላቸዉ ጉጉት የተነሳ በሚመስል መልኩ እስከ ጨዋታዉ መጠናቀቂያ ድረስ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ሁለቱም ቡድኖች ኳስ እና መረብን ማዋሀድ ሳይችሉ ቀርቶ ጨዋታዉ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።