“እኔን ለማስፈረም ለሚፈልጉኝ ክለቦች በሬ ክፍት ነው”
“በሀምበሪቾ ደስተኛ ነኝ ግን ደመወዝ የለም ጥቅማ ጥቅምም የለም ቤተሰቤን መምራት ከበደኝ”
ቴዎድሮስ በቀለ
/ሀምበሪቾ ዱራሜ/
መከላከያ 4 አመት፣ አዳማ ከተማ 2 አመት ፣ሀድያ ሆሳዕና፣ ኢትዮጵያ ቡናና ኢትዮጵያ መድን አንድ አንድ አመት ተጫውቷል..ዘንድሮ ደግሞ ለአምበሪቾ እየተጫወተ ይገኛል ቴዎድሮስ በቀለ …..። በአምበሪቾ ቀሪ 6 ወር ቢኖረውም በደመወዝና ከጥቅማጥቅም አለመከፈል ጋር ተያይዞ በሁለተኛው ዙር የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት የክለብ ለውጥ ለማድረግ እያሰበ መሆኑን ተናግሯል።በመሃል ተከላካይነት ሚና እየተጫወተ ያለው ቴዎድሮስ ከሀትሪክ ድረ ገጹ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ባደረገው ቆይታ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።
ሀትሪክ:- ተከላካይ የመሆን ፍላጎት እንዴት ሊያድርብህ ቻለ..?
- ማሰታውቂያ -
ቴዎድሮስ:- መጀመሪያ አጫወት የነበረው የመስመር ተከላካይ ሆኜ ነበር ከዚያ በኋላ ነው አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ መከላከያን እያሰለጠነ እያለ ከሰበታ ከተማ ወስዶኝ የመሃል ተከላካይ ያደረገኝ.. በተለየ መንገድ መርጨው ሳይሆን የህይወት ጉዞ ያመጣው ምርጫ ነው
ሀትሪክ:- ጎል ማስቆጠር ውስጥ ያለው ደስታ አልሳበህም ..?
ቴዎድሮስ:- መከላከልም የገባ ግብ ማዳንም ደስታ አለውኮ በዚህ ደስ ይለኛል ቦታውን በተለየ መንገድም አይቼው አይደለም ግን ውስጤ መረጠው የአሰልጣኙ ምርጫ ደግሞ መሃል ሆነ አሁን ተመችቶኛል…የመሃል ተከላካይ ቦታ መጫወት ሪስክ አለው ለትላልቅ ቡድኖች መጫወት በበርካታ ደጋፊ መታጀቡ ሲመጣ ጫናው በይበልጥ ተከላካይ ክፍሉ ላይ ይሆናል… በኛ ሀገር ደግሞ ይብሳል ግብ ጠባቂና ተከላካይ ላይ ያለው ጫና ይሰፋል። ጫና ውስጥ ብሆንም ተቀብሎ መሄድ የግድ ይላል
ሀትሪክ:- ቲየሪ ኦነሪ ሲባል አርሴን ቬንገር ይታወሳሉ ለቴዲስ ማን ይጠራል..?
ቴዎድሮስ:- በርካታ አሰልጣኞች አሰልጥነውኛል ያሰለጠኑኝን በሙሉ አመሰግናለሁ… ከዚያ ውጪ በተጨዋችነት ዘመኔ አሰልጣኝ ገ/መድህን ሃይሌ፣ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ትልቅ ቦታ አላቸው ሶስቱንም በዚሀሰ አጋጣሚ አመሰግናለሁ።
ሀትሪክ:- ፕሪሚየር ሊጉን እንዴት አገኘኧው..?
ቴዎድሮስ:- ሊጉ ጠንካራ የሚባል ነው። ጥሩ ፉክክር አለበት ሲኒየሮቹ ከታዳጊዎቹ ጋር ተቀላቅለው የሚፋለሙበት ሊግ ነው ትልቅም ለውጥ አለው
ሀትሪክ:-የዋንጫ ፉክክሩን እንዴት አየኧው …?
ቴዎድሮስ:- ነጥቡ ተቀራራቢ ነው እንደ ቀድሞ አይደለም አንድ ቡድን ብቻ የበላይ የሚሆንበት አይመስለኝም አራት ወይም ሶስት ጨዋታ እስኪቀረው ድረስ አሸናፊው ላይታወቅ ይችላል ብዬ አስባለሁ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መቻልና ባህርዳር ከተማ ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉ ስለ ዋንጫ የሚፋለሙበት ሊግ ሆኗል ማን ያሸንፋል የሚለውን በቀጣይ 18 ጨዋታዎች ማየት ነው
ሀትሪክ:- ከኢትዮጵያ መድን ስትለቅ ሳይታሰብ ድንገት ነው …ምክንያቱ ምንድነው…?
ቴዎድሮስ:- እውነት ነው ድንገት ነው ሳልጠብቅ ዝግጅት ላይ እያለሁ አሰልጣኙ እንዳልፈለገኝ የተነገረኝ… 24 ጨዋታ በጥሩ አቋም ስለተጫወትኩ ስንብቱን አልጠበኩም ነበር ያው ግን ቀሪ ኮንትራት ቢኖረኝም የዝውውር መስኮቱ ሊጠናቀቅ ሲል ነው ክለብ ፈልግ ያሉኝ.. .. ወቅቱ ትንሽ ከበድ ያለ ጊዜ ነበር የአሰልጣኜኝ ቃል አከብራለሁ በሰላም ነው የተለያየነው … ጊዜው ከባድ ስለነበር አማራጭ አጥቼ ቤቴ ልቀመጥ ስል ነው የሀምበሪቾ ዱራሜ አመራሮች አነጋግረው ያስፈረሙኝ በዚህ አጋጣሚ አመሰግናቸዋለሁ። በዚያ ላይ አስቀድሞ ሌሎች ክለቦች ፈልገውኝ ለአሰልጣኝ ገብረ መድህንና ለመድን ክብር ስለነበረኝ አልፈልግም ብያለሁ እንደዚያም ሆኖ በስምምነት ነው የተለያየነው ለወደፊቱ በእግርኳስ የሚፈጠር ነገር አይታወቅም ነገም ተመልሰን ልንገናኝ ስለምችል በሰላም ነው የተለያየነው ያለው ሁኔታ ይህ ነው
ሀትሪክ:- መድንን ለቀህ ለአምበሪቾ የመፈረም ሂደቱ ምን ይመስላል..?
ቴዎድሮስ:- መድን 3ኛ ሆኖ ጨረሰ እኔም በ24 ጨዋታ ተካፍዬ ጥሩ ግልጋሎት ሰጥቼ ወደ ቤቴ ስሄድ ስሜት ይጎዳል በግሌ ምንም የባህሪ ችግር የለብኝም.. የዲሲፕሊን ችግርም እንደዛሁ የምንም ሱስ ተጠቂ አይደለሁም በእምነቴና በመልካም አኗኗር የምታወቅ ነኝ ያም ሆኖ በወቅቱ የሀምበሪቾዎች እድል ሲመጣ በደስታ ተቀብዬ ፈረምኩ
ሀትሪክ:- ከጨዋታም ርቀህ ነበር አይደል ..?
ቴዎድሮስ:- አዎ በጥሩ አቋም ነው ያለሁት… በሀምበሪቾም ደስተኛ ነኝ ግን ደመወዝ የለም ጥቅማ ጥቅምም የለም ቤተሰቤን መምራት ከበደኝ …ኳስ መጫወት ስራዬ ነው ስራዬ ግን ክፍያ የለውምና በስነ ልቡና ተጎዳሁ… አዕምሮዬ በጥሩ ሁኔታ እንድጫወት አላደረገኝም ይሄ ነው ምክንያቱ እንጂ በጥሩ አቋም በመልካም ጤንነት ላይ እገኛለሁ..
ሀትሪክ :- ዋናው የመልቀቅ ፍላጎትህ መነሻ ምንድነው ..? ተፈቀደልህ..?
ቴዎድሮስ:- የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም መብቶች አልተከበሩም በርግጥ ተቸግረው እንደሆነ እረዳለሁ ቤተሰብ አለኝ ስራዬ እግርኳስ ነው ተጫወቼ በማገኘው ነው የማስተዳድራቸው ግን ደመወዝ ከተከፈለ ቆየና ተቸገርኩ ፈጣን ምላሽ ያስፈልገኛኛል አመራሮቹን አነጋግሬያቸዋለሁ ጥሩ ግንኙነት ነው ያለኝ በክለቡ ደስተኛ ነበርኩ ነገር ግን ቤተሰቤን ለማስተዳደር በመቸገሬ መለያየቱና ሌላ ክለብ ለመፈለግ ተገድጃለሁ ..ክለቡም ይህን ተረድቶ ፈቅዶልኛል..
ሀትሪክ::- ለሌሎች ፈላጊ ክለቦች ምን ማለት ትፈልጋለህ…?
ቴዎድሮስ:- ቀድመው ሲፈልጉኝ የነበሩትም ክለቦች ይሁኑ ሌሎች ክለቦች ከፈለጉኝ በሬ ክፍት ነው በመልካም ጤንነት በጥሩ አቋም ላይ እገኛለሁ ነገሮች ከተስተካከሉ መብቴ ከተከበረ በሁለተኛው ዙር ለመጫወት ዝግጁ ነኝ ለመነጋገር የሚፈልግ እኔን ማስፈረም የሚፈልግ ካለ ያለኝን የሚጠበቅብኝን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ለማለት እፈልጋለሁ
ሀትሪክ– የመጨረሻ ቃል..?
ቴዎድሮስ :- ለአምበሪቾ ዱራሜ አመራሮችና አሰልጣኞች እንዲሁም ደጋፊዎች ለእስካሁኑ ቆይታችን ለሰጡንም ድጋፍ ማመስገን እፈልጋለሁ።