” የቡድን ህብረታችን እና አንድነታችን ለዚህ ክብር አብቅቶናል ”
” በቀጣይ በሊጉ ጠንካራውን ሀምበሪቾ ዱራሜ ጠብቁ ” የሻምፒዮኖቹ ግብ ጠባቂ አስራት ሚሻሞ
ትውልድ እና እድገቱ ሆሳዕና ከተማ ነዉ ከልጅነቱ አንስቶ ለእግርኳስ የተለየ ፍቅር የነበረዉ ፤ በዚህም የሚወደውን እግርኳስ ገና በታዳጊነቱ በሆሳዕና ከተማ ፕሮጀክት አንድ ብሎ ጀምሮ በሀድያ ሆሳዕና ዋና ቡድንም መጫወት ችሏል።
በዚህ መንገድ የእግርኳስ ሂወቱን የጀመረዉ የግብ ዘቡ አስራት ሚሻሞ በወላይታ ዲቻ እና የከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊ ክለብ ሺንሽቾ ከተማ የተወሰኑ አመታትን ካሳለፈ በኋላም ከቀናት በፊት ወደ ፕሪሚየር ሊግ መቀላቀል የቻለውን ሀምበሪቾ ዱራሜ ዳግም ከ2014 የውድድር አመት አጋማሽ አንስቶ በመቀላቀል ለክለቡ የፕሪሚየር ሊግ የተሳትፎ ጉዞም ከፍተኛ ሚናን እንደተወጣ በርካቶች ይመሰክሩለታል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም ለሀምበሪቾ ዱራሜ ፕሪምየር ሊግ መቀላቀል ዋነኛዉ ነገር የቡድን አጋሮቹ እና አሰልጣኞቹ የነበራቸዉ ህብረት ትልቁ ነገር እንደሆነ የሚናገረው ግብ ጠባቂዉ አስራት ሚሻሞ ስለ ልጅነት የእግርኳስ ሂወቱ ፣ ስለ ክለቡ ሀምበሪቾ ዱራሜ እንዲሁም ለፕሪሚየር ሊጉ ስላበቃቸዉ ዋነኛዉ ሚስጥር እና ለእንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል ስላለዉ የተለየ ፍቅር ከሀትሪኩ ጋዜጠኛ ኤርሚያስ ምስጋናው ጋር ተከታዩን ቆይታን አድርጓል።
ሀትሪክ :- በመጀመሪያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ አመሰግናለሁ ።
አስራት :- ምንም አይደል እኔም አመሰግናለሁ ።
ሀትሪክ :- እንግዲህ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማደጋችሁ ደግሞ እንኳን ደስ ያለህ ለማለትም እወዳለሁ ።
አስራት :- በጣም አመሰግናለሁ እንኳን አብሮ ደስ አለን።
ሀትሪክ :- የውድድር አመቱ እንዴት አለፈ ?
አስራት :- በእርግጥ ሀምበሪቾ ዱራሜ የቀድሞ ክለቤ ቢሆንም ዳግም ወደ ክለቡ የተመለስኩት ግን ከ2014 የውድድር አመት አጋማሽ አንስቶ ነዉ ፤ በነዚህ ጊዜያት ደግሞ ባለመሸነፍ ጉዞ ረዘም ያለ ጊዜን ማሳለፍ ችለናል ። በጣም ጠንካራ የቡድን ስብስብ ነበረን አንድ እና አንድ አላማችን ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀል ነበር በዚህም ጠንክረን ሰርተን ያም ነገር ተሳክቶልን ወደ ሊጉ ማደግ ችለናል ።
ሀትሪክ :- በምድባችሁ በተለይ ከገላን ከተማ ጠንካራ የሚባል ፉክክር ገጥሟችሁ ነበር እዚህ ላይ ምን ሀሳብ አለህ ?
አስራት :- ልክ ነህ እንደሚታወቀው በከፍተኛ ሊግ ስትወዳደር በርከት ያሉ ችግሮች አሉ ከዳኛ ጋር ተያይዞ ፣ ከሜዳ ጋር ተያይዞ እና ከሌሎች ነገሮች አንፃርም በርከት ያሉ ችግሮች ያሉበት ውድድር ነዉ። በተለይ በከፍተኛ ሊጉ ወደ ላይ መውጣትም እንዲሁም ወደ ታች መውረድም የማይፈልጉ ጠንካ ክለቦች አሉ እነርሱን መግጠም በራሱ ከባድ ነበር ፤ ከዚያ ውጭ ግን እንዳነሳኸዉ ከገላን ከተማ ጥንካራ ፉክክር ገጥሞን የነበረ ቢሆንም እግዚአብሔር ረድቶን ራሱን ገላንን ጭምር አሸንፈን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደግ ችለናል።ሀትሪክ :- በውድድር አመቱ በነበራችሁ ጉዞ የማትረሳው ጨዋታ ካለ ወይም የፈተናችሁ ቡድን ካለ ?
አስራት :- ልክ ነህ ብዙ የሚፈትኑ ቡድኖች እንዲሁም ጨዋታዎች ይኖራሉ ፤ ግን በተለይ በሁለተኛዉ ዙር ከአርሲ ነገሌ እና ገላን ከተማ ቀላል የማይባል ፉክክር እንደገጠመን መናገር እችላለሁ።
ሀትሪክ :- ለዚህ ውጤት ያበቃችሁ የቡድናችሁ ጥንካሬ ምን ይሆን ?
አስራት :- የቡድናችን ዋነኛዉ ጥንካሪ የኮችንግ ስታፉ ብቃት እንዲሁም የእኛም የተጫዋቾች ጠንክሮ መስራት ነዉ ፤ ይሄ ደግሞ ለዚህ ውጤት አብቅቶናል ብየ አስባለሁ ።
ሀትሪክ :- በአመቱ በጣም የተለየ ነበር ወይም የእርሱ መኖር ለዚህ አብቅቶናል የምትለዉ ተጫዋች ካለ ?
አስራት :- አይ እንደዛ እንኳን አልልህም እኛ እንደቡድን በጣም ጣንካራ ሰራተኞች ነበርን ፤ በዚህም በግል ሳይሆን በቡድን ሰርተን ነዉ ይሄንን ነገር ማሳካት የቻልነው ።
ሀትሪክ :- ስለ አሰልጣኛችሁ ምን አስተያየት አለህ ?
አስራት :- አሰልጣኛችን በጣም ልምድ ያለዉ ትልቅ አቅም ያለዉ አሰልጣኝ ነዉ ፤ ለእያንዳንዱ ጨዋታ በጣም ያዘጋጀን ነበር ልምምድ ሜዳም ላይ የተለያዩ አይነት ታክቲኮችን ያሰራን ስለነበር በዚህም ወደ ሜዳ ስንገባ ደግሞ ጨዋታዎች በጣም ይቀሉን ነበር አጠቃላይ ወደ ሊጉ ለማደጋችን የአሰልጣኛችን ድርሻ ዋነኛዉ እና ቀዳሚዉ ነዉ ማለት እችላለሁ ።
ሀትሪክ :- የክለቡን ደጋፊዎች እንዴት ትገልፃቸዋለህ ?
አስራት :- በእውነት ስለ እነርሱ ለመናገር ቃል ያጥረኛል ፤ ደጋፊዎች በሌሊት ተነስተው ረጃጅም ጉዞዎችን አድርገዉ ሲደግፉን ሲያበረታቱን ነበር ወደ ሊጉ እንድንገባም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርገዉልናል ብየ አስባለሁ ፤ በአጭሩ ለእኔ ደጋፊዎቹ የክለቡ የጀርባ አጥንት ናቸዉ ብቻ ነዉ ማለት የምችለው ።
ሀትሪክ :- እስኪ ወደ አንተ የግል ጥያቄዎች ልምጣ እና በቀጣይ በእግርኳስ ሂወትህ ምን ታስባለህ ?
አስራት :- ያዉ ብዙ ነገር አስባለሁ ግን እግዚአብሔር ቢረዳኝ ወደ ፊት የተሻለ ነገር ሰርቼ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሀገሬን ባገለግል በጣም ደስ ይለኛል።
ሀትሪክ :- በቀጣይ በሊጉ ምን አይነት ሀምበሪቾ እንጠብቅ ?
አስራት :- ያዉ አንግዲህ ክለባችን ከዚህ በኋላ ብዙ የቤት ስራ ይጠብቀዋል ብየ አስባለሁ ፤ በዚህም ጠንካራ ስራ ከሰራን በሊጉም ጠንካራ ሁነን እንቀጥላለን ብየ ነዉ የማስበዉ ።
ሀትሪክ :- አንተ እግርኳስን እንድትወድ ያደረገህ ወይም አርአያየ ነዉ የምትለዉ ተጫዋች ማን ይሆን ?
አስራት :- እግርኳስን እንድወድ ያደረገኝ ወላጅ አባቴ ነዉ ፤ አባቴ የድሮ ኳስ ተጫዋች ነበር እና በእርሱ ፍላጎት እና ምክርም ነዉ እኔ ወደ እግርኳስ የገባሁት አርአያየ የምለውም እርሱን ነዉ ።
ሀትሪክ :- በቀጣይ ምን ታስባለህ ?
አስራት :- ያዉ እንግዲህ እኔ የማስበዉ በግሌ በጣም ጠንክሬ ሰርቼ በሊጉ ከሚገኙ ተጠቃሽ ግብ ጠባቂዎች ተርታ ተመድቤ ሀገሬን ማገልገል እና የብሔራዊ ቡድንም ተመራጭ ግብ ጠባቂም መሆን ነዉ ዋነኛዉ ፍላጎቴ ።
ሀትሪክ :- ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከውጭ የየትኛዉ ክለብ ደጋፊ ነህ ?
አስራት :- ከሀገር ውስጥ የራሴ ክለብ ሀምበሪቾ ዱራሜ ደጋፊ ነኝ ፤ ከውጭ ደግሞ የሊቨርፑል ደጋፊ ነኝ ግብ ጠባቂውን አሊሰን ቤከርንም በጣም ነዉ የምወደው።
ሀትሪክ :- ከምግብ ምን ትወዳለህ ?
አስራት :- ከምግብ እንኳን ለፓስታ የተለየ ፍቅር አለኝ ፤ ፓስታ በጣም እወዳለሁ።
ሀትሪክ :- በመጨረሻም ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ ?
አስራት :- በመጨረሻም እንግዲህ ለዚህ ክብር እንድበቃ የረዳኝን እግዚአብሔር አምላክ ነዉ ተመስገን ማለት የምፈልገው።
ሀትሪክ :- አመሰግናለሁ ፤
አስራት :- እኔም በጣም አመሰግናለሁ ።