ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን አጠናክሮ ያስቀጠለበትን ዉጤት ለገጣፎ ለገዳዲን 2-1 በማሸነፍ አስመዝግቧል።
ቀዝቀዝ ባለ እና ባልተረጋጋ አጨዋወት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የጀመረ ሲሆን ፈረሰኞቹ ገና በ16ኛዉ ደቂቃ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረላቸዉ ጎል ገና በጠዋቱ መሪ መሆን ችለዉ ጨዋታው 1-0 በሆነ ዉጤት ቀጥሏል።
ለገጣፎ ለገዳዲዎች ጎሏ ከተቆጠረችባለዉ በኋላ ወደ ጊዮርጊሶች የግብ ክልል በመድረስ ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ለአብነትም ኢብሳ ፍቃዱ አከታትሎ የሞከራቸዉ ለጎልነት የቀረቡ ኳሶች ተጠቃሽ ናቸዉ።
- ማሰታውቂያ -
ከእዛ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለጎል የቀረቡ ኳሶች ሙከራ ሳይደረገ በተቀዛቀዘ አጨዋወት ጨዋታዉ የቀጠለ ሲሆን ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት የመጀመሪያው አጋማሽ በጊዮርጊስ መሪነት 1-0 ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ካርሎስን እና ሱራፌልን በመቀየር ወደ ሜዳ ይዘዉ የገቡ ሲሆን አጥቅተዉ የጎል እድል ለመፍጠር የተጫወቱ ቢሆንም ነገር ግን ሳይሳካላቸዉ ቀርቶ በተቃራኒዉ ጊዮርጊሶች ጥንቃቄ የተሞላበትን አጨዋወትን ሲከተሉ የነበረ ሲሆን በ58ኛዉ ደቂቃ ሀይደር ሸረፋ ለጊዮርጊሶች ሁለተኛዋን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታዉ ወደ 2-0 አመራ።
ጨዋታዉ ወደ 2-0 ካመራ በኋላ ከቀድሞዉ ይልቅ መነቃቃት የተስተዋለበት ሲሆን ለገጣፎዎች በተደጋጋሚ ለጎል የቀረበ ኳስ በመሞከር የጊዮርጊስን የግብ ዘብ ባህሩ ነጋሽን ሲፈትኑ ነበር።
ጨዋታዉ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ ፉክክር እየተደረገበት ተጨማሪ የጎል እድል ሳይፈጠር እስከ ሁለተኛዉ አጋማሽ መጠናቀቂያ ድረስ ቢደርስም ባለቀ ሰአት በጨዋታዉ መገባደጃ ላይ ኢባሳ በፍቃዱ ለለገጣፎ ከሽንፈት ያላዳነችዉን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታዉ 2-1 በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታዩ ባህርዳር ከነማ ጋር ያለዉን የነጥብ ልዩነት ወደ 8 ማስፋት ችሏል።