በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚውን አርባምንጭ ከተማ አንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ተመጣጣኝ የሚባል የሜዳ ላይ ፉክክር ባስመለከተዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያ 25 ያህል ደቂቃዎች አዞዎቹ በመስመር በኩል ያመዘነ የጨዋታ መንገድን ሲከተሉ በተቃራኒው ፈረሰኞቹ ደግሞ በሜዳዉ የመሐል ክፍል ላይ ብልጫ በመዉሰድ የጨዋታውን የበላይነት ለመወለሰድ ሲጥሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በተለይ የአዞዎቹ የፊት መስመር አጥቂ አህመድ ሁሴን በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ እንደምንም ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ግብ የሞከራት ኳስ የመጀመሪያዋ ድንቅ ሙከራ ነበረች።
በተደጋጋሚ በተመስገን ደረሰ ፣ አህመድ ሁሴን እና ኤሪክ ካፓይቶ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አዞዎቹ ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በተመሳሳይ ረሰኞቹም ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በአጋማሹ ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ግን ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም ነበር ፤ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸዉ በፊት ግን ግን ፈረሰኞቹ ድንቅ የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለዉ ነበር በዚህም ከአማካዩ ዳዊት ተፈራ የተሻገረለትን ኳስ አጥቂዉ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ቀጥታ ወደ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
ከዕረፍት መልስ በንፅፅር ተሽለው የተመለሱት ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ አጋጣሚ በተለይ በፊት መስመር አጥቂዉ አጎሮ ምክንያት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ ሲሆን ፤ በ61ኛዉ ደቂቃ ላይም በዚሁ አጥቂ የግል ብቃት ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ማግኘት ችሏል። በዚህም ከቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ ማጥቃት በኩል ሄኖክ አዱኛ ያቀበለዉን ኳስ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ከሳጥን ዉጭ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ፈረሰኞቹ መሪ መሆን የሚችሉበትን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በአመዛኙ ጥንቃቄ ላይ መሰረት ያደረገን የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲከተሉ በተቃራኒው አዞዎቹ የአቻነት ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታዉ በቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ዉጤቱን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ48 ነጥቦች በመሪነት ስፍራዉ ሲቀመጥ በተቃራኒው በምሽቱ ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገደዉ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በ22 ነጥቦች አስራ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።