በመሸሻ ወልዴ
የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም
በክለባቸው የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ
የማንሳት ተስፋ ዙሪያና በሌሎች ተያያዥ
ጥያቄዎች ላይ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ 6 ጅማ
አባጅፋር 1 የሚል ውጤት በጎንደሩ
ፋሲልደስ ስታዲየም ተመዝግቧል?
የጨዋታው መልክ ምን ይመስል ነበር?
በድሉስ ምን ተሰማህ?
ሙጂብ፡- ጅማ አባጅፋርን በሰፊ ግብ
ያሸነፍንበት የእሁዱ ጨዋታ በሜዳ ላይ
በነበረው እንቅስቃሴ እኛ ከተጋጣሚያችን
ተሽለን እና ጥሩም በመንቀሳቀስ
የተጫወትንበት ሲሆን የተገኘው ድልም
ክለባችንን የሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ
በመሸነፉ ምክንያት እኛን ለመጀመሪያ
ጊዜ በመሪነት ደረጃ ላይ እንድንቀመጥ
ስላደረገን በጣም ነው ያስደሰተን፡፡
ሀትሪክ፡- ያሸነፋችሁት የዓምናውን
ሻምፒዮና ከመሆኑ አንፃር ጎሉ ግን በዛ?
ሙጂብ፡- የጅማ አባጅፋር ጋር በነበረን
ጨዋታ እኛ ያስቆጠርነው ስድስት ጎል በሜዳ
ላይ ከነበረን እንቅስቃሴ አንፃር ፈፅሞ
አልበዛም፤ ጅማን በሰፊ ግብ ያሸነፍነው
ቡድናችን ለዋንጫ ከመጫወቱ አንፃር በጣም
ጥሩ ሆኖና ተጭኖ ስለተጫወተ ነበር፤ ከዛ
ውጪም እነሱ ተከላክለው እና በመልሶ
ማጥቃት ሊጫወቱ ያሰቡትን እንቅስቃሴ
ስላከሸፍንባቸውም ጨዋታውን በሰፊ ግብ
ልናሸንፍ በቅተናል፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ጅማ አባጅፋርን
ሲያሸንፍ በጎንደሩ የፋሲለደስ ስታድየም
የነበረው ድባብ ምን ይመስል ነበር?
ሙጂብ፡- የደጋፊዎቻችን ድባብ በውጤታችን በመደሰት
እና የጨዋታው ወቅት ላይም ለእኛ
የሐዋሳ ከተማ ቡድን መቐለን
እየመራ መሆኑን ለማመልከት ሐዋሳ
እያሉ ይጨፍሩም ስለነበር ያን
ስናደምጥ በጨዋታው ላይ ከፍተኛ
ተነሳሽነትንም ይፈጥሩልን ስለነበርም
አጠቃላይ ድባቡ በጣም ነበር ያምር
እና ያስደስትም የነበረው፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ
በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ፊት ነው
የተሸነፈው፤ ይሄን ውጤትና በዚህ
ሳምንትስ ውስጥ መሪ እንሆናለን
ብላችሁ ጠብቃችሁ ነበር ?
ሙጂብ፡- በፍፁም፤ እንዴት
ብለን ነው የምንጠብቀው፤ መቐለ 70
እንደርታ በሜዳው ላይ ካለው ከፍተኛ
የማሸነፍ ሪከርዱ አንፃር ነጥብ ይጥላል
ብለን አልገመትንም ነበር፤ ግን
እግር ኳስ ሆነና ተሸነፈ፤ እኛ ደግሞ
ለዋንጫው ባለቤትነት የምንጫወት
ስለነበርን ጅማን በማሸነፍ አሁን ላይ
መሪ ሆንን፤ የመሪነቱ አናት ላይ
እንቀመጣለን ያልነው በዚህ ሳምንት
አልነበረም፤ ኳስ እንግዲህ እንዲህ
ነው፤ የእኛ ጥሩ መሆን ቀዳሚው ቦታ
ላይ አስቀምጦናል፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር
ሊግ ዋንጫን ማን ያነሳል? ፋሲል
ከነማ? መቐለ 70 እንደርታ? ወይንስ
ሲዳማ ቡና?
ሙጂብ፡- የሊግ ውድድሩ
ሊጠናቀቅ የአምስት ሳምንታት
ጨዋታዎች ይቀራሉ፤ አሁን
ላይ ሶስታችንም ቡድኖች ካለን
የነጥብ ቅርርቦሽ አንፃር ይሄ ቡድን
ሻምፒዮና ይሆናል ብሎ መገመት
ከባድ ይሆንብኛል፤ የሊግ ውድድሩን
በአሸናፊነት የሚያጠናቅቀው ቡድን
በቀሪዎቹ ግጥሚያዎች ጥሩ
ብቃቱን የሚያሳይ እና ጨዋታዎቹን
የሚያሸንፈው ቡድን ነው ያኔም
ባለድሉ ችታወቃል፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ይሄን
ዋንጫ የማንሳት ዕድሉን ለማሳካት
በቀጣዮቹ አምስት ጨዋታዎች በምን
መልኩ ይቀርባል?
ሙጂብ፡- የፕሪምየር ሊግ
ውድድራችንን ልናጠናቅቅ በሜዳችን
ሁለት ከሜዳችን ውጪ ሶስት
ጨዋታዎች ይቀሩታል፤ በእነዚህ
ግጥሚያዎች የውድድሩ አሸናፊ
ለመሆን ቀሪዎቹን 5 ግጥሚያዎች
ማሸነፍ የግድ ስለሚል እኛም
ለእነዚህ ጨዋታዎች ከፍተኛ ትኩረት
በመስጠት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ
ሻምፒዮና ለመሆን ከፍተኛ ጥረትን
እናደርጋለን፡፡
ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ 12
ግቦችን አስቆጥረህ ለኮከብ ግብ
አግቢነቱም እየተፎካከር ይገኛል፡
፡ ኮከብ ግብ አግቢነቱን የምታገኝ
ይመስልሀል?
ሙጂብ፡- አሁን ላይ እኔን
የሚያስጨንቀኝ ኮከብ ግብ አግቢ
ስለመሆን ሳይሆን ቡድኔ እንዴት
አድርጎ የሊጉ ሻምፒዮና ይሆናል
በሚል እሳቤ ላይ ነው የምገኘው፡
፡ ዋናው ፍላጎቴና ሕልሜ ፋሲልን
ለመጀመሪያ ጊዜ ለፕሪምየር ሊጉ
ሻምፒዮንነት ክብር ማብቃት ነውና
በዛ ላይ ነው ትኩረትን አድርጌ
የምገኘው፡፡
ሀትሪክ፡- የረመዳን ጾምን
በመጾም ነው 4 ጎሎችን በጅማ
አባጅፋር ላይ ያስቆጠርከው፡፡ በዚህ
መልኩ ተጫውቶ ጎል ማስቆጠር
አይከብድም?
ሙጂብ፡- ከባድ ቢሆንም ጾሙ
ብርታት ነው የሆነኝ፡፡ ውስጤ ላይ
ያለው እምነትም ኃይል ስለሆነኝ በዚህ
መልኩ በርካታ ግቦችን ላስቆጥር
ችያለሁ፡፡