በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ቀዳሚ ጨዋታ የአምና ሻምፕየኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልቂጤ ከተማን 4 – 1 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል ።
በጨዋታው በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ሄኖክ አዱኛ ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱህ ፣ አማኑኤል ተርፉ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ ፣ ዳዊት ተፈራ ፣ አቤል ያለው ፣ ተገኑ ተሾመና አማኑኤል ኤርቦ በምርጥ 11 ተካተዋል ።
በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ወልቂጤ ከተማ በኩል መሳይ አያኖ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ በቃሉ ገነነ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ ፣ ዳንኤል ደምሴ ፣ ጌቱ ሀይለማርያም ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ አቡበከር ሳኒና ስንታየሁ መንግስቱ በመጀመሪያው አሰላለፍ ተካተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ገና ከጅምሩ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጎል ለማስቆጠር ወደ ፊት ለፊት አዘንብሎ በመጫወት የተሻሉ የነበረ ሲሆን ወልቂጤ ከተማዎችም በበኩላቸዉ ለጎል የቀረበ ኳስ መሞከር ችለዋል።
ጨዋታዉ በተጀመረ በ20ኛዉ ደቂቃ የወልቂጤዉ ዳንኤል ደምሴ በእራሱ ላይ ጎል አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪ መሆን ችለዋል።
ጨዋታዉ በፈረሰኞቹ የ1 – 0 መሪነት ለ11 ደቂቃ ያህል ብቻ መቀጠል የቻለ ሲሆን የወልቂጤ ከተማው ስንታየሁ መንግሥቱ የቅዱስ ጊዮርጊስን ስህተት በመጠቀም በ31ኛዉ ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ የጨዋታውን ውጤት ወደ አቻት መልሶታል።
ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል እምብዛም ለጎል የቀረበ ሙከራ ሳይደረግ የመጀመሪያው አጋማሽ በ1-1 አቻ ዉጤት ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመጀመሪያው አጋማሽ በብዙ ረገድ የተሻለ አጨዋወት ይዘዉ ወደ ሜዳ የቀረቡ ሲሆን ገና ከጅምሩ የወልቂጤዎቹን የግብ ክልል የፈተኑ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
ፈረሰኞቹ ተደጋጋሚ ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ ከቻሉ በኋላ በ57ኛዉ ደቂቃ በአማኑኤል ኤርቦ በኩል ዳግም መሪ መሆን የቻሉበትን ጎል አስቆጥረዋል።
ጨዋታዉ በ2-1 በጊዮርጊሶች መሪነት ቀጥሎ በ74ኛዉ ደቂቃ ፈረሰኞቹ ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ አቤል ያለዉ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ዉጤት ወደ 3-1 ከፍ አድርጓል።
ወልቂጤዎች የተወሰደባቸዉን የጨዋታ ብልጫ ለማስመለስ ጥረት አድርገዉ ለመጫወት ቢሞክሩም ነገር ግን ሳይሳካላቸዉ ቀርቶ በ87ኛዉ ደቂቃ ተገኑ ተሾመ ለፈረሰኞቹ አራተኛዉን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታዉ በፈረሰኞቹ 4-1 በሆነ ዉጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው አርብ ጥቅምት 2 በ9:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ሲጫወት በተከታዩ ቀን ቅዳሜ ጥቅምት 3 በተመሳሳይ ሰዓት ወልቂጤ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ጨዋታውን ያደርጋል ።