*….ስለኮንትራቴ አሁን የምናገረው ነገር የለም…..
ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የፊታችን እሁድ ከማሊ አቻው ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን አሰልጣኝ ፍሬው ሃ/ገብርኤል ተናገሩ።
አሰልጣኙ ዛሬ ከቀትር በኋላ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በሰጡት መግለጫ ቡድናቸው በቅጣት አርአያት ኦዶንጎ በጉዳት ደግሞ ነጻነት ጸጋዬ ከሚያጣው ውጪ ሌሎቹ በመልካም ጤንነት ሆነው ጨዋታውን እየጠበቁ ነው ። ከሜዳ ውጪ 2 ለ0 ብናሸንፍም ቀሪ 90 ደቂቃ ስላለ ጠንክረን ተጫውተን ውጤታችንን ለማስጠበቅ እንጥራለን ” ሲሉ አስረድተዋል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኙ እንደገለጹት “ተጨዋቾቼ ከሜዳችን ይልቅ ከሜዳ ውጪ ያላቸው በራስ መተማመን የሚያስደስት ነው … ከአመታት በፊት ወጣት ቡድኑን ይዞ በአርጀንቲና ሻምፒዮና ተሳታፊ እንዳደረጉን ፈረንሳዊው ዲያጎ ጋርዚያቶ ሁሉ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድኑን ለኮሎምቢያው የአለም ዋንጫ ለማብቃት እጥራለሁ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ወጣት ቡድኑን ስኬታማ ኤንዳደረገ ሁሉ እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ የጋርዚያቶን ገድል ለሀገሬ
መስራት እፈልጋለሁ ” ሲሉ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ከ20 አመት በታች የአሰልጣኝ ፍሬው ቦታ ይመስላል ..
የተባሉት አሰልጣኙም ” የአሰልጣኝነት ስራ ስጀምር የመጀመራያ ስራዬ የነበረው ከ20 አመት በታች ቡድን ነው የብሄራዊ ቡድኑን ሃላፊነት ከያዝኩ ጀምሮ አዳዲስ ተጨዋቾች እያመጣሁ ስለሆነም ደስተኛ ነኝ በዚህም ኩራት ይሰማኛል በዚህ ውድድር አገሬ ያመጣችው ዋንጫ በኔ በመሆኑም ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ከጅማሮው ስለያዝኩት ከ20 አመት በታች ውድድር ይለይብኛል ነገር ግን እንደ ሀገር በሚሰጠኝ አጠቃላይ ሃላፊነት ደስተኛ ነኝ” ሲሉ መልሰዋል።
ከማሊ ጋር ስላደረጉት ጨዋታ የተጠየቁት አሰልጣኙ “ማሊን ልንገጥም ስንሄድ በደንብ ተዘጋጅተን ነው የሄድነው ታክቲካሊ ጥሩ የሆኑ ተጨዋቾች አሏቸው ፕሮፌሽናል ሆነው ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጨዋቾችም አካተዋል ሀገሪቱ በሴቶች እግር ኳስ ጥሩ እየሰራች እንዳለ መረጃ አግኝቻለሁ…. ምንጊዜም ከሀገር ሲወጣ ጫና አለው ማሊያዊያን ግን በጥሩ ሁኔታ ተቀብለውናል ሌላ ሀገራት የምንቸገርበትን የአንድ ጊዜ ልምምድ ቦታ እነሱ ግን ሁለቴ ፈቅደውልናል በጥሩ ሁኔታ ተቀብለውን አስተናግደውናል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በኮንትራታቸው ዙሪያ የተጠየቁት አሰልጣኙ “ስለኮንትራቴ አሁን የምናገረው ነገር የለም ሂደቱን በቀጣይ የምናየው ይሆናል ” ሲሉ አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድናችን የእሁዱን ጨዋታ በድል ከተወጣ የመጨረሻውንና ወሳኙን ማጣሪያ ከጊኒና ሞሮኮ አሸናፊ ጋር የሚያደርጉ ይሆናል።