“በሊጉ አሁን ከሚከፈል ደመወዝ
ያልተጋነነ ክፍያ እንከፍላለን”
አቶ ባዩ አቡሃይ
/የክለቡ ፕሬዝዳንት/
“በፕሪሚየር ሊጉ የተሻሉ ከሚባሉ አሰልጣኞች
ያላነሰ ደመወዝ ይከፈለኛል”
አሰልጣኙ ውበቱ አባተ
“ከሚዲያ ጋር መልካም ግንኙነት አለን ነገር ግን የማያተርፍ ዜና ይፋ ማድረግ አይጠበቅብንም…”
አቶ አቢዮት ብርሃኑ
/ዋና ስራ አስኪያጅ/
” እንኳን 20 አዳዲስ ተጨዋች ማስፈረም የቤት እቃ ከቦታ ቦታ ማመላለስ ይከብዳል”
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
- ማሰታውቂያ -
“በፋሲል ከነማ ያየሁት የደጋፊ ስሜትና የአመራሩ ቁርጠኝነት ፣ የክለቡ አመራሮች ያሳዩኝ ክብርና በክለቡ ረዘም ያለ ጊዜ የምሰራበት መንገድ መመቻቸቱ ፋሲል ከነማን እንድመርጥ አድርጎኛል” ሲሉ አዲሱ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተናገሩ።
የሀትሪክ ድረገጽ ከታማኝ ምንጭ ባገኘችው መረጃ አሰልጣኙ ከወራት በፊት ለቀጣዩ ሶስት አመት ከፋሲል ከነማ ጋር ለመስራት መስማማታቸውን መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን ክለቡና አሰልጣኙም ዛሬ በጁፒተር ሆቴል በሰጡት ይፋዊ መግለጫ ይፋ አድርገውታል ።
“ፋሲል ከነማ የጎንደር አርማ ነው ክለባችን የኢትዮዽያ እግርኳስ ክስተት እንደሆነም ይታወቃል ከ2009 ጀምሮ በሀገሪቱ እግርኳስ ትልቅ አሻራ አምጥቷል ባለፉት አመታት በተከሰተው መጠነኛ የውጤት ማጣት በመገንዘብና ሂደቶችን ከመሰረቱ በመገምገም የ5 አመት ስትራቴጂ በማዘጋጀት አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ሾመናል” ያሉት የጎንደር ከተማ ከንቲባና የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ባዩ አቡሃይ ” አሰልጣኝ ውበቱ በቀጣዪቹ 3 አመታት በገባው ውል በ2016 ቡድናችንን ዋና ተፎካካሪ እንዲያደርጉ በ2017 ደግሞ ዋንጫ እንዲያመጡ ተስማምተናል። ከዚህ ውጪ ክለባችንን በምስራቅ አፍሪካ የሚታወቅ ክለብ እንዲሆን ማስቻል፣በዚህ ታሪካዊና በህዝብ ልብ ውስጥ የታተመ ክለብ የእግርኳሳችን ስጋት የሆነው የስነምግባር ጥሰትን አስወግዶ ተተኪ ታዳጊ እንዲያፈራ ተስማምተናል” ሲሉ አስረድተዋል።
የአራት ወር ደመወዝ ስላለመክፈላቸው የተጠየቁት አመራሮቹ “ፋሲል ከነማ ብሄራዊ ሊግም እያለ በደመወዝ አይታማም በአመራር ደረጃ በነበረ ልውውጥ የነበረ ክፍተት አለ አሁን ተስተካክሏል ክፍተቱም ታርሟል” ሲሉ መልሰዋል። ለዝውውር 100 ሚሊዮን ብር መድባችሁ በርካታ ተጨዋቾች እንድታስፈርሙላቸው አሰልጣኙ ጠይቀዋል ለሚለው ጥያቄ በተሰጠ ምላሽ “አሰልጣኙን ስንቀጥር መጠነኛ ተጨዋቾችን ጨምሮ ባሉት ተጨዋቾች ላይ ጠንካራ ቡድን እንዲገነባ እንጂ ዝም ብሎ የሚወጣ ብር የለም ክለባችንኮ በጎ አድራጊ ተቋም አይደለም እንደ አሰራር አሰልጣኙ ይጠቁማል እንጂ የዝውውር ኮሚቴ ስላለ ገንዘቡ ላይ አይገባም” ሲሉ መልሰዋል። አሰልጣኝ ውበቱም በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ ” እንኳን 20 አዳዲስ ተጨዋች ማስፈረም የቤት እቃ ከቦታ ቦታ ማመላለስ ይከብዳል” ሲሉ መረጃውን አስተባብለዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ በበኩላቸው “በየቀኑ ከተጨዋችና ከሚዲያ ጋር መገናኘቱ ይናፍቃል ዲ ኤስ ቲቪ ሲጀመር አንዱ የሊጉ አካል ባልሆንም ለብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋች ከዚያ እመርጥ ስለነበር ውድድሮችን መከታተሌ አልቀረም… ከእቅድ አንጻር በግሌ የማቅደው እቅድ የለም… ክለቡ ያቀደው እቅድ ነው የኔ እቅድ…በቀጣይ ከምንጨምራቸው አንዳንድ ባለሙያዎች ውጪ ካሉት አሰልጣኞች ጋር እቀጥላለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የአሰልጣኝ ውበቱ ዝውውር ሲነገር ለምን ቶሎ አስተባበላችሁ የተባሉት ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ አቢዮት ብርሃኑ በበኩላቸው ” በወቅቱ የአሰልጣኝ ቦታው በሌላ አሰልጣኝ ተይዞ ነበር ፌዴሬሽኑም እንደማይቀበለን እናውቅ ነበር አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከነበረብን ችግር አውጥቶ ከፍ ያለ ደረጃ ይዘን እንድንጨርስ አስችሏል ይሄም መከበር ነበረበት ለዚህ ነው ያስተባበልነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ከሚዲያ ያላችሁ ግንኙነት ጥሩ አይመስልም ይሄስ ለምን የሆነ ይመስላችኋል..? ለሚለው ጥያቄ ዋና ስራ አስኪያጁ በሰጡት ምላሽ ” እኛ ጥሩ ግንኙነት እንዳለን ነው የምናምነው… በርግጥ ምስጢር መጠበቅ ባለብን ጉዳይ ላይ እንጠብቃለን..ከአሰልጣኞችና ተጨዋቾች ጋር ባለን ግንኙነት ነገሮችን ላለማጦዝና ሚዲያ ላይ ቶሎ ወጥተን ላለመናቆር እንጥራለን እንደ አጠቃላይ ግን ከሚዲያ ጋር መልካም ግንኙነት አለን ነገር ግን የማያተርፍ ዜና ይፋ ማድረግ አይጠበቅብንም…” ሲሉ መልሰዋል።
በሶስት አመት ውል መሰረት የአሰልጣኙ ደመወዝ ስንት ነው ..? ተብለው ከሚዲያው ለቀረበ ተደጋጋሚ ጥያቄ አሰልጣኙና አመራሮቹ ቀጥተኛ ምላሽ ያልሰጡ ሲሆን አሰልጣኙ ውበቱ አባተ “በፕሪሚየር ሊጉ የተሻሉ ከሚባሉ አሰልጣኞች ያላነሰ ደመወዝ ይከፈለኛል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በበኩላቸው “በሊጉ አሁን ከሚከፈል ደመወዝ ያልተጋነነ ክፍያ እንከፍላለን” ሲሉ ተዘዋዋሪ ምላሽ ሰጥተዋል።
ያም ሆኖ በወር 400 ሺህ ይከፈላቸዋል … አይደለም የሚከፈላቸው 250 ሺህ ብር ነው …. አይደለም 415 ሺህ የተጣራ ደመወዝ ነው የሚያገኙት የሚሉ የመረጃ ምንጮችን ዘገባ አመራሮቹና አሰልጣኙ ማመንም ሆነ ማስተባበል ሳይችሉ ቀርተዋል።