ባህርዳር ከተማ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ እየተሳተፈ ይገኛል….የታንዛኒያውን አዛም በደርሶ መልስ የረታው ባህርዳር ከተማ የቱኒዚያውን ክለብ አፍሪካን ለመግጠም እየተዘጋጀ ነው….የሀትሪክ ድረገጹ ዮሴፍ ከፈለኝ በዚህ የክለቡ ዝግጅት ዙሪያና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከባህርዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጋር ያደረገው አጠር ያለ ቃለምልልስ የሚከተለው ይመስላል…
ሀትሪክ:- አዛምን በደርሶ መልስ አሸንፋችሁ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋችኋል…እንኳን ደስ አላችሁ..
ደግአረገ:- አመሰግናለሁ። እንኳን አብሮ ደስ አለን ..ጥሩ ውጤትም በመሆኑ ደስ ብሎኛል …
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ:- ከዋሊያዎቹ ጋር ያደረጋችሁት ጨዋታ ምን ልምድ አስገኝቶልናል ትላለህ…?
ደግአረገ:- ከዋሊያዎቹ ጋር ያደረኩት ጉዞ ከሀገር ውጪ የመጀመሪያዬ ጉዞ በመሆኑ ጥሩ ተሞክሬ አግኝቼበታለሁ ከአዛም ጋር ለነበረንም የደርሶ መልስ ጨዋታ ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ ነበረው… እንደ ሀገር ከሚኖረው ጨዋታ አስቀድሞ የወዳጅነት ጨዋታ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ግልጽ ነው… እንደ ባህርዳር ከተማ የነበረን ተሞክሮ ውስን ነው ምናልባት በጣና ካፕ ሁለት ክለቦች ከውጪ መጥተው ስለነበር ከነሱ ጋር ያደረግነው ውደድር እንደ አንድ ተሞክሮ ሊወሰድ ይችል ይሆናል ..እንደ አጠቃላይ ግን አዛም አራት የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ መምጣቱ ምን ያህል ጥሩ ልምድ ይዘው እንደመጡ ያሳያል እኛ ጋር ግን ከነበረው ጊዜ አንጻር አስቸጋሪ ነበር ያም ሆኖ ተጨዋቾቼ ጠንካራ ተጋድሎ አድርገው ራሳቸውን አይተው ማሸነፍ ችለዋል ከክለብ አፍሪካ ጋር ላለብን ጨዋታ ትልቅ ስንቅ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ።
ሀትሪክ:- ከአዛም ጋር በነበራችሁ ጨዋታና ቆይታ ለኛ ሀገር ክለቦች የተገኘ ጥሩ ተሞክሮ ነበር..?
ደግአረገ:-/ ሳቅ/ ያስቀናል … በጣም ይገርማሉ ካየሁት ተነስቼ ስናገር በጣም የተደራጀ ነው …የልምምድ ሜዳውን የመጎብኘት ዕድል ነበረኝና የተጨዋቾች ማረፊያ እጅግ ዘመናዊ ነው ከሜዳው ጎል ጀርባ ነው የሚገኘው ሌላው የገረመኝ እጅግ ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ አለው … ክለቡ ሙሉ ማቴሪያል ያሟላ ዘመናዊ የራሱ የሆነ ጂም አለው … በአጋጣሚ ለጉብኝት ስንደርስ ተጨዋቾቹ ልምምድ እየሰሩ ነው የደረስነው…. ተጨዋቾቹ የግል ብቃታቸውን ለማሳደግና ብቁ ሆነው ለመገኘት ሲሰሩ አይተናል… ከአርቴፊሻል ሜዳ ውጪ ሌላም ሜዳ አላቸው ሶስተኛም በአሸዋ የተሞላ ሜዳ አላቸው ሶስቱም ሜዳዎች በተጨዋቾቻቸው የተሞሉ ናቸው ሜዳው ትንሽ ከ10-15 ሺህ ህዝብ ቢይዝ ነው በቀላል መንገድ ነው የተሰራው ብረት ገጣጥመው ወንበር አስቀምጠው ነው የገነቡት …ሜዳው ግን የተደረገበት ጥንቃቄና ልፋት ልዩ ነው እኛ ሀገር ግን አስገራሚ በርካታ ህዝብ የሚይዙ ስታዲየሞች አሉን የሜዳዎቹ ጥራት ግን ጥሩ የሚባል አይደለም ለንጽጽርም አይቀርብም ትልቁ ስራ ተሰርቶ ውስጥ ያለው መጫወቻ ሜዳ ግን ትኩረት አልተደረገበትም….ሜዳዎቹ ላይ ትኩረት ቢደረግ የተሻሉ የሚባሉ ስታዲየሞች ባለቤት ነን በአጠቃላይ ያየነው ነገር አስቀንቶኛል የክለቡን አርማ የያዙ ሁለት ባሶችንም አይተናል በአጠቃላይ ተገርሜ ነው የተመለስኩት ….
ሀትሪክ:- ቀጣዩ ተጋጣሚ የቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ነውና ስለቡድኑ መረጃ አገኛችሁ..?
ደግአረገ:- የክለቡን አጨዋወትና የተሻለ አቋም የሚያሳይ
መረጃዎችን እየፈለግን ነው .. ከዚያው ጎን ቡድናችን ተሰባስቦ ልምምዱን ቀጥሏል በተሻለ መንገድ ተዘጋጅተን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እንጥራለን….
ሀትሪክ:- ወሳኝ ተጨዋቾቻችሁ ለዋሊያዎቹ ተጠርተው መሄዳቸው ሙሉ ዝግጅቱን አላጎደለውም…?
ደግአረገ:- አዎ …ወደ አራት ተጨዋቾች ሀገራቸውን ለማገልገል ሀገራዊ ግዴታውን ተቀብለው ወደ ግብጽ ተጉዘዋል.. ቡድኑ ላይ የሚጠበቁ መሆናቸውም ያስደስታል .. ካይሮ ላይ በሚኖራቸውም ጨዋታ ከጨዋታው በፊትም በሚኖራቸው የዝግጅት ጊዜ ጥሩ የሆነ ስራ ይሰራሉ ብለን እናምናለን ከግብጽ ጨዋታ መልስ ከእኛ ጋር የሚዘጋጁበት ጊዜ ስላለ ጥሩ ስራ የመስራት እድል ይሰጠናል። ከግብጽ ጋር ጳጉሜ 3/2015 ተጫውተው በማግስቱ ጳጉሜ 4 ስለሚመለሱ ከክለብ አፍሪካ ጋር መስከረም 6/2016 እስክንጫወት ጊዜ ድረስ ወደ 8 ጥሩ የምንዘጋጅበት ቀናቶች ይኖረናል። ጥሩው አጋጣሚ የመጀመሪያ ጨዋታ እዚሁ አበበ ቢቂላ ስታዲየም መካሄዱ ትልቅ ጥቅም አለው… ተጨዋቾቼ ከአዛም ጋር ባገኙት ልምድ በጥሩ የራስ መተማመን ለጨዋታው ይቀርባሉ ብዬ አስባለሁ… በጨዋታው ወደ ቀጣዩ ዙር የምናልፍበት ሀገራችንን የምናኮራበት ይሆናልና ብዬ አምናለሁ።
ሀትሪክ:- የዝውውር መስኮቱ ተዘግቷል በነበረው የዝውውር ጊዜ ጥሩ ተሳትፎ አደረጋችሁ..? ጠንካራውን ከ2015 የተሻለውን ቡድን በ2016 ይዛችሁ ትቀርባላችሁ…?
ደግአረገ:- በነበረው የዝውውር መስኮቱ ሊጉ ላይ ጥሩ የነበሩና ለክለባችን ይመጥናሉ ያልናቸውን ተጨዋቾች አግኝተናል የነበሩትን ለማቆየት ሞክረን ሳይሳካልን ቢቀርም ባሉን የተሻለ ተዘጋጅተን ጥሩ የተባለውን ተፎካካሪ ክለብ ለማሳየት እንጥራለን። ያው እንደሚታወቀው የዝውውር የመስኮቱን የፈለከውን ተጨዋች እንደፈለከው የምታገኝበት አይደለም ፕላን ኤ
ፕላን ቢ ፕላን ሲ እያልክ ነው የምትሄደውና ክለቡን ለማጠናከርና ጥሩ ቡድን ለመገንባት እየሰራን ነው ማለት ይቻላል። ለአፍሪካ ኮንፌዴሬችን ካፕ የምናደርገው ዝግጅት በዋናነት ለፕሪሚየር ሊጉ ውድድርም የሚያገለግል ነውና በ2016 ጠንካራውን ባህርዳር ከተማ ይዘን እንቀርባለን ብዬ አምናለሁ
ሀትሪክ :- አመሰግናለሁ…።