*…. ሰባት ክለቦች ተሳታፊ ናቸው…..
*…አዳማ ከተማና ሀድያ ሆሳዕና ተጋባዥ ክለቦች ናቸው..
ሰባት ክለቦች በሁለት ምድብ ተደልድለው የሚፋለሙበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ነገ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
በወጣው መርሃግብር መሰረት ነገ ከቀኑ 8 ሰአት ላይ ሃድያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይጫወታሉ። ጨዋታው የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌና የአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የታክቲክ ፍልሚያ የሚታይበት ይሆናል። ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሻሸመኔ ከተማ ይገናኛሉ። አዲሱ የቡናማዎቹ አሰልጣኝ ሰርቪያዊው ኮቫዞቪች ኒኮላ ቡድናቸውን የሚያዩበት ሲሆን የአሰልጣኝ ጸጋዬ አዲሱ አዳጊ ክለብ ሻሸመኔ ከተማም ከ2 ሳምንት በኋላ ለሚጀመረው ፕሪሚየር ሊግ ራሳቸውን የሚያዩበትና የሚዘጋጁበት ጨዋታ ይሆናል ተብሏል።
- ማሰታውቂያ -
የዕለተ ማክሰኞ ብቸኛ ጨዋታ የሆነውና በ8 ሰአት የሚካሄደው የአዳማ ከተማና የኢትዮጵያ መድን ፍልሚያ ይጠበቃል። በዚህ ጨዋታ ወጣቱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለና በሊጉ ሻምፒዮን ከሆኑት አሰልጣኞች መሃል ከሁለት ክለቦች ጋር ዋንጫ በማንሳት ብቸኛ በሆነው አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ መሃል ያለው ፉክክር ይጠበቃል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄደው 17ኛው የሲቲ ካፕ ፍልሚያ ላይ በምድብ ሀ የምድብ አባት ኢትዮጵያ ቡና ሲሆን ሀድያ ሆሳእና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሻሸመኔ ከተማ ተደልድለዋል። በምድብ ሁለት ቅዱስ ጊዮርጊስ የቡድን አባት ሲሆን አዳማ ከተማና ኢትዮጵያ መድን በምድቡ ውስጥ ይገኛሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከመስከረም 7-13/2016 ድረስ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚካሄድ የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ አስታውቋል።