ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ትላንት ምሽት በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ የመልስ ጨዋታ የሞሮኮዉ ዋይዳድ ካዛብላንካ እና የግብፁ አላህሊ ያደረጉትን ጨዋታ በብቃት መምራቱ የሚታወስ ነዉ ፤ በዚህ ተጠባቂ የፍፃሜ የመልስ ጨዋታም የግብፁ ክለብ አላህሊ በደርሶ መልስ ዋይዳድ ካዛብላንካን 3ለ2 በሆነ ውጤት በመርታት የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆኑን ማረጋገጡ ይታወቃል።
ከተጠባቂዉ የፍፃሜ ጨዋታ አስቀድሞ የግብፁ ክለብ አላህሊ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ስዊዘርላንዳዊው ማርሴል ኮለር ባምላክ በፍፃሜዉ የመልስ ጨዋታ ላይ መመደቡን ተከትሎ ያላቸዉን ተቃውሞ በተደጋጋሚ ሲያሰሙ እንደነበርም አይዘነጋም።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከፍፃሜ ጨዋታ በኋላም በርካታ የስፖርቱ ዘርፍ ትልልቅ ሚዲያዎች የትላንት ምሽቱ የፍፃሜ ጨዋታ የባምላክ የመጨረሻው መሆኑን ሲገልፁ መቆየታቸዉ የሚታወስ ሲሆን ፤ ነገር ግን ይህ የሚሰራጨዉ ዜና ሀሰት መሆኑን እና ዳኛዉ ከዚህም በላይ በአፍሪካ እንዲሁም በአለምአቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ በዳኝነት እንደሚቀጥል ታውቋል።