በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ቀዳሚ ጨዋታ መቻል ወልቂጤ ከተማን 2 – 0 አሸንፏል ።
ወልቂጤ ከተማዎች በ27ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በተመስገን በጅሮንድ ምትክ ኤፍሬም ዘካርያስን አሰልፈዋል ። በመቻል በኩል በሳምንቱ በባህርዳር ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ስድስት ለውጦች በማድረግ ዳግም ተፈራ ፣ ያብስራ ሙሉጌታ ፣ ግርማ ዲሳሳ ፣ በኃይሉ ግርማ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ምንይሉ ወንድሙን በውብሸት ጭላሎ ፣ ቶማስ ስምረቱ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ተሾመ በላቸው እና እስራኤል እሸቱ ተክተው በመግባት ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው መቻል በተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከተጋጣሚው ተሽሎ አጋማሹን አሳልፏል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይም ከነአን ማርክነህ ለሳሙኤል ሳሊሶ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሳሙኤል አስቆጠረው ተብሎ ቢጠበቅም የግብ ሙከራው ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
- ማሰታውቂያ -
የተሻለ ጫና በመፍጠር የማጥቃት ሂደታቸውን እያጠናከሩ የሄዱት መቻሎች ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። በወልቂጤ ከተማ በኩል በቀደሙት ጨዋታዎች ላይ እንደሚታየው የቡድኑን ወሳኝ ተጫዋች ጌታነህ ከበደን ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ፊት ለማድረስ ቢጥሩም የመቻል ተከላካዮች ያንን የፈቀዱ አልነበሩም ።
የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በ17ኛው ደቂቃ ላይ ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ የግብ ሙከራ በቀርም ዳግም ተፈራን የፈተነ የግብ ሙከራ በአጥቂውም ሆነ አጠቃላይ በቡድኑ በኩል አልተደረገም ።
በመቻል በኩልም በተደጋጋሚ ወደ ወልቂጤ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው የነበረ ቢሆንም የሚፈጠሩት የግብ ዕድሎች በጠንካራ የግብ ሙከራዎችች የታጀቡ አልነበሩም ። በ28ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች ቀዳሚ መሆን የቻሉበትንም የግብ ዕድል ያገኙ ቢመስሉም በረከት ደስታ ከሳሙኤል ሳሊሶ የደረሰውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ በመቻል በኩል ግብ ተቆጥሯል ። የወልቂጤ ከተማው አስራት መገርሳ መዘናጋት ሚናው ከፍ ብሎ በታየበት በዚሆ አጋጣሚ ምንይሉ ወንደሙ ከከነአን ማርክነህ የተቀበለውን ኳስ በቀላሉ ከመረብ አሳርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በመቻል የ1 – 0 መሪነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የአቻነቱን ግብ ለማግኘት ጥረቶች አድርገዋል ።
በተለይም በመስመሮች በሚደረጉ የማጥቃት ሂደቶች የመቻልን የኋላ ክፍል ለመፈተን ያደረጓቸው ጥረቶች በጠንካራ የግብ ሙከራዎች አልታጀቡም ።
በ64ኛው ደቂቃ ላይ ግን መቻሎች ሁለተኛ ግባቸውን አግኝዋል ። ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ግብ ሲያሻግረው ግብ ጠባቂው ፋሪስ አሎው በሚገባ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱ የግሩም ሐጎስን ጀርባ ነክቶ ከመረብ ላይ አርፏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልልሎች ለመድረስ የሚደረጉ ሙከራዎች እምብዛም የነበሩ ሲሆን ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ግን የተሻሉ የግብ ሙከራዎች በመቻልም ሆነ በወልቂጤ ከተማ በኩል ተደርገዋል ።
ነገር ግን እነዚህ ሙራዎች ወደ ግብነት ሳይቀየሩ ጨዋታት በመቻል የ2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ29ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 22 ሐሙስ ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ ወልቂጤ ከተማ ከወላይታ ድቻ ሲጫወቱ ሰኔ 24 በተመሳሳይ ሰዓት መቻል ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ ።