በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር የ26ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከአናት የተቀመጡትን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማን አገናኝቶ 2 – 2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ27ኛው ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን በረቱበት ጨዋታ ላይ በነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በባህሩ ነጋሽ እና አማኑኤል ተርፉ ምትክ ቻርለስ ሉክዋጎ እና ፍሪምፖንግ ሜንሱህ ተክተው ገብተዋል ። በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በሚመራው ባህርዳር ከተማ በኩልም በተመሳሳይ በሳምንቱ መቻልን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በፉዓድ ፈረጃ ምትክ ቻርለስ ሪባኑን ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን ከኋላ መስርተው ለመውጣት ጥረት በማድረግ የጀመሩት ሲሆን በባህርዳር ከተማ በኩል ተጭነው ወደ ፊት በመጠጋት አንድም ፈረሰኞቹ ኳሱን መስርተው እንዳይወጡ እንዲሁም በሚነጠቁ ኳሶች ወድያውኑ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል ።
ኳሱን ይዘው ከሜዳቸው ለመውጣት የተቸገሩት ፈረሰኞቹ የመጀመሪያ የግብ ዕድል ለመፍጠር በቻሉበት 14ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ቢንያም በላይ ከቀኝ አቅጣጫ በአየር ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ቸርነት ጉግሳ በግንባር በመግጨት ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ ማድረግ ችሏል ።
ከግቡ መቆጠር ሰከንዶች በኋላ የቢንያም እና የቸርነት ጥምረት ዳግም የታየበት የግብ ሙከራ አጋጣሚ በፋሲል ገብረሚካኤል ግብ ከመሆን ድኗል ።
ከግቡ በኋላ የጣና ሞገዶቹ በይበልጥ ተጭነው በመጫወት የአቻነት ግብ ፈልገዋል ። በቀላሉ ለመስበር የማይቻለው እና በውድድር አመቱ በ26 ጨዋታዎች 17 ግቦችን ብቻ ያስተናገደው የቅዱስ ጊዮርጊስ የኋላ መስመር እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ ጠንካራ የግብ ዕድሎች እንዳይፈጠሩ ማድረግ ችለዋል ።
በ30ኛው ደቂቃ ላይ ግን ድንቅ የውድድር አመትን እያሳለፈ የሚገኘው አለልኝ አዘነ ቀደም ባሉ ጨዋታዎች ላይ ያስቆጥር የነበረው አይነት ግብ በቻርለስ ሉክዋጎ መረብ ላይ አሳርፏል ።
አለልኝ አዘነ ከሳጥኑ ውጪ ከቻርለስ ሪባኑ የደረሰውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ነው የጨዋታውን ውጤት ወደ 1 – 1 ለመቀየር የቻለው ።
በቀጣዮቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ጨዋታ አጋማሹ ከመጠናቀቁ በፊት ሌላ ግብ አስተናግዷል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል በግራ አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት ፍራኦል መንግስቱ በግራ እግሩ ወደ ግብ ሲያሻግር በናትናኤል ዘለቀ ጭንቅላት ተጨርፎ ከመረብ ላይ አርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው ክፍለጊዜም በባህርዳር ከተማ የ2 – 1 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሀል የሜዳው ክፍል ላይ በአንፃራዊነት የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ በሚመስል መልኩ ጋቶች ፓኖምን በሀይደር ሸረፋ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
አጋማሹን በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ፈረሰኞቹ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴው እምብዛም በነበረው አቤል ያለው አማካኝነት ተደጋጋሚ የማጥቃት አጋጣሚዎች ለመፍጠር ችለዋል ።
ከአቤል ያለው ባሻገር በ47ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የነበረው ቸርነት ጉግሳ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ለእስማኤል ኦሮ አጎሮ ለማቀበል ያደረገው ሙከራ በፋሲል ገ/ሚካኤል ተይዟል ።
በ50ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፈረሰኞቹ ግብ አስቆጥረዋል ። አቤል ያለው ! 10 ቁጥር ለባሹ አቤል ያለው ከቢንያም በላይ የተቀበለውን ኳስ በግቡ የቀኝ ቋሚ አስታኮ በመምታት በፋሲል ገብረሚካኤል መረብ ላይ አሳርፏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ፈረሰኞቹ በይበልጥ በሁለቱ መስመሮች ለመጠቀም ጥረቶችን ቢያደርጉም ውጤታማ አልነበሩም ። በተጨማሪም የሊጉን ኮከብ ግብ አስቆጣሪ እስማኤል ኦሮ አጎሮን ኢላማ ያደረጉ ኳሶች ወደ ፊት ቢላኩም በተደጋጋሚ ከጨዋታዉ ውጪ ሆነዋል ።በባህርዳር ከተማ በኩል በተለይም እንደ አደም አባስ ፣ ፉዓድ ፈረጃ እንዲሁም ማማዱ ሲዲቤ አይነት የማጥቃት ሚና ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን አድርገዋል ።
የጣና ሞገዶቹ በአለልኝ አዘነ እና በፉዓድ ፈረጃ ካደረጓቸው ያልተሳኩ የቆሙ ኳስ ሙከራዎች ባለፈም በፍራኦል መንግስቱ ወደ ግብ ተሻግሮ ሉክዋጎ ባወጣው ኳስ የግብ አጋጣሚዎች ለመፍጠረ ችለዋል ።
በ87ኛው ደቂቃ ላይም በፈጣን እንቅስቃሴ ማማዱ ሲዲቤ ከቀኝ አቅጣጫ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ፉዓድ አግኝቶ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በ90+1 ደቂቃ ላይ የፈረሰኞቹ የመሀል ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱህ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሂደት ከግራ አቅጣጫ ለአጎሮ ለማድረስ የላከው ኳስ በያሬድ ባየህ ተመልሷል ።
በመጨረሻም ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታው በ2 – 2 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 59 በማድረስ መሪነቱን ሲያስቀጥል ባህርዳር ከተማ በ54 ነጥቦች ተከታዩን ደረጃ ይዟል ።