በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሀያ ስምንተኛ ሳምንት ሁለተኛ ዕለት ጨዋታ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ላይ የተገናኙት አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታቸውን ሶስት አቻ በሆነ ዉጤት አጠናቀዋል።
ተመጣጣኝ በሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በተለይ በሜዳዉ የመሐል ክፍል ላይ ከፍተኛ ፉክክር ያስመለከተን ሲሆን ፤ በጨዋታው መባቻ 7ተኛው ደቂቃ ላይም አዳማ ከተማ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
በዚህም የሀድያዉ ተከላካይ ግርማ በቀለ ዮናታን ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠዉን ቅጣት ምት ረዘም ላሉ ሳምንታት በጉዳት ላይ ያሳለፈው አጥቂው ዳዋ ሁቴሳ በቀጥታ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ መነቃቃት ያሳዩት አዳማዎች ያስቆጠሯትን ግብ ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ እና የሚያገኟቸዉን አጋጣሚዎችም በቶሎ ፊት መስመር ላይ ለሚገኙት ተጫዋች በማቀበል ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሰመጥሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በተቃራኒው ጥሩ የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢያስመለክቱም ግብ ማስቆጠርም ሆነ ተጠቃሽ የሚባል ሙከራን ለማድረግ የተቸገሩ የሚመስሉት ሀድያዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ የተወሰኑ ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅት ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በዚህም በ39ነኛዉ ደቂቃ ላይ የሀድያዉ ግብ ጠባቂ አሜ መሐመድ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ ወደ ግብነት በመቀየር ለራሱም ለክለቡም ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ምንም እንኳን ሁለት ግብ ይቆጠርባቸዉ እንጅ በእንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩት ሀድያዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ አጋማሹ እንደተጀመረ ወዲያውኑ አዳማ ከተማዎች ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም በ47ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ተከላካዩ አዲስ ተስፋየ በግንባሩ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ሶስተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ በሜዳ ላይ ጥሩ በመንቀሳቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲጥሩ የነበሩት ሀድያዎች በ53ተኛዉ ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸዉን ግብ በሰመረ ሀፍተይ አማካኝነት ማስቆጠር ችለዋል። ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ ጫና መፍጠር የቻሉት ሀድያዎች ከግቧ መቅጠር ከአስር ደቂቃ በኋላም ሁለተኛ ግብ ማግኘት ችለዋል ፤ በዚህም የአዳማዉ ተከላካይ ተመስገን ብርሀኑ ሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት አጥቂዉ ባየ ገዛኸኝ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።
ከሶስት ለዜሮ መመራት ወደ ሶስት ለሁለት ከፍ ማለት የቻሉት ሀድያዎች ከተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ በ83ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ አጥቂዉ ባየ ገዛኸኝ ከርቀት አስደናቂ ግብ በማስቆጠር ክለቡ ሀድያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ ጨዋታውን ሶስት አቻ በሆነ ዉጤት እንዲያጠናቀቅ ማድረግ ችሏል። ዉጤቱን ተከትሎም ሀድያ በ40 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፤ በተቃራኒው አዳማ ከተማ ደግሞ በ37 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።