የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሶስት ቀናት በኋላ ወደ ውድድር ሲመለስ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም በተደረገው የ28ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲን 2 – 1 አሸንፏል ።
በ27ኛው ሳምንት ከሲዳማ ቡና አቻ የተለያዩት አርባምንጭ ከተማዎች በጨዋታው ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ አበበ ጥላሁን ፣ ወርቅይታደስ አበበን እና ቡጣቃ ሸመናን በአካሉ አትሞ ፣ አሸናፊ ፊዳ እና አቡበከር ሻሚል ተክተው ገብተዋል ። በሳምንቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተረቱት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በበኩላቸው አራት ለውጦችን በማድረግ በተስፋዬ ነጋሽ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ መሀመድ አበራ እና አማኑኤል አረቦ ምትክ አቤል አየለ ፣ አስናቀ ተስፋዬ ፣ ሱራፌል አወል እና ካርሎስ ዳምጠውን ተክተው ገብተዋል ።
በጨዋታው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የግድ ከጨዋታዉ ሶስት ነጥቦችን ማግኘት የነበረበት አርባምንጭ ከተማ ጨዋታውን በብልጫ መጀመር ችሏል ። አዞዎቹ በተደጋጋሚም ፊት መስመር ለሚገኙ ተጫዋቾች በሚላኩ ኳሶችም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶች አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
አዞዎቹ ብልጫውን ወስደው በመጫወት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ቢጥሩም የለገጣፎ ለገዳዲ የኋላ ከፍል አልፈው ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረው ቆይተዋል ።
ጨዋታው 18ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አሸናፊ ፊዳ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከተመስገን ደረሰ የተላከለትን ኳስ ለመጠቀም ሲሞክር በአስናቀ ተስፋዬ በተሰራበት ጥፋት አዞዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም አህመድ ሁሴን ከመረብ አሳርፎታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ35ኛው ደቂቃ ላይ ግን ለገጣፎ ለገዳዲዎች አቻ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ሱራፌል አወል ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት የተገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
ከግቡ መቆጠር ሰከንዶች ቆይታ በኋላ አስናቀ ተስፋዬ ወርቅይታደስ አበበ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜም በ1 – 1 ውጤት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽም አርባምንጭ ከተማዎች ይበልጥ ጫና በመፍጠር ከጨዋታው ውጤት ይዘው ለመውጣት ጥረቶች ያደረጉበት ነበር ።
አዞዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ለገጣፎ ለገዳዲ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶች ቢያደርጉም የለገጣፎ ለገዳዲውን ግብ ጠባቂ ኮፊ ሜንሳህን የፈተነ የግብ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል ።
በ61ኛው ደቂቃ ላይ ግን የለገጣፎ ለገዳዲን መረብ በጨዋታው ለሁለተኛ ጊዜ ማግኘት ችለዋል ። የአርባምንጭ ከተማን ቀዳሚ ግብ ያስቆጠረው አህመድ ሁሴን ከወርቅይታደስ አበበ የተሻገረለትን ኳስ ከመረብ ላይ አሳርፏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም አዞዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማከል ተጭነው ሲጫወቱ ለገጣፎ ለገዳዲዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከኳስ ጀርባ ለማሳለፍ ተገደዋል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ አርባምንጭ ከተማዎች በተለይም በኤሪክ ካፓይቶ አማካኝነት በ79ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጉት ሙከራን ጨምሮ ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል ።
በመጨረሻም በበረከት ደሙ በሚመራው አርባምንጭ ከተማ የ2 – 1 ድል ጨዋታው ተጠናቋል ።