በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ለረጅም አመታት በረዳት አርቢትርነት ያገለገሉት ኮሚሽነር ተስፋዬ ኦሜጋ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሆነው ተሾሙ።
በ1986 የዳኝነት ኮርስ ወስደው የዳኝነቱን ዓለም የተቀላቀሉት ኮሚሽነር ተስፋዬ የዳኝነት ህይወት ለ15 አመታት የዘለቀ ሲሆን ፌዴራልና ኢንተርናሽናል ረዳት አርቢትር ሆነው የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ምስጉን ዳኛ ሆነው ተመርጠዋል። በርካታ ኢንተርናሽናሽናል ጨዋታዎችንም የመሩት ኮሚሽነር ተስፋዬ ባለፉት ሁለት አመታት የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትንት አገልግለዋል።
በሹመቱ ዙሪያ የተጠየቁት ኮሚሽነር ተስፋዬ ” በጣም ደስ ብሎኛል መንግስት በሚሰጠኝ አቅጣጫ የአዲስ አበባን ስፖርት የተሻለ ደረጃ ለማድረስ አብረውኝ ከሚሰሩ ባለሙያዎች ጋር በጋራ ስኬታማ ስራዎች እንደምሰራ ተስፋ አደርጋለሁ። ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ለአዲስ አበባ ስፖርት ዕድገት መስራት በላይ የሚያስደስት ነገር የለምና ስኬታማ ስራ ለመስራትም ተዘጋጅቻለሁ” ብለዋል። እንደ ኮሚሽነር ተስፋዬ አገላለጽ ” በተለይ የዛሬ አመት በተካሄደው የፌዴሬሽን ምርጫ ባይሳካም ያለኝን አቅም በመረዳት እንድመረጥ ሚዲያው ላደረገው ድጋፍ አመሰግናለሁ በቀጣይም አብሬያቸው እንደምሰራ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ኮሚሸነር ተስፋዬ ከቢሮው ሃላፊ አቶ በላይ ደጀን ጋር በሚፈጥሩት ጥምረት የከተማው ስፖርት ካለበት ደረጃ ወደ ተሻለ ከፍታ እንዲወጣ ያደርጋሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል
ኮሚሽነር ተስፋዬ በወርልድ ቴኳንዶ ከነበረባቸው ሃላፊነት በተጨማሪ የጉለሌ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነውም ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በከተማው ስፖርት ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የኮሚሽነር ተስፋዬ ሹመት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
ኮሚሽነር ተስፋዬ ኦሜጋ በተለይ በቅርብ አመታቶች በርካታ የፕሪሚር ሊጉን ጨዋታዎችን በኮሚሽነርነት የመሩ ልምድ ያላቸው ባለሙያ መሆናቸውን አብረዋቸው የሰሩ ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል። በዳኝነት አለም ከፍተኛ ድርሻ ከነበራቸው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በኮሚሽነርነት እያገለገሉ ከነበሩት ኮሚሽነር ሳራ ሰኢድ ጋር ትዳር የመሰረቱት ኮሚሽነር ተስፋዬ የሁለት ልጆች አባትም ናቸው።