በ8ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ አንድ ጨዋታ የተከናወነ ሲሆን በጨዋታውም ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬደዋ ከተማን 3-2 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ አስተያየታቸውን ሲጀምሩ “ዛሬ ስለተቆሩብን ሁለት ግቦች መነጋገር አለብን። ምክንያቱም ባለፉት 7ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ ሁለት ግቦች አልተቆጠሩብንም። ግን 3ግቦች አስቆጥረናል፤ 3ነጥቦች አግኝተናል፤ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ተጫውተናል። በሁለተኛው አጋማሽም በጋዲሳ መብራቴ ግሩም ግብ ማስቆጠር ችለናል።” ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም “በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረነው ነበር ከዛ በኋላ ግን ትኩረት ማጣት ለድሬደዋዎች ሁለት ግብ እንዲያስቆጥሩ አድርጓቸዋል ብለዋል።” ስለሁለቱ አጥቂዎቻቸው ጉዳት የተጠየቁት አሰልጣኙ “እስካሁን ስለ ጉዳታቸው ያወቅኩት ነገር የለም፤ ከሀኪሞች ጋር እንመክራለን።” በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።
የድሬደዋ ከተማው አሰልጣኝ ስምዖን አባይ “እንደ እንቅስቃሴ የምናየው ከሆነ ውጤቱ አይገባንም፤ የነበሩብንን ስህተቶች ማረም አልቻልንም። አሁንም ጨዋታ በተጀመረ በ10 እና በ15 ደቂቃዎች ግቦች ይቆጠሩብናል። እነዚህ ስህተቶች ናቸው ዛሬም ዋጋ ያስከፈሉን። ግን ዛሬ በቡድኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለናል። ማጋነን አይሁንብኝ እና 90ደቂቃ በኳስ ብልጫ መውሰድ ችለናል። ውጤቱ ጨዋታውን ይገልጻል ብዬ አላምንም።” ብለዋል። አሰልጣኙ ስለተጋጣሚያቸው ተጠይቀው ሲመልሱ “ሶስት አጋጣሚዎች አግኝተው ተጠቀሙ፤ ሌላ ምንም ያየሁት ነገር የለም።” በማለት መልሰዋል።