እንግሊዛዊው አሰልጣኝ ስቴዋርት ሃል ላለፉት ስምንት ወራት ፈረሰኞቹን ሲያሰለጥኑ የነበሩት ሲሆን በዛሬው እለት የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አስገብተዋል ሲል ክለቡ በይፋዊ ገፁ (#Saint George S.A) አስታውቋል።
አሰልጣኙ በዛሬው እለት በልምምድ ሜዳ ያልተገኙ ሲሆን ከክለቡ ውጤት ማጣት ጋር ተያይዞ ስራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለመልቀቅ ነው የስንብት ደብዳቤ ያስገቡት።
ይሁንና የአሰልጣኙን የስንብት ደብዳቤ በተመለከተ ከክለቡ የቦርድ አመራር ምላሽ እየተጠበቀ ነው።
በ2011 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ24 ሳምንታት ጉዞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወጥ አቋም ባለማሳየት 39 ነጥቦችን ሰብስቦ በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዡ አራተኛ ላይ ይገኛል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ 14 ጊዜ ሲያነሳ ፤ ባለፈው ዓመት ዋንጫውን በጅማ አባ ጅፋር የተነጠቀ ሲሆን ዘንድሮም ሊጉ ሊጠናቀቅ የስድስት ጨዋታዎች ዕድሜ እየቀሩት ከመሪው መቐለ 70 እንደርታ በዘጠኝ ነጥብ እርቆ ይገኛል፡፡