በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ድል ሲቀናው ፋሲል ከተማ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
ኢትዮጵያ ቡና ሳሙኤል ሳኑሚ በ69ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ያሸነፈው። በዚህም ፋሲል ከተማን በአንድ ነጥብ በልጦ በ20 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ከወላይታ ድቻ ጋር ተጫውቶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
አላዛር ፋሲካ በ1ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ወላይታ ድቻ መምራት ቢጀምርም ከአምስት ደቂቃ በኋላ ፍቅረስላሴ ተክለብርሃን ንግድ ባንክን አቻ አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -
በ43ኛው ደቂቃ ደግሞ ቢንያም በላይ ንግድ ባንክን ወደ መሪነት መልሷል፤ ከዚያም በ83ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዩ ለወላይታ ድቻ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል።
ባለፈው ሳምንት በሊጉ ሁለተኛውን ሽንፈቱን በደደቢት ያስተናገደው ፋሲል ከተማ ከመከላከያ ጋር ያደረገው ጨዋታ 2 ለ 2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ለፋሲል አብዱራህማን ሙባረክ ሁለቱንም ግቦች አስቆጥሯል። ማራኪ ወርቁ እና ሳሙኤል ታዬ ደግሞ መከላከያን አቻ ያደረጉ ጎሎች አስቆጥረዋል።
በጨዋታው የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ50ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬም ሲቀጥል በክልል ከተሞች ሶስት፤ በአዲስ አበባ ደግሞ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በክልል ከተሞች ጅማ ላይ ጅማ አባቡና ወልድያ ከተማን ሲገጥም፣ አርባምንጭ ከተማ ሲዳማ ቡናን እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን በተመሳሳይ 9 ስአት ላይ ያስተናግዳሉ። 22 ነጥብ በመሰብሰብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 ስአት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል።
ዛሬ የሊጉ መሪዎች አዳማ ከተማ እና ደደቢት 11 ስአት ከ30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።